ዋዜማ- የሱማሊያዋ ፑንትላንድ ራስ ገዝ፣ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሃመድ ለሚመሩት የሱማሊያ ፌደራል መንግሥት እውቅና መንፈጓንና ከፌደሬሽኑ በይፋ ለቅቃ መውጣቷን ቅዳሜ’ለት አስታውቃለች። ፑንትላንድ፣ ኹሉም የሚስማማበት የፌደራል ሕገመንግሥት በሕዝበ ውሳኔ እስኪጸድቅ ድረስ፣ ራሴን የቻልኩ ሉዓላዊ አገር ኾኛለሁ በማለት ነው ያወጀችው። ፑንትላንድ ከዓለማቀፍ ድርጅቶችም ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደምትጀምር ገልጣለች።
ፑንትላንድ ራስ ገዝ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው፣ የሱማሊያ ፓርላማ አወዛጋቢ ከኾነው የሕገመንግሥት ማሻሻያ ከፊሎቹን ማሻሻያዎች ማጽደቁን ተከትሎ ነው። የሕገ መንግሥት ማሻሻያው፣ አገሪቱ በፓርላሜንታዊ የመንግሥት አወቃቀር ፋንታ ፕሬዝዳንታዊ የመንግሥት አወቃቀር እንድትከተል፣ የጠቅላይ ሚንስትርነት ሥልጣን እንዲቀር እና የጎሳ ውክልናን መሠረት ባደረገው የምርጫ ሥርዓት ፋንታ የአንድ ሰው አንድ ድምጽ ቀጥተኛ የምርጫ ሥርዓት እንዲኖር የሚደነግግና ሌሎች ማሻሻያዎችን ያካተተ ነው። ፑንትላንድ ከፌደሬሽኑ መውጣቷን ብታውጅም፣ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሃመድ ግን ፓርላማው ያጸደቃቸውን ከፊል ማሻሻያዎች ትናንት በፊርማቸው አጽድቀው የአገሪቱ ሕግ አድርገዋቸዋል።
ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሃመድ ሥልጣን ከያዙ ጀምሮ፣ ላለፉት 12 ዓመታት ሲንከባለል የቆየው የአገሪቱ ጊዜያዊ ሕገመንግሥት አንዳንድ ማሻሻያዎች እንዲደረጉበት የፌደሬሽኑን አባል መንግሥታት ሲያግባቡ ቆይተው ነበር። በዚህ ጥረታቸው ከፑንትላንድ በስተቀር የሁሉንም ፌደራል ግዛቶች ይሁንታ ማግኘት ችለዋል። በተቃውሞው ጎራ በኩል ደሞ፣ ፑንትላንድ ብቻ ሳትሆን የቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዝዳንቶችም ሕገመንግሥታዊ ማሻሻያውን በጥብቅ ይቃወሙታል።
የሕገመንግስታዊ ማሻሻያው የተቃውሞ መነሻ፣ ማሻሻያው ጊዜያዊውን ሕገመንግሥት ከሥረ መሠረቱ የሚቀይር፣ ሥልጣን በፕሬዝዳንቱ እጅ እንዲከማች የሚያደርግና ለአምባገነንነት በር የሚከፍት እና በቂ ውይይትና መግባባት ያልተደረሰበት ነው የሚል ነው። ተቃዋሚዎቹ፣ ሕገመንግሥታዊ ማሻሻያው የፕሬዝዳንቱ የግል ፍላጎት እንጂ የሕዝቡ ፍላጎት ነጸብራቅ አይደለም የሚል አቋምም አላቸው።
ፑንትላንድ ራሷ ከምርጫ ጋር የተያያዘ ውጥረት ሰፍኖባት ነው የከረመችው። የአኹኑ የራስ ገዟ ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ደኒ ለኹለተኛ ዙር ባለፈው ጥር የተመረጡት፣ ደም ካፋሰሰ ግጭትና የፖለቲካ ቀውስ በኋላ ነበር። ፕሬዝዳንቱ ፑንትላንድ በሱማሊያ ታሪክ በጎሳ ላይ የተመሠረተውን የምርጫ ሥርዓት በመተው፣ ከ1969 ወዲህ በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀጥተኛ ያልኾነ ምርጫ በራስ ገዟ እንዲካሄድ ማሻሻያ አድርገው ነበር። ሆኖም ተቃዋሚዎቻቸው ነባሩ ጎሳን ማዕከል ያደረገው ቀጥተኛ ያልኾነ ምርጫ እንዲቀጥል በመፈለጋቸው፣ በመንግሥት ወታደሮች እና በተቃዋሚ ሚሊሻዎች እንዲሁም ጎራ በለዩ ጸጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት በርካቶች ተገድለዋል። ቀጥተኛ ምርጫ ቢካሄድ፣ የራስ ገዟ የመንግሥት አወቃቀር ከፓርላሜንታዊ የመንግሥት አወቃቀር ወደ ፕሬዝዳንታዊ አዋቃቀር ይቀየር ነበር። ፕሬዝዳንቱም በቀውስ ሳቢያ ሃሳባቸውን ቀይረው፣ ቀጥተኛ ባልሆነ የምርጫ ሥርዓት ተወዳድረው ድጋሚ ለማሸነፍ ችለዋል። ፑንትላንድ ያም ሆኖ የአካባቢ ምርጫዋን፣ በቀጥተኛ ምርጫ በማካሄድ የመጀመሪያዋ ፌደራል ግዛት ሆናለች።
ፑንትላንድ የሱማሊያን ፌደሬሽን መሠረት የጣለች ብትሆንም፣ ለበርካታ ዓመታት ከፌደራሉ መንግሥት ጋር ተደጋጋሚ ቅራኔ ውስጥ ስትገባ ነው የቆየችው። ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ግንኙነቷን ስታቋርጥና ለፌደራል መንግሥቱ እውቅና ስትነፍግም የአሁኑ የመጀመሪያዋ አይደለም። ከዓመት በፊትም፣ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በፈጠረችው ቅራኔ ሳቢያ ተመሳሳይ ውሳኔ ላይ ደርሳ ነበር።
ባለፈው ዓመት መጋቢት፣ ፌደራል መንግሥቱና የፌደራል ግዛቶች የአገሪቱን ተቋማት በማጠናከር፣ የጸጥታ መዋቅር ማሻሻያ በማድረግ እና ፋይናንስ ነክ ሥልጣኖች ያልተማከሉ እንዲሆኑ በማድረግ አስፈላጊነት ላይ ስምምነት ላይ ሲደርሱ፣ የፑንትላንድ ራስ ገዝ ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ደኒ ግን የስምምነቱ አካል አልነበሩም። ይህም ውጥረቱን አባብሶት ቆይቷል። አኹን በጸደቀው የአገሪቱ ሕገመንግሥት የማሻሻል ሂደትም፣ ፑንትላንድ ከጥንስሱ ጀምሮ በእምቢተኝነት አልተሳተፈችበትም። ሆኖም ፕሬዝዳንት ሞሃመድ በቅርቡ በተካሄደው የፕሬዝዳንት ደኒ በዓለ ሲመት ላይ መገኘታቸው፣ ውጥረቱን ያለዘበው መስሎ ነበር።
ፕሬዝዳንት ደኒ፣ ከኹለት ዓመት በፊት በተካሄደው የሱማሊያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተወዳድረው ነበር። በመጨረሻው ዙር ግን፣ ከአሁኑ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሃመድ ይልቅ የቀድሞው ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ፎርማጆ በድጋሚ እንዲመረጡ ድግፍ ሰጥተው እንደነበር ይታወሳል።
ፑንትላንድ የሱማሊያ ፌደራል አወቃቀር መሠረት ከመኾኗም በላይ፣ የነዳጅ ዘይት ክምችት ያላት ራስ ገዝ ናት። የጸጥታ ኃይሏም ከሌሎች ግዛቶች በተሻለ ጠንካራ ሊባል የሚችል ነው። ፑንትላንድ ከተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች ጋር የጸጥታ ትብብር ያላት ሲኾን፣ ቦሳሶ ወደብንም የምታስተዳድረው ኢምሬቶች ናት።
ራስ ግዟ አኹን ከፌደሬሽኑ ወጥቻለሁ ማለቷ፣ የውጭ ኃይሎች ይበልጥ በሱማሊያ የውስጥ ፖለቲካ ጣልቃ እንዲገቡ በር ሊከፍት ይችላል። የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሃመድ፣ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የደረሰችበትን የባህር በር ስምምነት አገራዊ አንድነት ለመፍጠር ሙከራ በሚያደርጉበት ወቅት ፑንትላንድ ከፌደሬሽኑ ወጣሁ ማለቷ፣ ትልቅ ራስ ምታት እንደሚሆንባቸው እሙን ነው። ፑንትላንድ ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ግንኙነት ያላት ራስ ገዝ እንደሆነች ይታወቃል። ኢትዮጵያ የግዛት አንድነቴንና ሉዓላዊነቴን ጣስች ብላ ለከሰሰችው ሱማሊያ፣ አኹን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ፈተናው ከውስጥ ነው የመጣባት።
ፑንትላንድ ይህን ውሳኔዋን ያሳወቀችው አልሸባብ እንደገና በሱማሊያ ጦር ላይ መልሶ ማጥቃት በጀመረበት ወቅት መኾኑም፣ ሌላው ችግር ነው። ፌደራል መንግሥቱ ደሞ ከአልሸባብ ጋር ለሚያደርገው ውጊያ፣ የፑንትላንድ ድጋፍ ወሳኝ ነው።
ሌላው ጉዳይ፣ ይህ ቀውስ የተፈጠረው፣ ከሶማሊላንድ ጋር ተዋግተው በቅርቡ ተገንጥለናል ያሉት የሱል አውራጃና አካባቢው ራሱን የቻለ ፌደራል ግዛት ለማቋቋም እየተንቀሳቀሱ ባሉበት ወቅት ላይ ነው። የፑንትላንድ ውሳኔ፣ እነዚሁ አውራጃዎች በጎሳ ከምትዛመዳቸው ፑንትላንድ ጋር አንቀላቀልም በሚለው አቋማቸው ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥር ይችላል። ምክንያቱም፣ ይሄ አካባቢ ፑንትላንድ የይገባኛል ጥያቄ ስታነሳበት የቆየችበትና ከሶማሊላንድ ጋር ስትወዛገብበት የቆየች አካባቢ ነው። በእነዚህ አውራጃዎች ገናና የሆነው ዱልባሃንቴ ጎሳ ፑንትላንድ ውስጥም፣ ቁልፍ ሥልጣኖች ያሉት ነው። ሞቃዲሾ ደሞ፣ ለእነዚህ አውራጃዎች የጊዜያዊ አስተዳደርነት እውቅና ሰጥታለች። [ዋዜማ]