ዋዜማ- በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ እየተካሄደ ባለው ቤቶችን የማፍረስና በግዳጅ የማስነሳት ሂደት የጸጥታ አካላት ተመጣጣኝ ያልሆነ የሃይል እርምጃ መውሰዳቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ቤቶቻቸው የፈረሱባቸውን ሰዎች በግልና በቡድን ለኮሚሽኑ ያቀረቡትን አቤቱታ ተከትሎ ከየካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ክትትልና ምርመራ ሲያደርግ ቆይቶ አርብ መጋቢት 22 ቀን 2015 ዓ. ም አመሻሹ ላይ ሪፖርት አውጥቷል፡፡
በአንዳንድ ቦታዎች ቤት የማፍረስና በግዳጅ የማስነሳቱ ሂደት ለሁከት፣ እንግልት፣ ለአካልና ሥነ ልቦና ጉዳትና ለእስር ምክንያት መሆኑኑን፤ ቤታቸው እንዳይፈርስባቸው የተቃወሙ፣ መንገድ የዘጉ፣ ጩኸት ያሰሙ ሰዎች በጸጥታ አስከባሪዎች ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል እርምጃ መደብደባቸውን ተረድቻለሁ ሲል ኢሰመኮ አስታውቋል፡፡
በተመሳሳይ የተወሰነ መጠን የአካል ጉዳት መድረሱን፣ በቤተሰብና ሕፃናት ልጆች ላይ የሥነ ልቦና ጉዳት መድረሱን እንዲሁም የተወሰኑ ሰዎች ደግሞ ለተለያየ የጊዜ መጠን እስር መዳረጋቸውን በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
ሪፖርቱ እንደሚመላክተው ፊሊዶሮ በተባለ ቦታ ላይ በተደረገው የቤት ፈረሳ የሰው ሕይወት ማለፉን መረጃ እንደደረሰውና ኮሚሽኑ ይህንን እያጣራ ስለመሆኑ እንዲሁም በከተማ አስተዳደሩ በጊዜያዊነት የታሰሩ ሰዎች እንዳሉ ለማወቅ ችያለሁ ብሏል፡፡
በተፈጠረው ክስተት ተማሪዎች ከትምህርታቸው ለማቋረጥ ተገደዋል፤ በርካታ ቤተሰቦች የእለት ተእለት ተግባራቸውን ማከናወን የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤ በርካቶች ተፈናቅለው ወደ ሌሎች ቦታዎች ለመሄድ ተገደዋል፤ከፊሎቹ መንገድ ላይ ወድቀዋል በተለያዩ የሀገር ውስጥ መጠለያ ጣቢያ በመሰብሰብ የመንግሥት እርዳታ ለመጠባበቅ መገደዳቸውን በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የኦሮሚያ ክልል ውስጥ በቅርቡ በአዲስ መልክ በተደራጀው የሸገር ከተማ አስተዳደር የቤቶች ፈረሳ እና በግዳጅ ማስነሳት የመኖሪያ ቤት አልባነትን ማባባሱን የገለጸው አሲመኮ ቤቶች እየፈረሱት ያሉት በቡራዩ፣ ሰበታ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ፣ መነ አብቹ እና በዙሪያው የሚገኙ አካባቢዎች ናቸው ብሏል፡፡
የነዋሪዎችን ቅሬታ ተከትሎ የሚመለከታቸውን የከተማ አስተዳደርና የጸጥታ አካላት በማነጋገር፤ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ቤቶችን የማፍረስና በግዳጅ የማስነሳት ሂደቱ የሚከናወንበትን ሁኔታ እንዲሁም ቀደም ሲል የፈረሱ ቤቶችን የመስክ ምልከታ በማድረግ መረጃና ማስረጃ ማሰባሰቡን አስታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ ኮሚሽኑ አሰባሰብኩት ባለው መረጃ እርምጃው ተገቢ ልየታ ያልተደረገበት መሆኑን፤ እርምጃው ያለ በቂ የቅድመ ማስጠንቀቂያ የተከናወነ ስለመሆኑ፣አድሎአዊ እርምጃ ስለመኖሩ፣እስር፣ የአካልና ሥነ-ልቦና ጉዳት እና እንግልት ስለመድረሱ አደረኩት ባለው ጥናት አመላክቷል፡፡
ኢሰመኮ በለገጣፎ ለገዳዲ፣ በሰበታ አካባቢ ፉሪና ለቡ ተክለሃይማኖት እንዲሁም በቡራዩ ገፈርሳ ኖኖ በተሰኙ አካባቢዎች በመዘዋወር ቀደም ሲል የፈረሱና የማፍረስ ተግባሩ እየተከናወነ የነበረባቸውን አካባቢዎች ተመልክቶ በምልከታው የቤት ማፍረሱና በግዳጅ ማስነሳቱ በግብረ ኃይል እየተከናወነ እንደነበረ እና በቦታው ከፖሊስ፣ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ አባላት በተጨማሪ ሌሎች ዱላ የያዙ ሲቪል ሰዎች እንደነበሩም ተመልክቻለሁ ብሏል፡፡
የቤት ፈረሳውና በግዳጅ ማንሳቱ የሚመለከተው የከተማውን መሪ ዕቅድ በሚጥሱ እና የመንግሥት ይዞታን በመውረርና ከአርሶ አደሩ ጋር በተደረገ ሕገ ወጥ የመሬት ግብይት የተገኙ ይዞታዎች ላይ የተደረጉ ግንባታዎችን ነው ቢባልም ሁሉም ቤቶች በተመሳሳይ ሥሪት ላይ የተመሠረቱ ባለመሆናቸው የሚገዛቸውም ሕጎች እና አሠራሮች በዚያው ልክ የተለያዩ ሊሆኑ ይገባ እንደነበር በመገለጫው አስታውቋልል፡
ከ2005 ዓ.ም. በፊት የተገነቡ ቤቶች ቤቶች በተመለከተ በሀገሪቱ የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ በወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 ላይ እንደተብራራው አዋጁ ከመውጣቱ በፊት በ-ኢመደበኛ መልኩ የተገነቡ ቤቶች የከተሞችን ፕላን እና የሽንሻኖ ስታንዳርድ ሲያሟሉ ወደ መደበኛ ሥሪት እንደሚዞሩ ቢደነግግም እነዚህን ቤቶች ሕጉ በደነገገው መሠረት በወቅቱ ወደ መደበኛ ሥሪት እንዲዘዋወሩ የሚያስችላቸውን መስፈርቶች ያሟሉ ቢሆንም የማዘዋወር ሥራ ሳይሠራ እንዲሁ እንዲፈርሱ መደረጋቸውን ኮሚሽኑ ተረድቻለሁ ብሏል፡፡
በግዢ የተገኙ ቤቶችና መደበኛ ካርታ፣ የአየር ላይ ካርታ እና አረንጓዴ ደብተር ያላቸው እንዲሁም እንዳይፈርሱ የፍርድ ቤት እግድ ያለባቸው ቤቶች ከከተማ ፕላን ጋር የማይሄዱ ቤቶች በሕግ አግባብ በተደነገገው መሠረት ተለዋጭ የቤት መሥሪያ ቦታ እና ተገቢው ካሳ ተከፍሏቸው መነሳት የሚገባቸው እንደነበር ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
ቤቶቹ በገጠር መሬት ላይ የተሠሩ ናቸው የሚባል ከሆነ ደግሞ በኦሮሚያ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 130/1999 አንቀጽ 6(8) መሠረት በቂ ጊዜ ተሰጥቶ ንብረቶቻቸውን እንዲያነሱ ይደረጋል እንጂ በድንገት መፍረስ እንደሌለባቸው አክሎ ገልጿል፡፡
ይሁን እንጂ በማናቸውም ዓይነት ይዞታና ሁሉም ዓይነት ቤቶች በመደበኛም ሆነ በኢመደበኛ መንገድ በተያዙ መሬቶች ላይ የተሠሩ ቤቶች የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ የመኖሪያ ቤት እንዲፈርስ መደረጉ አግባብ አለመሆኑን ኢሰመኮ አክሎ ገልጿል፡፡
ይህም ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሣ የሚከፈልበት እና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1161/2011 አንቀጽ 8(8) እና የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ በወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 አንቀጽ 26(4) ላይ በግልጽ ስለመደንገጉ በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
ኮሚሽኑ የከተማው አስተዳደር ቤቶቹን ከማፍረሱ በፊት በቂ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ አለመስጠቱንና በርካታ ሰዎች ቤታቸው እንደሚፈርስ አስቀድሞ ያልተነገራቸው መሆኑንና አፍራሽ ግብረ ኃይሉ በድንገት መጥቶ እንዳፈረሰባቸው ተረድቻለሁ ብሏል ፡፡
በተጨማሪም ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው ሰዎች አድሎው ብሔር ተኮር እንደሆነ እምነት እንዳለቸው የገለጸ ሲሆን በዚህ የማፍረስና በግዳጅ ማንሳት እርምጃ ለተጎዱ ሰዎች በሕጋዊ መንገድ የመኖሪያ ቤት ሊያገኙ የሚችሉበት መንገድና ለደረሰባቸው የንብረት ውድመት ሊካሱ የሚችሉበት መንገድ በአፋጣኝ ሊመቻች እንደሚገባ አሳስቧል፡፡ [ዋዜማ]