ዋዜማ- መንግስት እስከ 250 ሺህ የሚደርሱ ተዋጊዎችን ትጥቅ በማስፈታት የመልሶ ማቋቋም ስራ ለመጀመር ከለጋሾች ድጋፍ እየጠየቀ ነው። ከሰሜኑ ጦርነት ተዋጊ ኀይሎች በተጨማሪ “የኦነግ ሸኔ” ታጣቂዎችን በመልሶ ማቋቋሙ ለማካተት ታቅዷል።
የብሄራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትና ሌሎች አካባቢዎች ካሉ ግጭቶች ጋር በተገናኘ ለመልሶ ማቋቋም የሚያስፈልገውን 29.7 ቢሊዮን ብር (555 ሚሊየን ዶላር) እገዛ እንዲያደርጉለት መቀመጫቸውን በአዲስ አባባ ላደረጉ ዲፕሎማቶች ጥሪ አቅርቧል፡፡
ኮሚሽኑ በቀጣይ ሁለት አመታት ሊያከናውነው ላቀደው ትጥቅ የማስፈታት የመበተንና ወደ ሰላማዊ ህይወት የመቀላቀል ስራ ከዲፕሎማቶች ጋር ምክክር ማድረጉን ዋዜማ መረዳት ችላለች።
በውይይቱ ላይ ለፕሮግራሙ የሚያስፈልገው አጠቃላይ ወጭና ዝርዝር ስራዎችን የያዘ ረቀቅ ሰነድ ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበትም ተረድተናል፡፡
ዋዜማ የተመለከተችው ሰነድ እንደሚያመላክተው በተሃድሶ ፕሮግራሙ ከሰባት ክልሎች (ከኦሮሚያ፣ አማራ፤ አፋር. ትግራይ፤ ቤንሻንጉል፣ ከደቡብ ብሄር በሄረሰቦችና ከጋምቤላ) የተገኙ ተዋጊዎችንና የአካል ጉዳተኞችን ለማካተት ዕቅድ ተይዟል።
ይሁን እንጂ በመጀመሪያ ዙር ተሃድሶ ፕሮግራሙ የሚካተቱት በትግራይ፤ በአማራ እና በአፋር ክልሎች የሚገኙ ተዋጊዎች ናቸው፡፡
ለፕሮግራሙ ከሚያስፈልገው አጠቃላይ ገንዝብ ውስጥ ከ 20 እስከ 25 በመቶ የሚሆነውን በፌደራል መንግስት ለመሸፈን የታቀደ ሲሆን ቀረውን ደግሞ በለጋሽ ድርጅቶች እርዳታና ከፊል ብድር ለመሸፈን እነደታሰበ ሰነዱ ያብራራል፡፡
በዚህ የተሃድሶ ፕሮግራም እያንዳንዱ የቀድሞ ተዋጊ ከጦርነቱ በፊት እንደነበረው ሃብት፣ በስሩ እንደሚተዳደሩት የቤተሰብ ብዛት እና የጤና ሁኔታ እየታየ ለእያንዳንዱ ታጣቂ ከ 36 ሽህ እስከ 60 ሽህ ብር የመቋቋሚያ ገንዝብ ድጋፍ ይደረግለታል ይላል ሰነዱ፡፡
በተመሳሳይ የአካል ጉዳት ለደረሰበት ተዋጊ ደግሞ ለእያንዳንዱ 45ሽህ ብር የመቋቋሚያ ገንዘብ እንዲሁም በአጠቃላይ ትጥቃቸውን የሚፈቱ ኃይሎች ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ ለእያንዳንዳቸው 50ሽህ ብር እንደሚሰጣቻው ሰነዱ ያስረዳል።
ኦነግ ሽኔ ይካተታል ?
በዚህ ውይይት ላይ የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽነሩ አምባሳደር ተሾመ ቶጋና ሌሎች የመንግስት አካላት ለዲፕሎማቶቹ ስለጉዳዩ ሲያብራሩ በመንግስት ‹‹የኦነግ ሸኔ›› ተብለው የሚጠሩትና በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱት ታጣቂዎችም እንደሚካተቱበት መነሳቱን ዋዜማ ከተሳታፊዎች ስምታለች፡፡
ይሁን እንጅ በርካታ ዲፕሎማች ‹‹ኦነግ ሸኔ›› ከተሰኘው ታጣቂ ቡደን ጋር ስምምነት ባልተደረገበት ሁኔታ ላይ ታጣቂዎች በዚህ ፕሮግራም ይሳተፋሉ ብሎ መቅረቡ መንግሰት ከየትኛው ስምምነት ተነስቶ ነው የሚል ጥያቄ ማንሳታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም የመንግስታቸውን የግማሽ አመት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖረት በተመለከተ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ቀርበው ከአባለቱ ለተነሳላቸው ጥያቄ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረው ነበር፡፡
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ግን ከኢትዮጵያ መንግሥት የቀረበልኝ የሰላም ንግግር ጥሪ የለም በማለት ትናንት አስተባብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላም ጥረት አደረኩ የሚለው፣ የቡድኑን አመራሮችና አባላት የትጥቅ ትግላቸውን ትተው ለመንግሥት እጃቸውን እንዲሰጡ በአካባቢ ሽማግሌዎች አማካኝነት ያደረገውን ያልተሳካ ሙከራ ነው በማለት ቡድኑ ገልጧል።
ቡድኑ፣ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በዚህ ሳምንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ላይ፣ ግጭቱን ለመፍታት 10 ያህል ሙከራዎች ተደርገዋል በማለት የተናገሩት ንግግር ተጨባጭ ሁኔታውን በትክክል አይገልጽም ብሏል። ሆኖም ቡድኑ አሁንም በገለልተኛ ሦስተኛ አካል ለሚደረግ ድርድር ዝግጁ መሆኗን በድጋሚ ገልጧል።
የተሃድሶ ፕሮግራሙን አጠቃላይ ሁኔታ በሚያስረዳው ሰነድ በትግራይ ክልል ከባድ መሳሪያዎችን የመሰብሰብ ሂደቱ መጠናቀቁን እና የቀላል የጦር መሳሪዎችን የመሰብሰብ ሂደት ደግሞ በቅርቡ እንደሚጀመር ተመላክቷል፡፡
የቀድሞ ታጣቂዎችን በፌደራልና የክልል የጸጥታ መዋቅር ውስጥ እንዲካተቱ ማድረግ፣ ከግሉ ዘርፍ ቀጣሪዎች ጋር የማግባባት ስራ በማከናወን ቅጥር እንዲያገኙ ማድረግ፣ በቴክኒክና ሙያ ትምህርት እንዲሳተፉ፤ በጥቃቅን እና አንስተኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲገቡ እገዛ እንደሚደረግ፤ በሰነዱ ተካቷል፡፡
ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ሁለት የተሃድሶ ፕሮግራሞችን እንዳከናወነች የሚያመላክተው ሰነዱ፤ የመጀመሪያው ኢህአዴግ ስልጣን በተቆጣጠረበት ወቅት በ1983 ዓ.ም ከለጋሾች በተገኘ በ193 ሚሊዮን ዶላር ግማሽ ሚሊየንየሚደርሱ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ታጣቂዎችና የደርግ ወታደሮችን የመልሶ ማቋቋም ስራ መከናወኑን ሰነዱ ይናገራል።
በተመሳሳይ ለሁለተኛ ጊዜ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካካል የተካሄደውን ጦርነት መጠናቀቅን ተከትሎ 148 ሺህ የኢትዮጵያን ወታደሮችን በ174 ሚሊዮን ዶላር መልሶ የማቋቋም ስራ መሰራቱንም ያመላክታል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ትጥቃቸውን የሚፈቱ ኃይሎች ወደ ማህበረሰቡ በዘላቂነት እንዲቀላቀሉ እና ሰላማዊ ኑሮ መምራት እንዲችሉ የሚያደርግ ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን መቋቋሙን ያስታወቀው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ህዳር 3፣ 2015 ዓ.ም ባካሄደው 15 መደበኛ ስብሰባ ነበር፡፡ [ዋዜማ]