- አጠቃላይ በሀገሪቱ በጦርነቱ የደረሰው ውድመት 1 ነጥብ 5 ትሪሊየን ብር ወይም 28 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ይገመታል
ዋዜማ- የአማራ ክልል በሰሜኑ ጦርነት በመሰረተ ልማትና በዜጎች ላይ ከደረሰው ውድመት ለማገገምና መልሶ ለመገንባት በድምሩ 475 ቢሊየን ብር ያህል እንደሚያስፈልገው ለዋዜማ ተናግሯል።
በአማራ ክልል በጦርነት የተጎዱ አከባቢዎች መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፈንድ ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አባተ ጌታሁን (ዶ/ር) ለዋዜማ እንደገለፁት ጦርነቱ ያደረሰው ውድመት በገንዘብ ሲሰላ 292 ቢሊየን ብር ደርሷል። የገንዘብ መጠኑ በመሰረተ ልማት ላይ ብቻ የደረሰውን ውድመት የሚመለከት ሲሆን በክልሉ ያሉ በግጭት ሳቢያ የተፈናቀሉ ዜጎችን 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎችን ለማቋቋም የሚያስፈልገው ገንዘብ ጨምሮ ማህበረሰቡን ወደነበረበት ለመመለስ 475 ቢሊየን ብር መሆኑን አባተ ጌታሁን ነግረውናል።
በሰሜኑ ጦርነት 12 ሚሊየን ያህል የክልሉ ህዝብ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ጉዳት እንደደረሰበት የሚያስረዱት ስራ አስኪያጁ አንድ ሺህ ሰባ አምስት የክልሉ ቀበሌዎች በቀጥታ በጦርነቱ ጉዳይ የደርሰባቸው ናቸው ብለዋል።
የመልሶ ግንባታ ስራው በቅርቡ ጦርነቱ የከፋ ጉዳት ባስከተለባት በሰሜን ወሎ ወርቄ በምትባል ቦታ ላይ ይፋ መደረጉን ያስታወሱት አባተ የመልሶ ግንባታውን በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ የማጠናቀቅ ዕቅድ መያዙንም አስረድተዋል።
በትምህርት ፣ በጤና፣ በግብርና፣በሴቶች ፣ በወጣቶች፣በስራ ክህሎት ዘርፎች ላይ ሰራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ለዋዜማ ተናግረዋል ።
የክልሉ መንግስት እስካሁን አንድ ቢሊየን ብር መድቦ ችግሩ የባሰባቸውን 22 ትምህርት ቤቶችና 11 የጤና ማዕከላት እያስገነባ ነው።
የፌደራሉ ትምሕርት ሚኒስቴርም 45 ትምህርት ቤቶች በመገንባት ላይ መሆኑንም ስራ አስኪያጁ ያስረዳሉ።
የዓለም ባንክ የመደበው 300 ሚሊየን ዶላር በጦርነቱና በሌሎች ግጭቶች ጉዳት ለደረሰባቸው ለአማራ ፣ ኦሮሚያ፣ አፋር፣ ትግራይ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችና ለኮንሶ አካባቢ እንደሚከፋፈል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። የየክልሎቹ ተወካዮች ባለፈው ሳምንት አዳማ ላይ የተገኘው ድጋፍ በሚከፋፈልበት ቀመር ላይ ውይይት አድርገዋል።
የአማራ ክልል አሁንም ቢያንስ በየቀኑ አንድ ሺህ ያህል ተፈናቃዮችን ከኦሮሚያ እየተቀበለ መሆኑንና የሰብዓዊ ቀውሱ የማያቋርጥ በመሆኑ ክልሉ በተረጋጋ መልኩ የተቸገሩትን መደገፍ አዳጋች እንደሆነበት ሀላፊው ያብረራሉ።
የክልሉ ማህበረሰብ ፣ ለጋሾችና መንግስት በጋራ ድጋፍ ካላደረጉ የመልሶ ማቋቋሙ ስራ የተሳካ ሊሆን አይችለም ያሉት አባተ ጌታሁን ሁሉም ወገን ርብርብ እንዲያደርግ አሳስበዋል። [ዋዜማ]