Photo credit Save the Children

ዋዜማ- ጦርነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ከኢኮኖሚ ቀውስ ጋር ተዳምሮ በኢትዮጵያ 22 ሚሊየን ዜጎችን የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ፈላጊ እንዳደረጋቸው የመንግስታቱ ድርጅትና ሌሎች የረድዔት ድርጅቶች ይፋ ያደረጉት የተማፅኖ መግለጫ ያመለክታል።

የመንግስታቱ ድርጅት የስብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ እና ዓለማቀፉ የህፃናት አድን ድርጅት (ሴቭ ዘ ችልድረን) ባቀረቧቸው ተማፅኖዎች ላለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ዝናብ ባለመጣሉ ሚሊየኖች የምግብና ሌሎች ዕርዳታዎችን ይፈልጋሉ።

በደቡብ፣ በደቡብ ምስራቅ፣ በምዕራብና ሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በድምሩ 22 ሚሊየን የሚገመቱ ዜጎች ድጋፍ ፈላጊ ናቸው። ከነዚህ መካከል ግማሽ ያህሉ (11.6 ሚሊየን) ገደማ የሚሆኑት ፅኑ የጠኔ አደጋ የገጠማቸውና አጅግ አስቸኳይ ድጋፍ የሚፈልጉ ናቸው።

ለነዚህ ወገኖች ዕርዳታ ለማቅረብ 3 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ያህል የሚያስፈልግ ሲሆን እስካሁን ከለጋሾች የተገኘው አርባ ሰባት ከመቶ ያህሉ ብቻ ነው።

የህፃናት አድን ድርጅት ባወጣው መግለጫ ደግሞ የረሀብ አደጋ ካንጃበበባቸው መካከል 3 ነጥብ 9 ሚሊየኑ ህፃናት መሆናቸውን አስታውቋል።


የድርጅቱ የኢትዮጵያ ቢሮ ቃል አቀባይ ሕይወት እምሻው ለዋዜማ ዜና መፅሄት እንዳስረዱት አስቀድሞ አራት ሚሊየን የሚገመቱ እንሰሳት በድርቁ ምክንያት በመሞታቸው ለህፃናት መኖርና ዕድገት አስፈላጊ የሆነው ወተትና የወተት ተዋፃኦን ማግኘት አይችሉም።


በድርቅ ሁልጊዜም ህፃናት ቀዳሚ ሰለባ ስለሚሆኑ ድርጅታቸው ከመንግስትና ሌሎች የረድዔት ድርጅቶች ጋር በመሆን የተቸለውን የነፍስ አድን ስራ እያከናወነ ነው።


የሰሜኑ ጦርነት ሸፍኖት የቆየው የድርቅ አደጋ ምንም እንኳን ሀገሪቱ ጦርነት ላይ የነበረች ብትሆንም መንግስትና የረድዔት ድርጅቶች ብርቱ ርብርብ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ሕይወት እምሻው አስረድተዋል።

የመንግስታቱ ድርጅትም ሆነ የህፃናት አድን ድርጅቶች እንዳሳሰቡት ቢያንስ በአምስት የዝናብ ወቅቶች ዝናብ ባለመጣሉ የዘንድሮውን የድርቅ አደጋ አስከፊ ያደርገዋል። አደጋውን ለመቋቋም አሁን ያለው አቅም በቂ ባለመሆኑ ተጨማሪ ስብዓዊ ድጋፍ ማፈላለግ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው።


በኦሮሚያ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የሰብዓዊ እርዳታ ማድረስም ሆነ ስለ ችግሩ በቂ መረጃ ማሰባሰብ አስቸጋሪ መሆኑን የረድዔት ድርጅቶቹ ስጋታቸውን ይገልፃሉ።

ድርቁ በአየር ንብረት ለውጥ የተከሰተ ከመሆኑ ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ የግብርና ግብዓት አቅርቦት ለማግኘት ያለው አስቸጋሪነት፣ ሀገሪቱ የገጠማት የተባባሰ የዋጋ ግሽበት እንዲሁም በተለያዩ ግጭቶችና በሰሜኑ ጦርነት የዕለት ገቢያቸውንና ጉርሳቸውን ያጡ በሚሊየን የሚቆጠሩ የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ፈላጊዎች አሉ።

ከረድዔት ድርጅቶቹ በተጨማሪ መንግስት የራሱን በጀት መድቦ ዕርዳታ ለማቅረብ እየሞከረ ቢሆንም ከችግሩ ስፋት አንፃር ድጋፉ አነስተኛ የሚባል ነው።


በጉዳዩ ላይ በዋዜማ መፅሄት የቀረበውን የሕፃናት አድን ድርጅት ቃል አቀባይ ቃለ-ምልልስ የያዘ ዘገባ ከታች ያድምጡት።