ዋዜማ -በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር እየጨመረ የመጣውን የባለቤት አልባ ውሾች ቁጠር ለመቀነስ ሴት ውሾችን እንዳይወልዱ የማምከን ስራ ሊጀምር መሆኑን የከተማው አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
በከተማ አስተዳደሩ ይኖራሉ ተብለው ከሚገመቱ 250ሺህ ውሾች ውስጥ ቁጥራቸው ሰፋ ያሉት ባለቤት አልባ መሆናቸውን ለዋዜማ የገለጹት በኮሚሽኑ የእንስሳት በሽታ መከላከልና ቁጥጠር ቡደን መሪ አቶ ዳኘ በላይሁን ናቸው፡፡
በኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ባለቤት አልባ፣ ያረጁና የታመሙ ውሾችን ለማስወገድ ይጠቀምብት የነበረው አስተሪክኒን የተባለ የውሻ መግደያ መርዝ ውሻውን ከመግደል አልፎ አካባቢን የመመረዝ አቅም ስላለው እንዲሁም የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት አገልግሎት ላይ እንዳይውል በመከለከሉ ምክንያት አሁን ውሾችን ለመግደል ያለው አማራጭ በጥይት ወይንም በዱላ በመደብደብ ብቻ እንደሆነ አቶ ዳኘ ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ አሰራር አስተማማኝ ካለመሆኑም በላይ የውሾችን ቁጠር መቀነስ ባለመቻሉ የማምከን ስራው በአፋጣኝ ካልተጀመረ የባለቤት አልባ ውሾች ቁጠር መጨመር ከፍተኛ ስጋት እየሆነ መምጣቱን አክለው ገልጸዋል፡፡
በእብድ ውሻ በሽታን (ሬቢስ) ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው ደንብ መሰረት የውሻ ባለቤቶች ውሾችን በአመት አንድ ጊዜ ማስከተብና መንከባከብ ግዴታ ሆኖ ቢቀመጥም አተገባበበሩ በሚጠበቀው ልክ ባለመሄዱ ለምግብ ፍለጋ በሚጠፉና ከገጠር ወደ ከተማ በሚሰደዱ ውሾች ምክንያት ቁጠሩ ማሻቀቡን ቡድን መሪው ያብራራሉ።
ገዳይ የሆነው በእብድ ውሻ በሽታ (ሬቢስ) በቀላሉ ወደ ሰዎች የሚተላለፍ ሲሆን በሽታውን ለመፈወስና ህክምና ለመስጠት ውድና አስቸጋሪ መሆኑንንም ባለሙያው ይናገራሉ።
በከተማ አስተዳደሩ በወጣው ድንብ መሰረት የውሻ የባለቤትነት ምዝገባ የወሰዱ ነዋሪዎች ውሾቹን እንዲያስመዘግቡና የበሽታውን የቅድመ መከላከል ክትባት በአመት አንድ ጊዜ እንዲያደርጉ ህጉ ቢያስገድድም እንደ አደጉት አገሮች ለውሻ የሚደረግ እንክብካቤና የአያያዝ ሁኔታ በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ውሾች በቀላሉ ከቀያቸው በመንቀሳቀስ ወደ ጎዳና እንደሚወጡ አስረድተዋል፡፡
አሁን ላይ ባለቤት ላላቸው ውሾች የሚሰጠውን ክትባት ጎዳና ላይ ለሚገኙት ውሾችም በተለየም ውሾቹ በብዛት በሚገኙባቸው የመኪና ማጠቢና ፓርኪንግ፣ የከተማ ጽዳት ሰራተኞች ማረፊያ አካባቢና ጎዳና ላይ የሚተዳደሩ ሰዎችን በማስተባበበር ለመከተብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ቡድን መሪው ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ አሰራር አስተማማኝ ባለመሆኑ እና ውሾች በአመት እሰከ 14 የመውለድ አቅም ስላላቸው ቁጥሩን ለመገደብ ሴት ውሾችን የማምከን ስራ ለመጀመር ስትራቴጂ ተነድፎ በዘርፉ የባለሙያ ስልጠና እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
የባለቤት አልባ ውሾችን የመራባት ፍጥነት በቶሎ ማቆም ካልተቻለ በአዲስ አበባ በነዋሪው ህዝብ ላይ እንዲሁን በሌሎች እንሰሳት ጤና ላይ የከፋ አደጋ ሊያስከትል የሚችል ጠንቅ ይፈጠራል የሚል ስጋት መኖሩንም መስሪያ ቤታቸው ያስጠነቅቃል።
በእብድ ውሻ በሽታ (ሬቢስ) የተለከፉ ሰዎች ከሚወስዷቸው ሁለት ክትባቶች መካከል በሆድ የሚሰጠው የህመም ስሜት ያለው በመሆኑ ተመራጭ አለመሆኑንና ቀላል እና የመፈወስ አቅሙ ከፍተኛ ነው የሚባለውን መድሃኒት በክንድ የሚሰጥ ቢሆንም ዋጋው በጣም ውደ በመሆኑ የተነሳ ብዙውን ጊዜ በአገር ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውለው ለውጭ ዜጎችና በዲፕሎማቲክ ማህበረሱ ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ [ዋዜማ ]