- የሀብት ምዝገባ ቀነ ገደቡ በዚህ ሳምንት አብቅቷል
ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ መንግስት ሙስናንና ምዝበራን ለመከላከል ሁሉም የመንግስት ሰራተኞች ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ያሰቀመጠው ቀነ ገደብ በዚህ ሳምንት ሰኔ15 ቀን 2014 ዓም ተጠናቋል። ይመዘገባሉ ተብለው ከሚጠበቀት 2 ነጥብ 3 ሚሊየን የመንግስት ሰራተኞች ውስጥ በቀነ ገደቡ የተመዘገቡት 72 ሺህ ብቻ መሆናቸውን ዋዜማ ባደረገችው ክትትል ተገንዝባለች።
ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ መንግስት የሐብት ምዝገባ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች ሲያደርግ ቆይቷል።
ባለፈው ዓመትም የመንግስት ባለስልጣናትና በተለያየ ሀላፊነት ላይ ያሉ የመንግስት ሰራተኞችን ሀብት ለመመዘገብ የሚያስችል የድረገፅ ሐብት ማስመዝገቢያ ስርዓት ተዘጋጅቶ ለሁሉም የመንግስት ተቋማት ተሰራጭቶ ነበር።
ይህ አሰራርም በየተቋማቱ በተሰየሙ የስነ-ምግባር መኮንኖች አማካኝነት ይካሄድ የነበረ ሲሆን፤ ኮሚሽኑ እንደወጠነው አብዛኛው የመንግስት ሰራተኞች ሊመዘገቡለት አለመቻላቸውን ያምናል።
ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ ኮሚሽኑ በበይነ መረብ የሀብት ማስመዝገብ ስራውን መቀጠሉን በማሳወቅ እስከ ሰኔ 15፤ 2014 ዓ.ም. ድረስ ሁሉም የመንግስት ሠራተኛ፣ ተሿሚና የህዝብ ተመራጭ ሀብቱን እንዲያሳውቅ ቀነ ገደብ አስቀምጦ ነበር። ።
ይሁን እንጂ ዋዜማ ባገኘችው መረጃ ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ድረስ ማስረጃቸውን በማቅረብ ምዝገባ ያካሄዱ (በተለያየ እርከን ያሉ) የመንግስት ሠራተኞች ቁጥር 72 ሺህ 320 ገደማ ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ ኮሚሽኑ 31 ሺህዎቹን መረጃ የተቀበለ ሲሆን፤ የ41 ሺህ ገደማዎቹ ጉዳይ ደግሞ እየታየ ነው።
የኮሚሽኑ የሀብት ማሳወቅና ምዘገባ ዳይሬክተር መስፍን በላይነህ ለምዝገባው ቀን መቁረጥ ያስፈለገው ቀላል ስርዓት በመዘርጋቱ መሆኑን ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ኮሚሽኑ በአጠቃላይ ሀብት ማሳወቅና ምዝገባው የግንዛቤ ክፍተት እንዳለበት ያምናል። አዲሱን የድረገፅ የምዝገባ ስርዓት አለመላመድ ግን ትልቁ ፈተናው መሆኑን ለዋዜማ ተናግረዋል።
መረጃዎች የግድ መሟላት እንዳለባቸው የሚያነሱት ኃላፊው፤ ለምሳሌ የቤት ካርታ ቁጥር፣ የመኪና ሊብሬ፣ አካውንት ቁጥር የመሰሉ መረጃዎች መጓደል ወይም መዘለል የለባቸውም ብለዋል። መረጃዎቹ ካልተሟሉ ስርዓቱ ወደ ኋላ እንደሚመልስም ተናግረዋል። መረጃዎቹ በየድረገፅ ’ ከተሞሉ በኋላ ስርዓቱ (ኦንላይን) የምስክር ወረቀት እንደሚሰጥም አክለው ተናግረዋል።
በድረ ገፅ የመንግስት ሠራተኞች ሀብታቸውን ሲያስመዘግቡ ኮሚሽኑ ትክክለኛ መረጃ እንደተላከለት በምን ያረጋግጣል ብላ ዋዜማ የጠየቀች ሲሆን፤ ጥርጣሬ ካልቀረበ በቀር ለማረጋገጥተጨማሪ የመቆጣጠሪያና ማረጋገጫ ዘዴ ስርዓት አለመኖሩን አውቃለች።
ከተቋሙ በተገኘ መረጃ ከ2003 ዓ.ም. እስከ 2013 ዓ.ም. ባሉት አስር ዓመታት 840 ሽህ የሚደርሱ የመንግስተ ተሿሚዎች፣ ሠራተኞችና የህዝብ ተመራጮች ብቻ ሀብታቸውን አስመዝግበዋል።
የትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር የሆኑት ሳሙኤል ካሳሁን ምዝገባውን ማስፈፀም ከችግሩ ስፋት አንፃር ከባድ ስራ እንደሆነ ይናገራሉ። ከዚህ ባሻገርም መረጃ ማረጋገጡ የኮሚሽኑ ትልቁ ፈተናው ነው ይላሉ። በተለይም የተመዘገበሩ ሀብቶች በተለያየ ግለሰብ ስም በማስቀመጥ ዱካው እንዳይደረስበት ያደርጋል ሲሉ፤ የማረጋገጥ ስርዓቱ ላይ ስጋታቸውን ያነሳሉ።
በአዲሱ የዲጂታል ስርዓት የመንግስት ተሿሚዎች፣ ሠራተኞችና ተመራጮች ስራ ሲለቁም ያፈሩትን ሀብት እስከ ሁለት ዓመት ድረስ የማሳወቅ ግዴታ አለባቸው። ይህም የገንዘብ ምንጫቸውንና ከስራ በኋላ የሚኖራቸው እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ታሳቢ በማድረግ ነው ተብሏል።
እስከ ሰኔ 15 ሀብታቸውን ባላሰመዘገቡ በማያስመዘገቡ ሠራተኞች ላይ በአዋጅ በተሰጠ ስልጣን ከአስተዳደራዊ እርምጃ ጀምሮ በወንጀል እንደሚጠየቁ ዋዜማ ሰምታለች።
ከወራት በፊት ኮሚሽኑ ሀብታቸውን አላሳወቁኘም ያላቸውን ሚንስትር ዴኤታዎችና ባለስልጣናት የስም ዝርዝር ለፌደራል ፖሊስና ለዐቃቢ ህግ መላኩ የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያ ምንም እንኳ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በወሰደችው የህግ ማሻሻያና ሌሎች እርምጃዎች በሙስና ዓለም አቀፍ ደረጃዋ ተሻሽሏል ብትባልም፤ ሙስና ግን በአገሪቱ ተባብሶ ስለመታየቱ ባለሞያዎች ይናገራሉ። [ዋዜማ ራዲዮ]