PHOTO- ORGANIZERS

ዋዜማ ሬድዮ – ከ56 አገራት በተውጣጡ ተወዳዳሪዎች መካከል ከሰኔ 1 ጀምሮ በኢትዮጵያ ሲካሄድ  የቆየው አለም አቀፍ የቁርአን አቀራር እና አዛን ውድድር ሰኞ ሰኔ 6/2014 በአዲስ አበባ ስታዲየም ተጠናቋል፡፡ 

በእስልምና ታሪክ የመጀመሪያው ሙአዚን በሆነው በሀበሻው ቢላል አገር በኢትዮጵያ በተደረገው በዚህ ውድድር በቁርን ሂፍዝ ወይም ቁርአንን በቃል በማጥናት ሙሀመድ ኑር ከኡርዶን(ዮርዳኖስ) በአንደኝነት በማጠናቀቅ 10 ሺህ የአሜሪካን ዶላር የተሸለመ ሲሆን በአዛን ውድድር ደግሞ ዚያድ ፈሪጃ ከሊባኖስ በአንደኝነነት ማጠናቀቁን አዘጋጆች ለዋዜማ ሬድዮ ገልጸዋል፡፡ 

ውድድሩ ፍጻሜ በአዲስ አበባ ስታዲየም እሁድ ሰኔ 5/2014 ዓ.ም ሊደረግ ፕሮግራም ተይዞለት የነበረ ቢሆንም ከፈቃድ ጋር በተገናኘ ሁኔታ በዕለቱ ባይካሄድም ከመንግስት አካላት በተገኘ ፈቃድ በማግስቱ በሰላም መጠናቀቁን ከአዘጋጀች አንዱ የሆኑት አዱኛው ሙጨ ገልጸውልናል፡፡ 

በአገራችን በኢትዮጵያ ቅዱስ ቁርአን በአማርኛ እንዲተረጎም ትዕዛዝ ያስተላለፉት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ናቸው ። ንጉሱ ሐምሌ 18/1958 ዓ.ም በወቅቱ የትምሕርት ሚስቴር ሚስትር የነበሩት ዶ/ር ምናሴ ሃይሌ የትርጉም ስራውን እንዲያከናውኑ አዘዙ፡፡ 

ዶ/ር ምናሴም የታዋቂው አል-አህዛር ዩኒቨርሲቲ ምሩቅና በማስታወቂያ ሚ/ር ስር በአረቢኛ ቋንቋ የሚታተመው የአል-ዐለም  ጋዜጣ ምክትል አዘጋጅ የነበሩትን ሐጂ በሽር ዳውድን በተርጓሚነት መረጡ። 

ሐጂ በሽር ዳውድም በትርጉም ችሎታቸው የተመሰከረላቸውን ዓሊሞችን በማፈላለግ አለማዊ ትምህርት ከእስላማዊ እውቀት ያጣመሩ የአማርኛ ቋንቋ ሰዋሰው እና ስነ-ልሳን አጣምረው ያወቁትን ሐጂ መሀመድ ሳኒንና ከደሴ ወ/ሮ ስሂን ት/ቤት መምህር እና የሸሪአ ፍ/ቤት ዳኛ የነበሩትን ሼኽ ሰይድ መሀመድን መረጡ። ቀጥሎም የትርጉም ረቂቁን አንብበው የእርማትና ማሻሻያ እንዲሰጡ አምስት ታላላቅ ዑለማዎችን መመረጣውን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ 

የትርጉም ስራውን እንዲመለከቱ የተመረጡት በችሎታቸው የተመሰከረላቸው አምስቱ ኡለማች፡  ሼኽ ቡሽረል ከሪም ሙስጠፋ ከወሎ ፣ ሐጂ ዩሱፍ ዐብዱረሒም ገረድ ከሐረርጌ ፣ ቃዲ መሐመድ ዐብዱረህማን ከትግራይ ፣ ሐጂ አህመድ ዳለቲ ከሸዋ ፣ ሐጂ መንዛረሁ ከቢር ሑሴን ከአርሲ ናቸው፡፡ በመጨረሻም ተርጓሚዎቹ ከዑለማዎቹ አስተያትና ማሻሻያ ሀሳቦች ተቀብለው ረቂቁን አርመው በማዘጋጀት ቅዱስ ቁርአንን በአማርኛ ተርጉመው በ1961 ዓ/ም ለህትመት አበቁ። 

ፍጸሜውን ያገኘው የቁርአን ሂፍዝ (የቃል ንባብ) እና አዛን ውድድር የነቢዩ ዘመዶች እና የመጀመሪያ የእስልምና አማኞችን በመቀበል እንዲሁም የመጀመሪያው ሙአዚን አገር በሆነችው በኢትዮጵያ መደረጉ አገራችንን በአለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ የጎላ ድርሻ እንዳለው አዘጋጆች ገልጸዋል፡፡  [ዋዜማ ሬድዮ]