ዋዜማ ራዲዮ-የፌደራል መንግስት ለ2015 ዓ.ም ለክልሎች ካቀረበው አጠቃላይ የበጀት ድልድል ውስጥ ለትግራይ ክልል 12 ቢሊዮን ብር መድቧል፡፡
ለ2015 በጀት አመት ከቀረበው አጠቃላይ 786 ቢሊዮን ብር ረቂቅ በጀት ውስጥ ለኦሮሚያ ክልል 71 ቢሊዮን ብር፣ለአማራ ክልል 44 ቢሊዮን ብር፣ ለደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች 26.5 ቢሊዮን ብር፣ ለሶማሌ ክልል 20.5 ቢሊዮን ብር፣ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝች ክልል 6.4 ቢሊዮን፣ ለሲዳማ ክልል 8.4 ቢሊዮን ብር በረቂቅ በጀቱ ቀርቧል፡፡
በተመሳሳይ ለአፋር ክልል 6.2 ቢሊዮን ብር፣ ለቤንሻንል ክልል 3.7 ቢሊዮን ብር፣ ለጋምቤላ ህዝቦች ክልል 2.4 ቢሊዮን ብር፣ ለሃረሪ ህዝብ ክልል 1.5 ቢሊዮን ብር፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስታደዳር 3.2 ቢሊዮን ብር፣ ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳዳር 1.8 ቢሊዮን ብር ሆኖ በረቂቁ ተደልድሏል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክከር ቤት ግንቦት 30 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሳበ ከሚንስትሮች ምክርቤት በተመራለት አጠቃላይ የ2015 ረቂቅ በጀት ላይ የተወያየ ሲሆን ከአጠቃላይ በጀቱ ለመደበኛ ወጭዎች 345.1 ቢለዮን ብር ፣ ለካፒታል ወጭ 218 ቢሊዮን ብር፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ 209 ቢሊዮን ብር እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈፀሚያ 14 ቢሊዮን ብር ተመድቧል፡፡
በፌደራል የመደበኛና ካፒታል ወጭ ድልድል ውስጥ ከፍተኛ ድርሻን ከያዙ ወጭዎች መካከል እዳ ክፍያ 125 ቢሊዮን ብር፣ ለአገር መከላከያ 84 ቢሊዮን ብር፣ ለመንገድ 66 ቢሊዮንና ለትምህርት 64 ቢሊዮን ብር የመጀመሪያዎቹን አራት ከፍተኛ ድርሻ ይይዛሉ፡፡
በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት ከፌደራል መንግስተ የአገር ውስጥ ገቢ ምንጮችና ከውጭ ብድር በድምሩ 477 ቢሊዮን ብር ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገንዝብ ሚንስትር አቶ አህመድ የበጀቱን አጠቃላይ ማብራሪያ ለፓርላው ሲያቀርቡ ተናረዋል፡፡
የ2015 ዓ.ም የመንግስት ገቢ የአገር ውስጥ ብድር 266 ቢሊዮን ብር፣ የአገር ውስጥ ገቢ 438 ቢሊዮን ብርና ቀሪው ከፕሮጅክት ብድርና እርዳታ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
አቶ አህመድ ለ2015 ዓ.ም ከቀረበው አጠቃላይ ረቂቅ በጀት ውስጥ 234.4 ቢሊዮን ብር የተጣራ የበጀት ጉደለት እንደሚኖርና ይህ የበጀት ጉድለት ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት የ3.4 በመቶ ድርሻን ይይዛል ብለዋል፡፡
የበጀት ጉድለቱን ለመሸፈን 224 ቢሊዮን ብር ከአገር ውስጥ ብድርና 6.9 ቢሊዮን ብር ከውጭ አገር የተጣራ ብድር በመውሰድ እንደሚሟላ አቶ አህመድ ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጅ የልማት አጋሮች የሚሰጡትን የልማት ድጋፍ በከፍተኛ ደረጃ የቀነሱ መሆናቸውን በተለይም በበጀት ድጋፍ መልክ የሚሰጡትን ድጋፍ ሙሉ ለሙሉ እንደቆመ አክለው አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል መንግስት በመገባደድ ላይ ባለው 2014 በጀት ዓመት ኢኮኖሚው የ8.5 በመቶ ዕድገት እንደሚያስመዘግብ ግብ ይዞ የነበረ ቢሆንም በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው አለመረጋጋት ምክንያት በተለይም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረው ጦርነት ኢኮኖሚው መቀዛቀዝ በማስከተሉ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ቀደም ሲል ከተገመተው በታች ከ 6 እስከ 7 በመቶ ሊወርድ እንደሚችል አቶ አሀመድ ተናግረዋል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]