ዋዜማ ራዲዮ -የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ባለቤትና የሕወሓት ከፍተኛ አመራር የነበሩት ወይዘሮ አዜብ መስፍን ባለፈው ሳምንት ከኢትዮጵያ መውጣታቸውንና ከዚህ በኋላ ኑሯቸውን በውጪ ለማድረግ እንዳቀዱ ዋዜማ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።
ወ/ሮ አዜብ ለረጅም ዓመታት በታጋይነትና በአመራር ደረጃ አባል ከነበሩበት ከሕወሓት ከተባረሩ በኋላ በኢሕአዴግና ሕወሓት ውስጥ የአመራር ብቃ ማነስና ስርዓት አልበኝነት መስፈኑን፣ ሙስና መንሰራፋቱን እንዲሁም ድርጅቱ ለህዝብ የገባውን ቃል ማክበር አለመቻሉን አንስተው በአደባባይ ሲተቹ ነበር።
በተለይም ባለቤታቸው ካረፉ በኋላ በሕወሓት አንዳንድ አመራሮች የተደራጀ የስም ማጥፋትና መገለል እንደደረሰባቸው የሚናገሩት ወይዘሮ አዜብ በተደጋጋሚ የሚቀርብባቸው የሙስና ውንጀላ በማስረጃ አደባባይ እንዲቀርብና ንፅህናቸው እንዲረጋገጥ ፍላጎት እንዳላቸው ሲገልፁ ቆይተዋል።
አሁን መኖሪያቸውን በዩናይትድ ስቴትስ ለማድረግ ያቀዱት ወይዘሮ አዜብ ከፖለቲካ ፓርቲያቸው ከተገለሉ በኋላ ከኢትዮጵያ ሲወጡ ያሁኑ የመጀመሪያቸው ነው። ከሀገር እስከወጡበት ያለፈው ሳምንት ድረስ ደሳለኝ ሆቴል አካባቢ መንግስት በሰጣቸው መኖሪያቤት ይኖሩ ነበር።
በባለቤታችው ስም የጀመሩትን የመለስ ፋውንዴሽን በማቋቋምና በመምራት ያለፉትን አምስት ዓመታት ያሳለፉት ወሮ አዜብ በሀገሪቱ በተፈጠረው የፖለቲካ ለውጥና በኋላም በተቀሰቀሰው የትግራዩ ጦርነት ሳቢያ ፋውንዴሽናቸው በታሰበው መንገድ መጓዝ አልቻለም።
ወሮ አዜብ የሕወሓትን ግዙፍ የንግድ ተቋማት አስራ ሁለት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በበላይነት መርተዋል። ለሴቶች ዕኩልነትና መብት እንዲሁም በኤች አይ ቪ ኤድስ ዙሪያ በሚደረጉ የዘመቻ እንቅስቃሴዎች የጎላ ተሳትፎ ነበራቸው።
ከቀድሞ ባላቤታቸው ጋር በትግል ሜዳ የተገናኙት ወሮ አዜብ የሶስት ልጆች እናት ናቸው። [ዋዜማ ራዲዮ]