- በ196 ሚሊየን ብር የማተሚያ ማሽኖች ተገዝተው ተከፋፍለዋል
ዋዜማ ራዲዮ- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ ዘመናዊውን ዲጂታል የነዋሪነት መታወቂያ የክፍለ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሰሩት ለማስቻል 150 ማተሚያ ማሽኖችን ገዝቶ ለክፍለ ከተሞች ማከፋፈሉን ለዋዜማ ተናግሯል፡፡
በዚህም መሠረት የነዋሪውን ሙሉ ስም፣ የአደጋ ጊዜ ተጠሪው የትውልድ ዘመኑን፣ የመኖሪያ አድራሻውን፣ ዜግነቱን እንዲሁም በአገር ዓቀፍ ደረጃ የግል የነዋሪነት መለያ ቁጥሩን (ባር ኮድ) የሚይዘውን እና የግለሰቡን ፎቶግራፍ የሚያሳየውን የፕላስቲክ ዘመናዊ መታወቂያ ክፍለ ከተሞች አትመው ለተገልገዮች አግለግሎቱን መስጠት ሊጀምሩ እንደሆነ ታውቋል።
በመላ ሀገሪቱ ተጥሎ የቆየው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተነስቶ የመታወቂያ አገልግሎት መሰጠት ሲጀመር፣ የአዲስ አበባ ከተማ ክፍለ ከተሞች በቀጥታ አገልግሎቱን እንዲጀምሩ ይችሉ ዘንድ ኤጀንሲው ስለ መስሪያ ማሽኑ አጠቃቀም ሥልጠና ሰጥቷቸዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ መታወቂያውን ለሚያትሙት 150 ማተሚያ ማሽኖች ግዥ 196 ሚሊዮን ብር ወጪ ያደረገ ሲሆን፣ ግዥውን ለመፈጸም የወጣውን ዓለም ዓቀፍ ጨረታ አሸንፎ ፕሪንተሮቹን ለኤጀንሲው ያቀረበው ከነራ ኋላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት (Kenera PLC) መሆኑን የኤጀንሲው ኮምንኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዮሴፍ ንጉሴ ለዋዜማ ገልጸዋል፡፡
ላለፉት ሁለት ዓመታት ዘመናዊ የሆነውን እና የፕላስቲክ ይዘት ያለውን በላዩ ላይ የግለሰቡን መለያ ቁጥር እንዲሁም መሠረታዊ መረጃዎች የያዘውን የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ለከተማዋ ነዋሪዎች ሲሰጥ የቆየው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጄንሲ ብቻ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ነዋሪዎች ከመኖሪያ ወረዳቸው የክላሰሩን (የወረቀቱን) የነዋሪነት መታወቂያ ለማሳደስ፣ የጠፋ መታወቂያ ለመተካት እና አዲስ መታወቂያ ለማውጣት በትንሹ አንድ ሳምንት ይፈጅባቸው ነበር። ዘመናዊውን ዲጂታል መታወቂያ ለማግኘት ደሞ አንድ ወር ከአስራ አምስት ቀን እንደሚፈጅባቸው ዋዜማ ከተገልጋዮች ማረጋገጥ ችላለች። ይህ የሆነው ዘመናዊውን ዲጂታል መታወቂያ አትሞ የሚያቀርበው እና ለወረዳዎች የሚያከፋፍለው የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ ብቻ ስለነበር ነው፡፡
ኤጀንሲው የነዋሪነት መታወቂያ እደላን ወደ ክፍለ ከተማ ደረጃ ለማውረድ ለ11ዱም ክፍለ ክተማዎች የመታወቂያ አገልግሎት ክፍል ሠራተኞች የአሠራር ሥልጠና ሰጥቶ ማጠናቀቁን እና ማሽኖቹንም ለክፍለ ከተማዎቹ ማስረከቡን ኤጀንሲው ለዋዜማ አረጋግጧል። መንግሥት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማንሳቱ፣ ኤጀንሲው ከአዲስ የነዋሪነት መታወቂያ አገልግሎት ውጭ ለጊዜው አግዷቸው የቆዩ አገልግሎቶችን ከሰኞ የካቲት 14 ጀምሮ እንደገና መስጠት እንደሚጀምር ሰሞኑን ማስታወቁ ይታወሳል። [ዋዜማ ራዲዮ]