Journalists arrested related with AP video reporting assignment – PHOTO Addis Standard

ዋዜማ ራዲዮ- ኅዳር 19፣ 2014 ዓ.ም ፌደራል ፖሊስ ያሰራቸው ሁለት የአሶሴትድ ፕሬስ ጋዜጠኞች ረቡዕ’ለት ለመጀመሪያ ጊዜ በአራዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቀርበው ዘጠኝ ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ተፈቅዶባቸዋል። በዕለቱ ችሎት የቀረቡት ተጠርጣሪ ጋዜጠኞች አሚር አማን እና ቶማስ እንግዳ ናቸው።


ፌደራል ፖሊስ ጋዜጠኞቹን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ከፈረጀው የኦነግ ሸኔ ቡድን ከፍተኛ አመራሮች ጋር በተለይም ጅሬኛ ረቡማ የተባለውን የቡድኑ አመራር እና ሌሎች 30 ያህል የቡድኑን ታጣቂዎች በአካል እና በስልክ በመገናኘት፣ ከሽብር ቡድኑ ተልዕኮ ተቀብለው ሕገመንግሥቱ እና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ በመሞከር ወንጀል እንደሚጠረጥራቸው ለችሎቱ አስረድቷል።


ተጠርጣሪዎቹ የአሶሴትድ ፕሬስ እና የዓለም ዓቀፍ ጋዜጠኝነትን ሽፋን በማድረግ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ቶኬ ኩታዬ ወደተባለ ቦታ በአካል መሄድ የቡድኑን ታጣቂዎች እንቅስቃሴ በተንቀሳቃሽ ምስል እንደቀረጹ እና ለተለያዩ የአውሮፓ አገራት መረጃዎችን በመላክ ሀገራቱ ለኢትዮጵያ የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖራቸው እና የኦኑግ ሸኔን ቡድን እንዲደግፉ በመስራት ላይ እያሉ እንደተያዙ ፖሊስ ለችሎቱ ጨምሮ ገልጧል።


ፖሊስ የተጠርጣሪዎቹን ቃል መቀበሉን፣ ለብሄራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ተጠርጣሪዎቹን በተመለከተ የቴክኒክ ማስረጃ እንዲልክለት እንዲሁም ከተጠርጣሪዎች እጅ የተያዙ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ላይ ምርመራ እንዲደረግለት መጠየቁን፣ የተጠርጣሪዎቹን የባንክ እንቅስቃሴ ለማወቅ ለ18 ባንኮች በደብዳቤ ጥያቄ ማቀረቡን፣ በቀጣይ ለተላኩት ደብዳቤዎች ምላሽ እና የምርመራ ውጤት መቀበል እንደሚቀረው በመግለጽ፣ ፍርድ ቤቱ የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ይፍቀድልኝ ሲል ጠይቆ ነበር።


የተጠርጣሪዎቹ ጋዜጠኞች ጠበቆች በበኩላቸው፣ ደንበኞቻቸው መጀመሪያ የተያዙት ከአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ መሆኑን እና አሁን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጁን እንዳነሳው በመጥቀስ፣ ተጠርጣሪዎቹ እንዲፈቱ ችሎቱን ጠይቀዋል።

ጠበቆች በተጨማሪም፣ ደንበኞቻቸው በእስር እያሉ በመንግሥት ሚዲያ የተሠራባቸው ዘጋቢ ፊልም ፖሊስ ክስ ለመመስረት ዝግጅት መጨረሱን ያመለክት እንደነበር እና ደንበኞቻቸው የታሰሩት ጋዜጠኞች በመሆናቸው እንደሆነ፣ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ማክሰኞ’ለት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ የምርመራ ጋዜጠኝነት መጠናከር እንዳለበት መናገራቸውን በመጥቀስ፣ ችሎቱ ፖሊስ በጋዜጠኞቹ ላይ የጠየቀው የተጨማሪ ምርመራ ቀናት ጥያቄ ውድቅ አድርጎ ተጠርጣሪዎቹን በነጻ እንዲያሰናብት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።


ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ፣ የፖሊስን የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመቀነስ ዘጠኝ ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ብቻ ፈቅዷል።


የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ የሽብር ወንጀሎች ምርመራ ዲቪዥን ሃላፊ ኢንስፔክተር ተስፋዬ ኦላና ታኅሳስ 6፣ 2014 ዓ.ም አሸባሪውን ኦነግ ሸኔ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ የተጠረጠሩ ሦስት ጋዜጠኞች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በመንግሥት መገናኛ ብዙኀን ላይ ተናግረው ነበር።

ኢንስፔክተሩ ጨምረውም፣ ጋዜጠኞቹ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ሚዳ ቀኝ ወረዳ የሚንቀሳቀሰውን የሽብርተኛውን ሸኔ ቡድን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ተከታትሎ በተንቀሳቃሽ ምስል በመቅረጽ እና ለአባላቱ ቃለ መጠይቅ በማድረግ፣ መረጃዎችን ጉረቤት ኬንያ ለሚገኘው የአሶሴትድ ፕሬስ የምሥራቅ አፍሪካ ወኪል ለግብጻዊው ካሊድ ካዚሃ እንደላኩ ተደርሶባቸው በቁጥጥር ስር እንደዋሉ መግለጻቸው ይታወሳል።


ከሁለቱ ተጠርጣሪ ጋዜጠኞች ጋር በተመሳሳይ ወንጀል ተጠርጥሮ አብሮ ታስሮ የቆየው የፋና ብሮድካስት ጋዜጠኛ አዲሱ ሙሉነህ ቀደም ብሎ ከእስር እንደተፈታ ዋዜማ ሰምታለች። 


አሶሴትድ ፕሬስ እስር ላይ የሚገኙት ዘጋቢዎቹ እንዲለቀቁለት ለኢትዮጵያ መንግሥት ደብዳቤ መጻፉን ቀደም ሲል መግለጹ ይታወሳል። [ዋዜማ ራዲዮ]