ዋዜማ ራዲዮ- በራያ ቆቦ በፌደራሉ መንግስትና በሕወሓት አማፅያን መካከል አራት ቀናት ባስቆጠረው ውጊያ ሳቢያ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ሸሽተው ወልዲያ ከተማ መግባታቸውን የዋዜማ ሪፖርተር ከስፍራው ዘግቧል።
በራያ ቆቦ ወረዳ ዞብል፣ ተኩለሽ፣ ካራይላ፣ አርበት እና አራዱም በሚባሉ ስፍራዎች የፌደራሉ መንግስትና የአማራ ልዩ ሀይል በአንድ በኩል መንግስት “አሸባሪ” ሲል በፈረጃቸው የሕወሓት አማፅያን በሌላ በኩል ባደረጉት ውጊያ ደህንነታቸው ያሰጋቸው ነዋሪዎች መኖሪያቸውን ለቀው 50 ኪሎ ሜትር እርቃ ወደምትገኘው ወልዲያ ገብተዋል።
በአካባቢው እየተደረገ ስላለው ውጊያ በመንግስት በኩል የተሰጠ ማብራሪያ የለም። የሕወሐት አማፅያን ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ግን ወታደሮቻቸው ድል እንደቀናቸው በትዊተር ገፃቸው ፅፈዋል።
በስፍራው የሚገኘው የዋዜማ ሪፖርተር ዓርብ ከዕኩለ ቀን ጀምሮ በወልዲያ ከተማና በራያ ቆቦ መካከል በርከት ያለ የመንግስት ወታደሮች እንቅስቃሴ ተመልክቷል።
የሕወሐት አማፅያን በአፋርና በራያ ግንባር በኩል ጥቃት በማድረስ በምዕራብ በኩል በጎንደር ያለውን የመንግስት ሰራዊት ወደ ሌሎች ግንባሮች ለመሳብ አላማ እንዳላቸው የመንግስት ወታደራዊ ሹማምንት ሲናገሩ ተደምጠዋል። መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ መቀሌን ለቆ ከወጣ ሀያ ስድስት ቀናት ተቆጥረዋል።
የመንግስትን የተናጠል የተኩስ አቁም በዝርዝር ቅድመ ሁኔታዎች ያልተቀበለው የሕወሐት አማፂ ቡድን በተለያዩ አቅጣጫዎች ውጊያ በመክፈት በመንግስት ላይ ጫና ለማሳደር እየሞከረ ነው። ዋዜማ ራዲዮ
የአዘጋጁ ማስታወሻ- ይህ ዘገባ ሐምሌ 16 ቀን 2013 ዓ. ም ዓርብ ከቀትር በኋላ በአዲስ አበባ አቆጣጠር ከቀኑ 10 ሰዓት የተጠናቀረ ነው።