AP Photo/Mulugeta Ayene

ዋዜማ ራዲዮ- የኮሮናን ወረርሽኝ ለመከላከል የሚደረገው የእጅ ንፅህና አጠባበቅ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ5 በመቶ በታች እንደሆነ የፌደራል ጤና ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተተባበር በ14 ከተሞች ላይ የሰራው ጥናት ግኝት ያሳያል፡፡


የኮሮናን ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የአለም የጤና ድርጅት ካስቀመጣቸው መንገዶች መካከል የእጅ ንፅህናን በውሀ እና በሳሙና መታጠብ አልያም የእጅ ንፅህና መጠበቂያ ሳኒታይዘሮችን በየጊዜው መጠቀም አንዱ እና ዋነኛው ነው፡፡


ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት መጋቢት 4 2012 ዓ.ም ጀምሮ በነበሩት ጥቂት ወራትም በየፋርማሲው የነበረው የእጅ ማፅጃ ፈሳሽ (ሳኒታይዘር) ፍላጎት እና የግዢ ሰልፍ እጅግ ከፍተኛ ነበር፡፡


ፍላጎቱን ተከትሎም በየክልሉ የሚሰጠውን ፍቃድ ሳይጨም የፌደራል ምግብ እና መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ከ100 በላይ ለሚሆኑ አምራቾች የሳኒታይዘር ማምረቻ ፍቃድ ሰጥቶ በሰፊው መመረት ጀምሮ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ አሁን ለእጅ ማፅጃ ፈሳሽ (ሳኒታይዘር) ያለው ፍላጎት እጅግ ተቃራኒ እንደሆነ የዋዜማ ሪፖርተር ያነጋገረቻቸው አምራቾች ይገልፃሉ፡፡


“ኮሮና እንደገባ በቀን እስከ 30ሺህ ሊትር ሳኒታይዘር እናመርት ነበር” ይላሉ የኢትዮጵያ መድሀነት ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ታዬ፡፡ አሁን ግን በአማካይ በቀን 165 ሊትር ያህል ብቻ እያመረቱ ነው።

“መጥቶ የሚጠይቅ አከፋፋይም የለም፡፡ ምክኒያቱም የወሰዱትን እንኳን ሸጠው አልጨረሱም፡፡ ” ይላሉ አቶ ተስፋዬ ፡፡


አክለውም “ሀገሪቱ ላይ በየቀኑ የሚሰማ ብዙ ትኩሳት አለ ግን ያው በሽታውም በዛው ልክ እየተባባሰ ነው :: እና በዚህ የምርጫ ወቅት እንኳን ፖለቲከኞች በቅስቀሳ ወቅት ህዝቡ መከላከያውን እንዲተገብር መልክት ቢያስተላልፉ መልካም ነበር” ብለዋል::


የአቶ ተስፋዬን ሀሳብ የሚጋሩት የታፍለን ኢንዱስትሪ ቴክኒካል ማናጀር አቶ ታደለ አባተ በበኩላቸው “አሁን ላይ ሳኒታይዘር ተጠቃሚ የለም ማለት ይቀላል፡፡ ከድርጅቶች እና ከትምህርት ቤቶች ውጪ ሳኒታይዘር የሚገዛ የለም፡፡ በፊተ በወር 50ሺህ ሊትር እናመርት ነበር አሁን በወር 5ሺህ ሊትር እንኳን አንሸጠጥም፡፡” በማለት ለዋዜማ ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡


እንደ ጤና ሚኒስቴር ሪፖርት አሁን ላይ በመላ ሀገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 39,992 የደረሰ ሲሆን የ 4,048 ሰዎች ህይወትም አልፏል፡፡

ታዲያ እንዲህ በሽታው በስፋት በተሰራጨበት ወቅት መዘናጋቱ ለምንድን ነው ለሚለው ጥያቄ የመዲናዋ ነዋሪ የሆነው እደማርያም ብርሀኔ “በፊት በሽታው ገባ እንደተባለ አካባቢ ነው እንጂ አሁን ላይ ሳኒታይዘር መጠቀም የሚባለው ነገር ትዝም አይለኝም፡፡እውነቱን ለመናገር በሀገሪቱ ስንት ግድያ እና መፈናቀል እየሰማሁ ኮሮና ያን ያህል አያስጨንቀኝም፡፡” ይላል፡፡


ወ/ሮ ሳባ ረታ የተባሉ ሌላ ነዋሪ ደግሞ በበኩላቸው “ሁለት ቀን እንኳን የማታስጠቅም ሳኒታየይዘር 40 እና 50 ብር ነው የመሚሸጠው፡፡ ኑሮ እንዲህ ጣሪያ በነካበት ጊዜ ብር ለሳኒታይዘር ማውጣት ከባድ ነው፡፡ ቤት ስንሆን እንታጠባለን ውጪ ስንንቀሳቀስ ግን የዛሬ አመት እንደነበረው እጅ መታጠቢያ እንኳን አሁን በየቦታው የለም፡፡ ስለዚህ ያው መታጠቡም ይቀራል ” ብለዋል፡፡


በጥቅሉ በመላ ሀገሪቱ የእጅ ንፅህናን በመጠበቅ ረገድ ያለው ትግበራ ከ90 በመቶ በላይ ማሽቆልቆሉን ዋዜማ ከጤና ሚኒስቴር ያገኘችው መረጃ ያሳያል፡፡


የቫይረሱን መከላከያ መንገዶች ምን ያህል እየተተገበሩ እንደሆነ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በተባበር በ15 ከተሞች ላይ ባደረገው ጥናት በአዲስ አበባ ከተማ ያለው የእጅ ንፅህና አጠባበቅ ከ 10 በመቶ በታች ሲሆን በቀሪዎቹ 14 ከተሞች ደግሞ ከ5 በመቶ በታች እንደሆነ ያሳያል፡፡


አሁን ላይ የኮሮና ቫይረስ መከላከል እና መቆጣጠር ሀላፊነት የጤና ሚኒስቴር ብቻ እየተደረገ እንደሆነ የገለፁት በጤና ሚኒስቴር የኮቪድ 19 መከላከል እና መቆጣጠር ምላሽ ግብረ ሀይል አስተባባሪ መብራቱ ማሴቦ (ፒ.ኤች.ዲ) ሁሉም ተቋማት እና ህብረተሰቡ እንደመጀመርያው ሀላፊነት ሊሰማው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡


አክለውም እጅ መታጠቡም ሆነ ሳኒታይዘር መጠቀሙ መቀነሱ በግልፅ የሚታይ መሆኑንን የገለፁ ሲሆን በየቦታው ድንገተኛ ቁጥጥር የሚያደርግ ቡድን መቋቋሙንም ለዋዜማ ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡


በኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ባለሞያ የሆኑት አቶ ዘነበ ግርማ በበኩላቸው የሚስተዋለው ችግር እየገዙ አለመጠቀም ብቻ ሳይሆን የገዙትንም በአግባቡ አለጠቀም ላይ ነው፡፡


“ ሳኒታይዘር ቢያንስ 70 በመቶ የሚሆን የአልኮል መጠን በውስጡ ሊኖረው ይገባል ቦርሳችን ላይ እና ቀበቷችን ላይ አንጠልጥለን በፀሀይ ይዘነው ስንዞር ግን የአለኮል መጠኑ ይቀንሳል ስለዚህ እሱ ላይም ህብረተሰቡ ትኩረት አድርጎ በአግባቡ መተግበር ይኖርበታል::” ብለዋል:: [ዋዜማ ራዲዮ]