ዋዜማ ራዲዮ – የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግስት አካሂደዋለሁ ብሎ በዕቅድ ከያዛቸው የፖለቲካ ማሻሻያ አንዱ የሆነው የፀጥታና ደህንነት መዋቅራዊ ማሻሻያ ነው። ዋዜማ ራዲዮ አሁን በጠቅላይ ሚንስትሩ እጅ የሚገኘውንና የሀገሪቱን የፌደራልና የክልል ፖሊስ አደረጃጀት የሚወስን ረቂቅ ሰነድ ዋዜማ ራዲዮ ተመልክታለች። በአዲሱ አደረጃጀት የክልል ልዩ ኀይል አልተካተተም። የክልል ፖሊስ የስልጣን ወሰንና ሌሎች ጉዳዮችን ያነሳል። ዝርዝሩን አንብቡት
በሰላም ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ፖሊስ የሪፎርም ግብረሃይል ቡድን የተዘጋጁት ሁለት ሰነዶች የኢትዮጵያ ፖሊስ መርህ እና ፍልስፍና ምን መሆን እንዳለበት የሚያብራራ መመሪያ (ዶክተሪን) እና የክልል ፖሊስ ተጠሪነትን የትጥቅ እና የተልዕኮን ወሰን ዘርዝሮ የሚያስቀመጥ ነው።
በተለይ የክልል ፖሊሶችን የግዳጅ እና ተልእኮ እንዲሁም የጦር መሳሪያ የትጥቅ ሁኔታን በዝርዝር የሚያስቀምጠው ሰነድ “ልዩ ኀይል” የተሰኘውን የክልሎች አደረጃጀትን እውቅና የሚነፍግም ነው።
ከፖሊስ ምልመላ እስከ ስልጠናና እና የትምህርት ማእቀፍ ከዚህም ተሻግሮ ለፖሊስነት የሚመለመሉ ዜጎች ሊኖራቸው የሚገቡ ስብእናን ያትታል። በተለይ አሁን በሀገሪቱ እየታየ ለመጣው የፀጥታ መደፍረስም ሆነ በክልሎች መካከል በሚስተዋለው የልዩ ሃይል ፖሊስ ጦር የማደረጃት እንቅስቃሴ ስጋትነቱንም በግልፅ እንዲህ ያስቀምጣል
‘’ከፖሊስ እሴትና ሙያዊ አገልግሎት ይልቅ የግለስቦችን እና ቡድኖችን የፖለቲካ አመለካከትና ፍላጎት መሰረት ያደረጉ በክልል በዞን እና በወረዳ ጭምር በመንፀባረቃችው የሀገሪቱን ሰላም አደጋላይ ሊጥሉ የሚችሉ የፖሊስ አደረጃጀቶች በየክልሉ እየተፈጠሩ ይገኛሉ፡፡ ግልፅ አደጋ በፌደራላዊ ሥርአቱ ላይ ተደቅኖ በመገኘቱ እና የፌደራል የመንግስትን አወቃቀር ሥርአት የሚከተሉ ሌሎች የአለማችን ሀገራት ዘንድ በተገኙ ተሞክሮዎች የፌደራል እና የየክልሉ ፖሊስ ሊደራጅባቸው የሚገቡ አግባቦችን፣ የዕዝ ሰንሰለቶችን እና የግንኙነት አግባቦችን በግልጽ ማመላከት አስፈላጊ ነው’’ በሚል በሀገሪቱ የሚታየውን የዘርፉ ችግር ያስረዳል።
ቀጣዩን የሀገሪቱን የፖሊስ አደረጃጀት ፍፁም ዓለም አቀፋዊ ደረጃን በተላበሰ መልኩ የመምራተ ዓላማ እንዳለው የሚናገረው ሰነድ በክልሎች ደረጃ የሚቋቋመው የፖሊስ ሃይል የዜጎችን በሰላም ወጥቶ የመግባት ደህንነት ማረጋገጥ ላይ ብቻ መሆን እንዳለበት ያሰምርበታል። የክልልና የፌደራል ፖሊስ መካከል ያለውን የተልዕኮ ድርሻንም ድንበር ለማበጀት ሞክሯል።
‘’የክልል ፖሊስ በክልል ወሰን ውስጥ ለሚከሰቱ መደበኛ የወንጀል ድርጊቶችን በመከላከል የክልሉ ነዋሪ ሰላማዊ የእለት ተእለት ተግባሩን እንዲፈጽም ማስቻል ነው”
የፌደራል ፖሊስ ተልእኮ ሃገርና ህዝብን ለከፋ አደጋ ሊያጋልጡ የሚችሉና ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርአቱን ሊያናጉና ሊያፈርሱ የሚችሉ እንዲሁም መሰረታዊ የዜጎችን የእኩልነትና ሰብአዊ መብቶች ላይ ከባድ አዳጋ ሊጋርጡ የሚችሉ ሃገር አቀፍና ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ የወንጀል ድርጊቶችንና ስጋቶችን መቆጣጠር እንደሆነ ያትታል።
ሰነዱ የክልል የፖሊስ ሃይል ሊታጠቅ የሚገባውን የጦር መሳሪያ ጭምር በአይነት እና በመጠን ዘርዝሮ ያስቀምጣል።
የትጥቅ አይነትን መዘርዘር ያስፈለገው በአሁኑ ወቅት ክልሎች መደበኛን ፖሊስ በልዩ ኀይል እየተኩ እና በሀገር መከላከያ ሰራዊት ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ የታጠቀ ልዩ ኀይል ህዝብን በማስፈራራት እና በማሸማቀቅ በሙያ የታገዘ (ፕሮፌሽናል) ፖሊስ ከሚያከናውነው ወንጀልን ከመከላከል የተሻገረ ስጋት በሀገር ደረጃ መፍጠሩንም ይጠቅሳል።
በቅርብ ጊዜ በተለያዩ ክልሎች ተነስተው የነበሩ ግጭቶችንና ያደረሱትን ጉዳትም እንደ አስረጂ አድርጎ አቅርቧል። በሱማሌ እና በኦሮሚያ፤ በአማራና በትግራይ በቤኒሻንጉልና በአማራ/ኦሮሚያ፤ በሱማሌ እና በአፋር፤ በሀረሪ፤ በውስጣቸው የታየውና እየታየ ያለው ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ እና ስጋት መነሻው ህብረተሰቡን በማግለል በፈረጠመና በታጠቀ የፀጥታ ሀይል ወንጀልን የመከላከል የተሳሳተ አካሄድ ነው ብሎ ያምናል ።
ወንጀልን የመከላከል ተዕእኮ እንዲኖረው ታስቦ የሚደራጀው የክልሎች መደበኛ የፖሊስ ኀይል በነፍስ ወከፍና በቡድን የሚታጠቋቸው ትጥቆች በቀረበው ጥናት ላይ ተዘርዝረዋል።።
በወንጀል መከላክል እና በምርመራ ስራ የሚሰማሩ የፖሊስ አባላት የሚታጠቁት የነፍስ ወከፍ ትጥቅ፣ ሃላፊነታቸው ከስታፍ ቲም ሃላፊ በላይ የሆኑ መኮንኖች የቢሮ የፖሊስ ስራተኞች የሚይዙ የነፍስ ወከፍ ትጥቅ በዝርዝር ተለይቶ እንዲቀመጥ ተደርጓል።
ለመደበኛው ፖሊስ የቡድን ትጥቅ ሲባልም እያንዳንዱ አመራርም ሆነ አባሎች ለሚሰጡት ፖሊሳዊ አገልግሎት በቡድን ማከናወን የሚያስችል ትጥቅ ሲሆን እነኚህ ትጥቆች አገልግሎት ሲሰጡ የሚረከቧቸው እና አገልግሎት ሲጨርሱ የሚያስረክብዋቸው ማእከላዊ ቦታዎች ላይ የሚቀመጡም ይሆናሉ።
በወንጀል መከላከል እና በምርመራ ስራ የሚሰማሩ የፖሊስ አባላት ሽጉጥ ፣የሽጉጥ ካርታ፣ የሽጉጥ ጥይት፣ የሽጉጥ ማህደርን ፤የእጅ ባትሪ፤ካቴና የመሳሰሉ መሳሪያዎችን እንዲጠቀሙ ተለይቶ እና በቁጥርም ተወስኖ ጭምር የተቀመጠ ሲሆን ፖሊሶች በነፍስ ወከፍ እና በቡድን ሊታጠቋቸው የሚገቡ ትጥቆች ተለይተዋል።
ለአድማ ብተናና ለፈንጂ ማምከን የሚመደቡ ሌሎች የፖሊስ ክፍሎችም ለስራቸው አስፈላጊ ናቸው የተባሉ የትጥቅ አይነቶች ተዘርዝረው ቀርበዋል።
ይህ ሰነድ በአሁኑ ወቅት በዘመናዊ የቡድን የጦር መሳሪያ ጭምር እየተደራጁ የሚገኙ የክልል ልዩ ኀይል አደረጃጀትን እውቅና የማይሰጥ በመሆኑ ስለ ክልል ልዩ ይል አደረጃጀት እና የትጥቅ ሁኔታ ምንም ያስቀመጠው ዝርዝር የለም።
ይህ ሰነድ መስከረም ወር ላይ ጥናቱ ተጠናቆና በባለሙያዎች ምክክር ተደርጎበት ኋላ ላይ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተመራ ሲሆን ከክልል መሪዎችና ከህዝብ እንደራሴዎች ጋር ውይይት ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል። [ዋዜማ ራዲዮ]