ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም በዋስ ተፈተዋል

Sibhat Nega

ዋዜማ ራዲዮ- የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዛሬ ረፋድ ላይ በፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 2ኛ የጌዜ ቀጠሮ ችሎት ተሰይሞ በእነ አቶ ስበሀት ነጋ የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ላይ ካሉ 9 ተጠርጣሪዎች በሰባቱ ላይ የቅድመ ምርመራ ምስክር ለማስማት ሌላ መዝገብ ማስከፈቱን ለችሎቱ ገልፅዋል፡፡


የዋዜማ ሪፖርተር እንደዘገበችው፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀድሞ ፕሬዝዳንት የነበሩት ወ/ሮ ህርየቲ ምህረት እና አቶ ወልደጊዮርጊስ ደስታ ደግሞ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ወደ በረሀ አብረው ከመሄዳቸው በቀር ክስ የሚያስመሰረት ፍሬ ነገር በምርመራ መዝገብ አለማግኘቱን በመግለፅ ፍርድ ቤቱ በበቂ ዋስትና እንዲፈታቸው አቃቤ ህግ ጠይቋል፡፡


አቶ ስበሀትን ጨምሮ ሌሎቹን ሰባት ተጠርጣሪዎች ግን ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ለማፍረስ ወንጀል እና በሽብር ክስ ለመመስረት መዘጋጀቱን በመግለፅ ለዚህም 83 የሚሆኑ ምስክሮችን በቅድመ ምርምራ ችሎት ሊያሰማ መዘጋጀቱን አብራርቷል፡፡
አቃቤ ህጉ አክሎም አቶ ስበሀት “አሁን ያለው መንግስት ጥገኛ መንግስት በመሆኑ ከስልጣን መውረድ አለበት” የሚል የስምምነት ሰነድ ከህወሀት ማዕከላዊ ኮሚቴ እንደደረሳቸው እና ምክር በመለገስ ወታደራዊ ኮማንደ ፖስት እንዲቋቋም ከፍተኛ ድርሻ ነበራቸው ብሏል፡፡

ሌሎች ተጠርጣሪዎች ደግሞ መከታ የተባለ የኢኮኖሚ ኮሚቴ በማቋቋም “መከላካያ ሰራዊትን ለወጋው ጦር ምግብ ሲያመላልሱ ነበር” በማለት ከደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ 50 ሚሊዮን ብር ለዚሁ አላማ መውጣቱን ገልፅዋል፡፡
መዝገቡ ከመዘጋቱ በፊት የምርመራ መዝገቡን ችሎቱ አስቀርቦ እንዲመረምር የጠየቁት ጠበቆች ሰዎች እንዲታሰሩ ሰለሚፈለግ ብቻ ነው እንጂ በቃል የሚነገረው እና የምርመራ መዝገቡ ላይ ያለው ፍሬ ሀሳብ አንድ አይደለም ብለዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም አቶ ስበሀት ነጋን እንዲያክም የተፈቀደው የግል ሆስፒታል መሳሪያዎቼን ነቅዬ ያሉበት ድረስ አልሄድም በማለቱ እስካሁን ህክምና እንዳላገኙ ያስረዱት ጠበቆች ቅድመ ምርመራ ዋስትናን የሚከለክል ባለመሆኑ ተጠርጣሪዎች በውጭ ሆነው እንዲከራከሩ እንዲፈቀድ ችሎቱን ጠይቀዋል፡፡

ችሎቱ የአቶ ስበሀትን ህክምና ጉዳይ በተመለከተ የግል ሀኪማቸው ቃለ መሀላ ያረፈበት አቤቱታ እንዲቀርብ ያዘዘ ሲሆን ክርክሩ አቃቤ ህግ ባስከፈተው የቅድመ ምርመራ መዝገብ እንዲቀጥል በመወሰን የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡን ዘግቶታል፡፡
ዋስትና የተጠየቀባቸውን ሁለት ተጠርጣሪዎች የ30ሺህ ብር ዋስትና የፈቀደ ሲሆን ቀሪዎቹ ተጠርጣሪዎች ክርክሩንም በማረፊያ ሆነው እንዲከራከሩ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን በዛሬው ችሎት ወ/ሮ ኪሪያ ኢብራሂም ያልቀረቡ ሲሆን ፖሊስ በዋስ እንደፈታቸው አስረድቷል፡፡
በተጨማሪም በእነ አምባሳደር አባይ ወልዱ እናነነ በዶ/ር አዲስ አለም ቤሌማ የተከፈቱት የክስ መዝገቦችም ተመሳሳይ ክርክር የቀረበባቸው ሲሆን አቃቢ ህግ የቅድመ ምርመራ ምስክሮችን ባስከፈተው አዲስ መዝገብ ክርክሩ እንዲቀጥል በማለት ችሎቱ የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡን ዘግቶታል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]