ዋዜማ ራዲዮ- ጥቅምት 24 ቀን 2013 ምሽት 4:30 ላይ ሁለት አውሮፕላኖች 1.3 ቢሊየን አዲሱን የብር ኖት ጭነው መቀሌ አሉላ አባነጋ አየር ማረፊያ ደረሱ። በተመሳሳይ ወቅት በሕወሐት ታጣቂዎችና በመከላከያ ሰራዊት መካከል ግጭት ተቀሰቀሰ። ከአውሮፕላን ማረፊያው 300 መቶ ሜትር ርቀት ላይ ድንገተኛ ተኩስ ተከፈተ። ፓይለቶቹና የብሔራዊ ባንክ ወኪሎች ህይወታቸውን ለማትረፍ ተሸሸጉ። ትንሽ ቆይቶ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ነን ያሉ ወታደሮች ባደረጉት ድጋፍ 1.3 ቢሊየን ብሩ ከትግራይ የተለያዩ ባንኮች ለመጡ ተወካዮች ተከፋፈለ። ገንዘቡ ለባንኮቹ ስለመድረሱ ብሔራዊ ባንክ እስካሁን ማረጋገጫ አላገኘም። ዋዜማ ስለ ጉዳዩ ተከታዩን ዘገባ አሰናድታለች። አንብቡት
ማክሰኞ ምሽት ግጭቱ ሲነሳ ሁለት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎ አውሮፕላኖች በትግራይ ክልል ላሉ ባንኮች የሚሰራጭ አዲሱን የብር ኖት ጭነው በምትኩ ደግሞ ከትግራይ ክልል ካሉ ባንኮች የተሰበሰቡ አሮጌ የብር ኖቶችን ይዘው ወደ አዲስ አበባ ሊያመጡ ምሽቱ 4.30 ላይ መቀሌ አሉላ አባነጋ አየር ማረፍያ እንደነበሩ መጀመርያ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር አብር አህመድ ነበሩ።
ግጭቱ በተጀመረ በማግስቱ ማለትም ረቡዕ ጥቅምት 25 ቀን 2013 አ.ም በሀገር ውስጥ ቴሌቪዥን ጣብያዎች በዚሁ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ሲሰጡ የአውሮፕላኖቹን ሁኔታ እና በውስጣቸው ጭነውት ስለነበረው አዲሱ ብር መጨረሻ ሳይገልጹ ወደ ሌሎች ማብራሪያዎች አልፈዋል።
“በስድስት ሰዓታት ውስጥ ተኩስ ተቋቁመን ብሩን አድለናል“
ዋዜማ ራዲዮ ለጉዳዩ ቅርበት ከነበራቸው ምንጮቿ እንደሰማችው በትግራይ ክልል የመገናኛ አውታሮች ስለተቋረጡ ስለ ገንዘቡ መዳረሻ በርግጠኝነት ማወቅም ሆነ መናገር አልተቻለም። ሆኖም የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ( ኢቲቪ) ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ በሰጡ ማግስት ማለትም ሀሙስ ጥቅምት 26 ቀን 2013 አ.ም ወደ ትግራይ ስለተለከው አዲስ የብር ኖቶ ያሰራጨው ዜና ብዙ ያልጠሩ ነገሮችን የፈጠረ ነበር።
ዜናው አዲሱ የብር ኖት 1.3 ቢሊየን ሲሆን ከትግራይ ተሰብስቦ የሚመለሰው አሮጌው ብር ደግሞ አራት ቢሊየን መሆኑንና ፣ አዲሱ የብር ኖት በቦይንግ 787 ድሪምላይነር እና ኤርባስ ሁለት አውሮፕላኖች ተጭኖ ማክሰኞ ጥቅምት 24 ቀን 2013 አ.ም ምሽት 4:30 ሰአት መቀሌ አሉላ አባነጋ አውሮፕላን ማረፊያ መድረሱን ጨምሮ ይገልጻል።
በዜናው ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክን ወክሎ ገንዘቡን መቀሌ ላሉ የንግድ ባንክና ሌሎች ተወካዮች ሊያስረክብ የሄደው ቢንያም ፈቃደ ፣ አዲሱን ብር ከአውሮፕላኖቹ አውርደው አሮጌውን ብር በመረካከብ ሂደት ላይ እያሉ ተኩስ እንደሰሙና እንደተደናገጡ ይገልጻል። በዜናው ላይ ተኩሱ የተከፈተው እነሱ ከነበሩበት አካባቢ ከ200 እስከ 300 ሜትር ርቀት ላይ እንደሆነ እና ተኩሱን የከፈተው የትግራይ ልዩ ሀይል መሆኑን መረዳታቸውንም ነው ቢኒያም የሚናገረው።
በተኩሱ በመደናገጣቸው ብሩን አልሆነ ቦታ ትተውት እንደተንቀሳቀሱ የሁለቱ አውሮፕላን አብራሪዎችም ተደናግጠው በመጠለያ ውስጥ ተሸሽገው እንደነበርና መጉላላት እንደነበር ቢኒያም አብራርቷል ። ከዚያም የመከላከያ ሰራዊት አባላት ስፍራው ላይ ደርሰው እንዲረጋጉ እንዳደረጓቸው እና የመከላከያ ሰራዊት አባላት ራሳቸው ሀላፊነት ወስደው እነ ቢኒያም አዲሱን የብር ኖት ማይጨው ፣ አደዋ ፣ ሽሬ እንዳስላሴ ፣ አዲግራት ላሉ ባንኮች እንዲሁም መቀሌ ላለ የወጋገን ባንክ ቅርንጫፍ ማከፋፈላቸውንም አስረድቷል።
ዘገባው አዲሱ የብር ኖት ከተከፋፈለ በሁዋላ ሁለቱ አውሮፕላኖች አሮጌውን አራት ቢሊየን ብር ይዘው ማክሰኞ ጥቅምት 24 ቀን 2013 አ.ም ሌሊት 10 ሰአት ( ረቡዕ ንጋት) ቦሌ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፍያ እስከ ብሄራዊ ባንክ ተወካዩ ማረፋቸውን ይገልጻል።
ይህ ዜና የብሄራዊ ባንክ ሰራተኞች መቀሌ በተኩስ በተናወጠችበት በዛች ሌሊት በስድስት ሰአታት ውስጥ ማይጨው ፣ አደዋ ፣ ሽሬ እንዳስላሴ ፣ አዲግራትና መቀሌ በጥቅሉ አምስት የትግራይ ክልል ውስጥ ባሉ አካባቢዎች ላሉ ባንኮች አዲሱን የብር ኖት በተወካዮቻቸው አማካይነት አከፋፍለው አዲስ አበባ እንደተመለሱ ነው የገለጸው።
ይህ የመንግስት ትርክት ትግራይ በተለይም መቀሌ ከነበረችበት ሁኔታ አንጻር ማመን ከባድ ይሆናል። መከላከያ ስራዊት ከነበረበት ሁኔታ አንጻርም የማከፋፈሉ ስራ ላይ መሳተፉ ተጨማሪ ጥያቄ ያስነሳል።
ተረካቢዎቹና ፀጥታ አስከባሪዎቹ
ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮቻችን እንዳስረዱን የብሔራዊ ባንክ የላከውን ገንዘብ ለመረከብ ከባንክ ተወካዮች ጋር በአሉላ አባነጋ አየር ማረፊያ ተገኝተው የነበሩት ከሰራዊቱ ወደ ሕወሐት የወገኑና ገንዘቡን ለመቀራመት አስቀድመው የተዘጋጁ አካላት ናቸው። በማዕከላዊው መንግስትና በትግራይ ክልል መካከል ይፋዊ ግንኙነት ከተቋረጠ ሁለት ወራት ቢጠጋውም የገንዘቡን መምጣት ክልሉ በአፅንኦት ሲከታተለው እንደነበርና ገንዘቡም እንዲላክ ሲወተውት ነበር።
ገንዘቡ መቀሌ በደረሰበት ሰዓት መከላከያ ሰራዊቱ የመገናኛ ራዲዮ ተቋርጦበት እንዲሁም ራሱን ከጥቃት ለመከላከል የሞት ሽረት ትግል እያደረገ የነበረበት ወቅት ነበር።
የተለመደው የባንኮች የገንዘብ ርክክብ ስርዓት
ባንኮች ከብሄራዊ ባንክ ገንዘብ ሲወስዱ ብሄራዊ ባንክ ካላቸው ፔይመንት ሴትልመንት አካውንታቸው (የምዝገባ አሰራር) ላይ ይቀነሳል። ፔይመንትና ሴትልመንት አካውንት ባንኮች ከብሄራዊ ጋር የሚግባቡበት የምዝገባ አሰራር ነው። ብሄራዊ ባንክም ሆነ አዲስ አበባ ያሉ የባንኮች ዋና መስሪያ ቤቶች ቅርንጫፎቻቸው የተረከቡትን እና የሚያንቀሳቅሱትን ገንዘብም ያውቁበታል ይቆጣጠሩበታል። ስለዚህም ትግራይ ያሉ ባንኮች አዳዲስ የብር ኖቶችን ሲረከቡ የተረከቡትን ገንዘብ መጠን ከወረቀት ስራዎች ባሻገር ባንኮቹ የሚናበቡበት የኮምፒውተር ስርአት ውስጥ ሊመዘግቡት ግድ ነው።
ያነጋገርናቸው የባንክ ባለሙያዎች እንደነገሩን በዚህ መንገድ እንዲመዘገብ ካላረጉ በቀር ብርን ለቅርንጫፍ ባንኮች ለመስጠት የትኛውም ብርን የሚያድል ሰራተኛ ፍቃደኛ አይደለም። ሁለቱ አውሮፕላኖች መቀሌ አርፈው ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በሁዋላ ታድያ በትግራይ ክልል መብራት ከመጥፋቱ ባሻገር ኢንተርኔትና የስልክ ግንኙነቶች መሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ተቋርጦ ነበር። ታድያ ክልሉ በዚህ ሁኔታ እያለ የብሄራዊ ባንክና የንግድ ባንክ እንዲሁም ሌሎች የንግድ ባንኮች የገንዘብ ርክክቡን እንዴትና በምን ማስተማመኛ ፈጸሙት ? የሚለው ሊመለስ የሚገባው ጥያቄ ነው። ምክንያቱም በክልሉ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ትግራይ ክልል ያሉ ባንኮች በሌላው የሀገሪቱ ክፍል ካሉ ቅርንጫፎቻቸው ጋር ከሚገናኙበት የኮር ባንኪንግ ስርአት ተቋርጦ ነበር።
ከዋዜማ ጥያቄ ያቀረብንላቸው ከፍተኛ የባንክ የስራ ሀላፊ ” ስለ ገንዘቡ መድረስ አፋችንን ሞልተን መናገር አንችልም። ግንኙነት መቋረጡ ስለተፈጠረው ነገር ምንም መረጃ እንዳይኖረን አድርጓል” ብለውናል። [ዋዜማ ራዲዮ]