ዋዜማ ራዲዮ- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር ይፈታሉ በሚል የተከራያቸው 560 አውቶብሶች ጉዳይ የአዋጭነትና የግልፅነት ጥያቄዎች እየቀረበበት ነው። አስተዳደሩ ግን የከተማዋን የትራንስፖርት መፍታት ቀዳሚ አጀንዳው መሆኑን ይገልፃል። ።
     
ዋዜማ ራዲዮ እንደተረዳችው ከሆነ አውቶብሶችን ተከራይቶ ለከተማዋ ትራንስፖርት አገልግሎት የማዋሉን ነገር አስበው ወደ ተግባር ሊገቡ የነበሩት የቀድሞው የከተማዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ነበሩ። ሆኖም በወቅቱ ከተለያዩ አካላት ጋር በተደረገ ውይይት “አውቶብስ መከራየቱ አያዋጣም” የሚል አስተያየት ስለበዛ እንዲቀር ተደርጎ ነበር። የአሁኗ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ግን ከጥቅምት 9 2013 አ.ም ጀምሮ የአዲስ አበባን የትራንስፖርት ችግር ያቃልላል በሚል በፍጥነት የአውቶቡስ ኪራይ ዕቅዱን ተግባራዊ አድርገውታል።

አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለተከራያቸው 560 አውቶብሶች ጨረታ እንዳላወጣ ዋዜማ ራዲዮ አረጋግጣለች። የኪራዩ አካሄድ በጨረታ ማለፉ በአንጻሩም ግልጽነትን ሊያመጣ ቢችልም በምን መልኩ አውቶብሶቹ እንደተመረጡም ግልጽ አይደለም። የመስተዳድሩ ሀላፊዎች ከአውቶብሶቹ ባለቤቶች ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገው ከዚያም እንደ አውቶብሶቹ ሁኔታ ወርሀዊ የኪራይ ሂሳብ ወጥቶላቸው ከከተማዋ የትራንስፖርት ቢሮ ጋር ውልን እንደተዋዋሉ ያሰባሰብነው መረጃ ያመለክታል።

 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተከራያቸው አውቶብሶች በብዛት የክፍለ ሀገር መጓጓዣ የነበሩ ናቸው። አሁን በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የጸጥታ ሁኔታ አስተማማኝ ስላልሆነ እንዲሁም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት አውቶብሶቹ የአገልግሎት ገደብም ስላለባቸው በከተማው መሰማራታቸው ለህልውናቸው መቀጠል ደጋፊ እርምጃ መሆኑን የመስተዳድሩ ምንጮቻችን ይናገራሉ። ነገር ግን አውቶብሶችን የመከራየቱ ነገር የከተማ አስተዳደሩን ለገንዘብ ብክነት የሚዳርግ እና መከራት አስፈላጊ ቢሆን እንኳ ሌሎች የተሻሉ መንገዶች እንደነበሩ በሂደቱ የተሳተፉት የመረጃ ምንጮች ያሰምሩበታል።

የከተማ አስተዳደሩ ለ560ዎቹ አውቶብሶቹ ኪራይ በወር 71 ሚሊየን ብር ያወጣል። እንደተባለው የአውቶብሶቹ ኪራይ ለስድስት ወራት ብቻ የሚቆይ ቢሆን እንኳ የከተማ አስተዳደሩ ለአውቶብሶቹ ኪራይ ለስድስት ወራት 426 ሚሊየን ብር ወጪ ይጠብቀዋል። ይህን ያክል መጠን ያለውን ገንዘብ ለኪራይ ከማውጣት እስከ 100 የሚደርሱ አውቶብሶችን መግዛት አይሻልም ነበር ወይ ? የሚል ጥያቄን አስነስቷል። የከተማ አስተዳደሩ በቢሊየን በሚቆጠር ገንዘብ ሶስት ሺህ አውቶብሶችን ለመግዛት እየተዘጋጀ መሆኑን በቅርቡ ወራት አስታውቋል። ታዲያ ስለምን ከፍ ያለ ኪራይ ወደሚያስወጣ ኪራይ መሄድን እንደመረጠ አሳማኝ ምክንያት አልቀረበም። መስተዳድሩ በጉዳዩ ላይ ሀሳብ እንዲሰጥ ለማግባባት ብንሞክርም ከምክትል ከንቲባዋ በቀር በዚህ ጉዳይ መናገር የሚችል የለም በሚል ምክንያት የተብራራ ምላሽ አላገኘንም።

ዋዜማ ራዲዮ ከምንጮቿ እንደሰማችው ከሆነ በኪራይ ወደ ስራ ገቡ የተባሉት አውቶብሶች እንደየደረጃቸው በአንበሳ አውቶብስና በሸገር ባስ ታሪፍ ተሳፋሪዎችን እያስከፈሉ ይሰሩና በኪራይ አገልግሎቱን ስለሰጡ ብቻ ከከተማ አስተዳደሩ እንደየአውቶብሶቹ ደረጃ ወርሀዊ ኪራይ ይከፈላቸዋል።

የከተማ አስተዳደሩ አውቶብሶቹን በደፈናው ከሚከራይ ይልቅ አውቶብሶቹ ተሳፋሪዎችን ብናስከፍል ያዋጣናል የሚሉት ዋጋ አቅርበው በሱ ላይ ድርድር ከተደረ በሁዋላ የከተማ ትራንስፖርት እንዲሰጡ ቢፈቀድ ; እንዲሁም በአንበሳ አውቶብስና ሸገር ባስ ታሪፍ ሰርተው ህጋዊ ማረጋገጫ አቅርበው በመንግስት ታሪፍ በመስራታቸው ያጋጠማቸውን የገቢ ክፍተት ከተማ አስተዳደሩ ይሙላላቸው የሚሉ አማራጮች የቀረቡ ቢሆንም ተቀባይነት አለማግኘቱን ሰምተናል። [ዋዜማ ራዲዮ]

To reach Wazema Editors write —wazemaradio@gmail.com