- ውይይት ተደርጎ ቤተክርስቲያኗ የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክትን በራሷ መሀንዲስ እንድትገመግም ከስምምነት ተደርሷል
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ ትናንት (ሐሙስ) ወደ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ፅህፈት ቤት የልዑካን ቡድን ልከው ውይይት መደረጉን ዋዜማ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።
በመስቀል አደባባይና በጃንሜዳ የበዓል ማክበሪያ ቦታዎች ላይ መንግስት እያከናወነ ባለው ተግባር ቅሬታ የገባት የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅሬታዋን በዝርዝር ለልዑካን ቡድኑ አስረድታለች።
መንግስት አዲስ አበባ ከተማን ለማስዋብ በሚል እቅዱ የመስቀል አደባባይ መዘጋጃ ቤት ፕሮጀክትን በ2.5 ቢሊየን ብር ለመገንባት የመስቀል አደባባይ ቁፋሮን መጀመሩና የጃንሜዳ ጥምቀት ማክበሪያ ቦታን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቀነስ በሚል የፒያሳው የአትክልት ተራ ለጊዜው ወደዚያ እንዲሸጋገር ማድረጉን ተከትሎ ; የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ” በቦታዎቹ ላይ ዋና ዋና ክብረ በአላትን እንደማክበሯ የቦታዎቹም ጥንተ ባለቤት እንደመሆኗ ሳታውቅና ሳትፈቅድ መንግስት ከዚህ ውሳኔ ላይ መደረሱ በእጅጉ እንዳሳዘናትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አፋጣኝ ማብራሪያ እንዲሰጣት ” በደብዳቤ መጠየቋ ይታወቃል። በጉዳዩ ላይ ዋዜማ ይፋ ያደረገችው ዝርዝር ዘገባ እዚህ ያንብቡት።
ይህን ተከትሎም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በአማካሪያቸው ነብዩ ባዬ የተመራ ቡድን ወደ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ፅህፈት ቤት ልከው ከቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች ጋር ውይይት ተካሂዷል ።
ከአቶ ነብዩ ባዬ በተጨማሪ የከተማ አስተዳደሩ ስነ ህንፃ አማካሪ፣ የኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፊ፣ የፕላን ኮሚሽንና የግንባታ ፈቃድ ቢሮ ሀላፊዎች ከከተማ አስተዳደሩ በኩል ተሳትፈዋል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በኩል ፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ ፣ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃና መምሪያ እንዲሁም የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ያሬድ ውይይቱን መርተዋል። ሌሎች አባቶችም ተገኝተዋል።
በውይይቱ ላይ አቡነ ያሬድ የከተማ አስተዳደሩን ወኪሎች ” ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ ሉአላዊነቷ እንደተጠበቀ ሆኖ ሀገራዊ እንደመሆኗ የከተማ አስተዳደሩ ፍቃዷን ሳይጠይቅ ፣ ይሁንታዋን ሳያገኝ ጃን ሜዳ እና መስቀል አደባባይ ላይ ያደረገው ድርጊት በእጅጉ አሳዝኗታል ” ካሉ በኋላ ለአስተዳደሩ ወኪሎች ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል።
መንግስት ድርጊቱን ሲፈጽም ቤተ ክርስቲያንን ለምን አላማከረም? ቤተ ክርቲያኒቱን ማሳወቅ ያልተፈለገው ሆን ተብሎ ነው ወይስ በመዘንጋት? የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት መሰረታዊ አላማውስ ምንድነው? የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል።
ከቤተ ክርስቲያኒቱ ተወካዮች በኩል አንድ ተሳታፊም ለከተማ አስተዳደሩ ወኪሎች ” የከተማ አስተዳደሩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከመናቅና ምንም አታመጣም በሚል ነው ወይ እንዲህ አይነት ድርጊት ውስጥ የገባው?” ሲሉ ከረር ያለ ጥያቄ ማንሳታቸውንም ዋዜማ ራዲዮ ሰምታለች።
የከተማ አስተዳደሩ ተወካዮችም መንግስት ቤተ ክርስቲያኗንም ሆነ ህዝቡን ለማስቀየም አስቦ የሰራው አንድም ድርጊት የለም ማለታቸውን ሰምተናል። የጃን ሜዳው ውሳኔ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሳናሳውቅ የገባንበት የወረርሽኝ ጉዳይ አጣድፎን እንጂ ማሳወቅ ልናደርገው የሚገባ ቀላሉ ስራ ነበርም ብለው መልሰዋል።
የመስቀል አደባባዩንም ፕሮጀክት ሳናሳውቅ መጀመራችን ስህተት ነው ብለው አስተዳደሩ ግን አላማው ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የመስቀል በአልን ስታከብር ቦታው ይበልጥ እንዲያምር በማሰብ ምቹ የሆነ ቴክኖሎጂም እንዲኖረው ታስቦም መሆኑን ገልጸዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ጭንቀት የነበረው እንደውም የተቆፈረው የመስቀል አደባባይ ቦታ በፍጥነት የኮንክሪት ስራው ተጠናቆ ለፊታችን መስቀል በአል እንዲደርስና ቀሪ ስራዎቹን ከዚያ በሁዋላ ለማከናወን እንዲሁም መስቀል አደባባይ አሁን ካለው አቅም በላይ ሰፋ ብሎ ተጨማሪ ሰው ማስተናገድ የሚችልና ምቹ ማድረግ እንደሆነም የከተማ አስተዳደሩ ወኪሎች ለቤተክርስቲያኒቱ አባቶች እንዳብራሩም ነው ዋዜማ ራዲዮ ከምንጮቿ የሰማችው።
በውይይቱ ላይ የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት ዲዛይንን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የራሷን መሀንዲሶች በመወከል እንድትገመግምና መሻሻል ያለባቸው የዲዛይን ይዘቶች ካሉም ሀሳብ እንድትሰጥበት ከስምምነት መደረሱን ፣ እንዲሁም አሁን ላይ የተለቀቀው የአኒሜሽ ምስል የፕሮጀክቱን ግልጽነት ለማሳወቅ በቂ ባለመሆኑ ዝርዝር የፕሮጀክቱ ይዘቶች ላይ ውይይት እንዲደረግም መግባባት ላይ እንደተደረሰም ሰምተናል።
በተጨማሪም ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በጃን ሜዳም ሆነ በመስቀል አደባባይ የትኛውም የማዘመን ስራ ቢሰራ የመጠቀም መብቷ የማይነካ መሆኑን የሚያሳይ የጽሁፍ ማስተማመኛ ሰነድ እንዲሰጣት ማስቻልም የውይይቱ አካል ነበር።
አሁን ላይ መንግስት ቤተ ክርስቲያኒቱን ሳያወያይ ለፈጸመው ድርጊትም ይቅርታ ሊጠይቅ እንደሚገባ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች ለከተማ አስተዳደሩ ወኪሎች አሳውቀው ከመግባባት ላይ ተደርሷል። ይህ ግን ከከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ጋር ውይይት ተደርጎበት በቀጣይ ቀናት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስና ሊቀ ጳጳሳት በተገኙበት ሊከናውን እንደሚችል ከምንጫችን ሰምተናል። [ዋዜማ ራዲዮ]
To contact Wazema Radio, please write to wazemaradio@gmail.com