በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር በፀጥታ ሀይሎችና በታጣቂ ሀይሎች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት የሰው ህይወት መጥፋቱን ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ዋዜማ ራዲዮ- በማዕከላዊ ጎንደር ጭልጋ ወረዳ፡ ከአይከል ከተማ አንሥቶ እስከ ጓንግ- ቡሆና ድረስ በአካባቢው ታጣቂ ገበሬዎች (የቅማንት) እና በክልሉ ልዩ ኃይል መካከል በመስከረም 16/2012 ዓ.ም ጀምሮ የተቀሰቀሰው ግጭት እስከዛሬ ጧት ድረስ እንዳልተረጋጋ በአካባቢው ያነጋገርናቸው እማኞች ገለጹ፡፡
ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ዛሬ 4ኛ ቀኑ ሲሆን ከአይከል ከተማ ልዩ ስሙ ጓንግ አንስቶ እስከ ቡሆና አካባቢ አልፎ አልፎ የተኩስ ድምፅ እንደሚሰማ የዓይን እማኞች ገልጸዋል፡፡ በ16/01/2012 ዓ.ም የክልሉ ልዩ ኃይል ወደ አይከል ከተማ ሊገባ ሲል በታጠቁ የአካባቢው ገበሬዎች በልዩ ኃይሉ ላይ ተኩስ እንደከፈቱ እና ልዩ ኃይሉም የአጸፋ መልስ የተኩስ ልውውጥ በማድረጉ ግጭቱ ሊቀሰቀስ እንደቻለ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በግጭቱ እስካሁን ቁጥራቸው ያልታወቀ ገበሬዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡
በ2008ዓ.ም የክልሉ መንግሥት በማእከላዊ ጎንደር ዞን በቅማንት የማንነት ጉዳይ ላይ በተደረገው የወሰን ማካለል ሂደት ነጻ ቀጠና ሆነው እንዲቀጥሉ በተወሰኑት ጀጀቢት፣ ሽንፋና ልንጫ ሦስት ቀበሌዎች በመንግስትና በአካባቢው ገበሬዎች መካከል ከፍተኛ ያለመግባባት ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡ በእነዚህ ሦስት ቀበሌዎች ከቅማንት በተጨማሪ የአማራ ተወላጆች በቀበሌዎች አብረው ይኖራሉ ፡፡
የአማራ ክልል የሠላምና ደኅነነት ግንባታ ቢሮ ሓላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር 18/01/2012 ዓ.ም በሰጡት ማብራሪያ በማእከላዊ ጎንደር ጨልጋና አካባቢው የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ፣ መንግሥት የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት እየሠራ ባለበት ወቅት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የችግሩ ፈጣሪዎች “ከሌላ ወገን በሚያገኙት ድጋፍ” አካባቢውን የጦርነት ቀጠና የማድረግ ዓላማ እንዳላቸው አቶ አገኘሁ የገለጹ ሲሆን ነገር ግን የክልሉ መንግሥት በእነዚህ ችግር ፈጣሪዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ይሁንና ጎንደር አዘዞ ወጣ ብሎ እስከ ጓንግ ድረስ የሚሰማው የተኩስ ድምፅ እስካሁን [እሁድ ከቀትር በኋላ] ሊቆም አልቻለም፡፡ በልዩ ኃይሉና በአካባቢው ( የቅማንት) ገበሬዎች በሚደረገው የተኩስ ልውውጥ ምክንያት ሌሎች ንጹሃን ዜጎች ላይ ጉዳት እየደረሰ እንደሆነ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በአካባቢው የሚገኘው የሀገር መከላከለያ ችግሩን ለማብረድ ጣልቃ የገባ ቢሆንም እስካሁን ሰላም ሊመጣ አልቻለም፡፡ በመከላከያ በኩል አንድ ሻምበል እንደቆሰለ እማኞች ጨምረው ገልጸዋል፡፡
እሁድ ከቀትር በኋላ በአይከል ከተማ አካባቢ አልፎ አልፎ የስማ የነበረው የተኩስ ደምፅ ጋብ ቢልም ወደ ግጓንግና ቡሆና አካባቢ ግን የተኩስ ድምፁ ሊቆም አልቻለም፡፡ እንደ ምንጮች ከሆነ ጓንግ አካባቢ ወደ 15 መኪና የሚሆኑ የክልሉ ልዩ ኃይሎች ወደ አይከል ከተማው መግባት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ ከጎንደር መተማ የሚደረገው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ቆሟል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]