ዋዜማ ራዲዮ- የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዲዛይን የተሰራው 16 የሀይል ማመንጫ ተርባይኖች እንዲኖሩት ታስቦ መሆኑ የሚታወስ ነው። እነዚህ 16 የሀይል ማመንጫ ተርባይኖች በተለያየ ጊዜ በተሰሩ የጥናት ማሻሻያዎች ከህዳሴው ግድብ የሚያመነጩት ሀይል 6450 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሀይል ይሆናል ተብሏል። የተርባይኖች ምርትና ተከላ ስራ ላይ የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ድርሻ ሙሉ ተቀምቶ ሙሉ ስራው ለውጭ ኩባንያዎች መሰጠቱ የሚታወቅ ነው።


ዋዜማ ራዲዮ ያገኘችው መረጃ እንደሚያሳየው አሁን ላይ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ይገጠማሉ ተብሎ ከነበሩት 16 የሀይል ማመንጫ ተርባይኖች ውስጥ ሁለቱ እንዲቀሩ ተወስኗል። ግድቡ አስራ አራት ተርባይኖች ብቻ እንዲኖሩት የሚያስችል የዕቅድ ክለሳ እንዲደረግ በከፍተኛ የመንግስት አካላት ውሳኔ መተላለፉን ስምተናል።


ለመሆኑ እንዲህ አይነት ውሳኔ መወሰኑ ግድቡ በሚያስገኘው ጥቅምና ጉዳት ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ ምንድነው? የሚል ጥያቄ ዋዜማ ራዲዮ አቅርባ ምላሽን አግኝታለች። በመጀመርያ የግድቡ የሲቪል ስራ ሲከናወን 16 የሀይል ማመንጫ ተርባይኖችን ገጥሞ ሀይል ለማመንጨት በመሆኑ ለእያንዳንዱ ተርባይን ማስቀመጫ የሚሆን ግንባታ ወጪ ወጥቶ በግድቡ ላይ ተከናውኗል ። ሁለቱ የሀይል ማመንጫ ተርባይኖች የማይገጠሙ ከሆነ ሁለቱን ሀይል ማመንጫዎች ማስቀመጫ ለመስራት የወጣው ወጭ እንደኪሳራ የሚታሰብ ይሆናል።

የህዳሴው ግድብ 6450 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ሀይልን ያመነጫል እንደመባሉ ይተከላሉ ተብሎ ለነበሩት 16 ተርባይኖች ተካፍሎ የሚመረት ሀይል ነው የሚል ግንዛቤ አለ። የዋዜማ ምንጭ እንዳሉን ከሆነ ግን የተርባይን ቁጥር መቀነስ ግድቡ 6450 ሜጋ ዋትን እንዳያመነጭ የሚያደርግ ሳይንሳዊ ምክንያት የለም። ግድቡ በ10 የሀይል ማመንጫ ተርባይኖችም በቂ ውሃ እስካለ ድረስ 6450 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክን ማመንጨት ይችላል።

አሁን የሀይል ማመንጫ ተርባይኖች ቁጥር እንዲቀንስ የሚያደርጉ ውሳኔዎች የሚያመጡት ጉዳት ቢኖር አንዱ ከፍተኛ መጠን ያለው ውሀ በግድቡ ውስጥ በሚገባበት ጊዜ ውሀውን በከፍተኛ መጠን ተጠቅሞ ከፍተኛ መጠን ያለው ሀይል የማመንጨት እድልን ማሳጣት ነው።ለዚህ ሲባል የተርባይኖች ቁጥር ከፍ ቢል ይመረጣል።በሌላ በኩል የተቀነሱት ተርባይኖች ይተከላሉ በሚል ለግንባታ የወጣው ወጭ ኪሳራ ነው።

የህዳሴው ግድብ 16 የሀይል ማመንጫ ተርባይኖች ስላሉት 6450 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ያመነጫል ማለት አይደለም ይላሉ የዋዜማ ራዲዮ ምንጭ። አሁን ባለ የአየር ንብረት ሁኔታ ከቀጠለ ግድቡ በ16 የሀይል ማመንጫዎችም በሙሉ አቅሙ ሀይል የማመንጨት ስራ ሊሰራ የሚችለው በአመት ውስጥ ለአራት ወራት ብቻ ነው። ይህም የሚሆነው በውሀ አቅርቦት ምክንያት ነው። ከግድቡ የሀይል ማመንጫ ጋር የሚያያዘው ዋናው ጉዳይ የውሀ ጉዳይ ሲሆን በአካባቢ ጥበቃም ሆነ በዲፕሎማሲው መሰራት ያለበት እዚሁ ላይ ነው ተብሏል።


የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚደረጉ ይህ አይነት ማሻሻያዎች ዲፕሎማሲያዊ እይታቸው ምንድነው ? የሚል ጥያቄ ማስነሳቱም አይቀርም።በዚህ ዙርያ ያነጋገርናቸው ባለሙያ እንዳሉን የተርባይኖች ቁጥር መቀነስ የህዳሴው ግድብ ላይ ከሚያመጣው ተጽእኖ በላይ የግብጽ መንግስት ግድቡን አስመልክቶ የሀገሬን ጥቅም አስከብሬያለሁ በሚል ፖለቲካ ሊገዛበት ይችላል።

በጉዳዩ ላይ የውሀ የመስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ምላሽ እንዲሰጠን ብንጠይቅም እስካሁን ምላሽ አላገኘንም። [ዋዜማ ራዲዮ]