LTV ተሽጧል?
ዋዜማ ራዲዮ- ከቅርብ ቀናት ወዲህ አዋሽ ኤፍ ኤም የተባለ ራዲዮ አዲስ አበባና አካባቢው ስርጭት እያካሄደ ነው።
ስርጭቱ ባለፉት ዓመታት ዛሚ ኤፍ ኤም ሲተላለፍበት በነበረው 90.7 የአየር ሞገድ እየተላለፈ ይገኛል። በርካቶች በኪሳራና በፖለቲካዊ ምክን ያቶች ለመዘጋት ተቃርቦ የነበረው ዛሚ ኤፍ ኤም ለሌላ ወገን ተሽጦ መተላለፉን ሲተነብዩ ስንብተዋል።
የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ስራ አስኪያጅ ጃዋር መሀመድ ይህን ራዲዮ ጣቢያን መግዛቱ ሲነገር ነበር። ጃዋር መሀመድም ስለ አዋሸ ራዲዮ (የቀድሞው ዛሚ) በአዲስ መልክ ስራ መጀመር በማህበራዊ ገፁ አጋርቷል። ይህም የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ አዋሽ ራዲዮን ሙሉ በሙሉ አልያም በከፊል ገዝቶታል የሚለውን ግምት አጠናክሮታል።
ዛሚ የወይዘሮ ሚሚ ስብሀቱና የባለቤታቸው የአቶ ዘሪሁን ተሾመ ንብረት ነው።
በኢትዮጵያ ብሮድካስት ህግ መሰረት ለአንድ ራዲዮ ጣቢያ የተሰጠ የራዲዮ ሞገድ በሽያጭም ሆነ በዝውውር ወደ ሌላ እንዲተላለፍ አይፈቅድም። ጉዳዩን አስመልክተን የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት አነጋግረናል።
የዛሚ ስራ አስኪያጅና ባለቤት አቶ ዘርይሁን ተሾመ
ዛሚ ሬድዩ ጣቢያ ተሸጠ እየተባለ እየተናፈሰ ያለው ወሬ ከእውነት የራቀ ነው። ዛሚ የስም ቅያሬ አርጎ በአዲስ መልክ ስራ ጀምሯል ፣ እስካሁን ለማንም አልሸጥንም ከዚ በፊት ከናሁ ቲቪ ጋር ለሽያጭ ውል የተዋዋልን ቢሆንም ስላልተስማማን በፍርድ ቤት በግልግል ዳኝነት ላይ ነን ያለነው፡፡ ነገር ግን አሁን እየተባለ ያለው ፍፁም ውሸት ነው። ይህን ቃለምልልስ እስከሰጠሁበት ደቂቃ ዛሚ ለማንም አልተሽጠም። ነገ ከነገ ወዲያ የተወሰነ ድርሻ ልንሸጥ እንችላለን፣ ምክንያቱም ቢዝነስ ነው። በአሁኑ ሰአት ሬድዩ ጣቢያችን በአዲስ ስያሜ ፤ በአዲስ አመራር ወደስራ እየገባን ነው እንጂ ምንም የተሸጠ ነገር የለም – ሲሉ ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡
ኤል ቲቪስ ሊሽጥ ነው?
የ ኤል ቲቪ (LTV) ስራ አስኪያጅ አቶ መስፍን ብሩ የሚወራው ወሬ ውሸት ነው፡፡ ከዚህ በላይ በዚህ ጉዳይ ላይ ማውራት አልፈልግም ያሉ ሲሆን የዋዜማ ምንጮች ግን ድርጅቱን ገዛ እየተባለ ያለው አቶ ጃዋር መሀመድ ከሁለት ሳምንት በፊት ሚዲያውን እየጎበኘ እንደ ነበር የተናገሩ ሲሆን በመስሪያ ቤቱ አስተዳደር ምንም የተጣራ ነገር እንዳልተነገራቸው ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡
የብሮድካስት ባለስልጣን ስለጉዳዩ ያውቃል?
የስም ቅያሬ እና ሚዲያን መሸጥ ህጉ ምን እንደሚል ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የኢትዩጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ሀላፊ ዛሚ ሬድዩ የስም ቅያሬውን ያደረገው ለባለስልጣኑ አሳውቆ እንደሆነና ተሸጧል የተባለውን ግን ምንም መረጃ ወደ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እንዳልመጣ ያስረዳሉ። LTV ሆነ ዛሚ ተሽጠዋል የሚለውን በ ሶሻል ሚዲያ ላይ የተመለከትን ቢሆንም ገዝቻለሁም ሸጫለሁም ያለ አካል ወደ ባለስልጣን መስራቤቱ እንዳልመጣ ጠቁመዋል። ህጉ መሸጥን ይፈቅዳል ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ መሸጥ አይቻልም ፣ እቃቸውን መሸጥ እንጂ ፍሪኬንሲውን (የዓየር ሞገድ) መሸጥ አይቻልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አቶ ገብረጊዩርጊስ አብርሀ የኢትዩጵያ ብሮድካስት የኮሚኒኬሽን ዳሬክተር የሚዲያዎቹ ተሸጠዋል ወይ? ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሚያውቀው ነገር ካለ? ብለን ላቀረበንላቸው ጥያቄ ‹‹ስትነግሩኝ ሰማው እንጂ መረጃው የለኝም ለመሸጥም ህጉ አይፈቅድም ›› ብለዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]