ደኢህዴን በሲዳማ ክልል የመሆን ጥያቄ ዙሪያ ያወጣው ግልፅነት የጎደለው መግለጫ ውዝግቡ ገና ከመቋጫው እንዳልደረሰ ጠቋሚ ነው። ምርጫ ቦርድ በበኩሉ ውጥረቱን ረገብ ያደረገና ህዝበ ውሳኔ ለማድረግ የሚቻልበትን ሁኔታ ያብራራ ምላሽ ሰጥቷል። በመጪዎቹ ወራት ከሲዳማ የክልልነት ጥያቄና ህዝበ ውሳኔ ጋር ተያይዞ የሚጠበቁ አወዛጋቢ ጉዳዮችን የዋዜማው ቻላቸው ታደሰ እንደሚከተለው ዝርዝሯል -አንብቡት
ዋዜማ ራዲዮ- ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ተሸክሞት የከረመውን አንድ ሸክም ትናንት (ሐምሌ 9 ቀን 2011 ዓ. ም) ባንድ መግለጫ አቃሏል፡፡ በተለይ ሲዳማ ዞን በተናጥል ክልል መሆኑን ለማወጅ ያስቀመጠው የሐምሌ 11/2011 ዓ. ም የሕዝበ ውሳኔ ቀነ ገደብ ባለመከበሩ ከቦርዱ ጋር ከመወዛገብ ይልቅ፣ የቦርዱን የተራዘመ የጊዜ መርሃ ግብር መቀበሉ እንደ አንድ አወንታዊ ርምጃ መወሰድ ያለበት ነው፡፡ ምናልባትም የሲዳማ ልሒቃንን አቋም ያለዘበው ከደኢሕዴን መግለጫ ይልቅ የቦርዱ ውሳኔ ነው የሚመስለው፡፡ ቦርዱ ከዞኑ አመራሮች ጋር ውይይት ሲያደርግ እንደቆየ መግለጹም ጥሩ የትብብር መንፈስ መፍጠር የሚችል ሆናል፡፡
ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔውን ለማካሄድ የወሰነው የደኢሕዴንን ውሳኔ ካወቀ በኋላ ነው ወይስ ቀድሞ ተዘጋጅቶበት ነበር? የሚለው ጉዳይ ግን ግልጽ አይደለም፡፡ ከይዘቱ ግን በጥድፊያ የወጣ ይመስላል፡፡ ባንድ በኩል ይህን ለማለት የሚስደፍረው ከጥቂት ቀናት በፊት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራንን ተጋብዘው በፌደሬሽኑ ውስጥ አዲስ ክልል የመሆንን አስቸጋሪነት ሲናገሩ መደመጣቸው እና ቦርዱም በጉዳዩ ላይ ባለቀ ሰዓት ጥናታዊ ወረቀቶች እንዲቀርቡ ማድረጉን ስናስብ ነው፡፡ የሆነው ሆኖ የቦርዱ ውሳኔ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ሊገጥማቸው ይችል ከነበረው አጣበቂኝ አትርፏቸዋል ለማለት የሚያስችል ነው፡፡ ሲዳማ በተናጥል ክልልነቱን ቢያውጅ ኖሮ ዐቢይ ከሳምንት በፊት ፓርላማ ላይ በሰነዘሩት ዛቻ ሳቢያ ከባድ ቅርቃር ውስጥ ሊገቡ በቻሉ ነበር፡፡
ነገ ተነገ ወዲያ ግን ሌሎች ቦርዱንና ዞኑን የሚያወዛግቡ ጉዳዮች ብቅ ሊሉ ይችላሉ፡፡ የአዲስ ክልል መፈጠር ለሀገሪቱ የመጀመሪያ እንደመሆኑ ገና ዝርዝር ሥራዎች ሲጀመሩ መሰናክሎች መፍጠራቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በዚህ ጉዳይ ላይ የምርጫ ቦርድ ሥልጣን እስከምን ድረስ ነው? ቦርዱ አዲስ ይመሠረታል በተባለው ክልል ስለሚኖሩ ስለ የሌሎች ብሔረሰቦች ተወላጆች መብት ለመናገር ሥልጣኑ አለው ወይ? በነባር እና በአዲስ ክልል መካከል የሚደረግ ንብረት ክፍፍል የሚመለከተው የሚመለከተው የፌደሬሽን ምክር ቤትን ነው ወይስ ቦርዱን ነው? ለመሆኑስ ምርጫ ቦርድ ለሲዳማ ዞን እና ለክልሉ ያቀረባቸውን የቅድመ ሁኔታ ድምጸት ያላቸው ጥያቄዎች የማቅረብ ሕጋዊ ሥልጣን አለውን? የሚሉ እና ሌሎችም ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ የምርጫ ቦርድንና የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ገለልተኛነትና ተቋማዊ ብቃት፣ ብሎም የአዲሶቹን ተሹዋሚዎች አመራር ብቃት የሚለካ መሆኑ አይቀርም፡፡
ሲዳማ ዞን ክልል ከሆነ ዘርፈ ብዙ አንድምታዎች ይኖሩታል
በመጀመሪያ በሀገር ደረጃ በሕገ መንግስቱ ታሪክ የፌደሬሽኑን ክልሎች ከ9 ወደ 10 በማሳደግ አንድ ጉልህ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ያስከትላል፡፡ አዲስ ክልል በመመስረትም ፈር ቀዳጅ በመሆኑ ሕገ መንግሥቱም ሆነ ኢህአዴግ መራሹ መንግሥት እንዲህ ያሉ መሠረታዊ ጉዳዮችን ማስተናገድ እንደሚችል ማሳያ ይሆናል፡፡ ከሕዝበ ውሳኔ አንጻርም ቀደም ሲል ከተደረጉት የስልጤ እና ቅማንት ማንነት ሕዝበ ውሳኔዎች በኋላ የመጣ ትልቅ ሕዝበ ውሳኔ እንደሚሆን እሙን ነው፡፡ በሌላ በኩል ሲዳማ ክልል መሆኑ በደቡብ ክልል ብቻ የሚወሰን ሳይሆን በተለይ የገናና ብሄረሰብ ዞኖች ላሉባቸው ሌሎች ክልሎችም የሚተርፍ ሊሆን ይችላል፡፡
በኢሕአዴግ ደረጃ ሲታይ ደሞ ሲዳማ በሕጋዊ አግባብ ራሱን የቻለ ክልል ከሆነ እና ቀሪው ደኢሕዴን አንድነቱን አስጠብቆ ከቀጠለ፣ ወደፊት አንድ የሲዳማ ፖለቲካ ድርጅት 5ኛ የኢሕአዴግ አባል ድርጅት ሆኖ ሊቀላቀል የሚችልበት ዕድል አለ፡፡
የሲዳማን አጣዳፊ የክልልነት ጥያቄ በተለይ ሕወሃትና አክራሪ የሚባሉ የኦሮሞ ብሄርተኞች በሰፊው ደግፈዋል፡ በተለይ ሲዳማ ክልል ሀዋሳን ጠቅልሎ የሚወስድ ከሆነ፣ የኦሮሞ ብሄርተኞች አዲስ አበባ ላይ ለሚያነሱት የባለቤትነት ጥያቄ እንደ ጥሩ እርሾ እንደሚያዩት ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ይህን አቋም ግን ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ እና ከኢህአዴግ በተጻራራ እንደመቆም አድርገው የሚወስዱት ወገኖች አሉ፡፡ ሆኖም ዐቢይ ሲዳማ እና መሰል አዳዲስ ክልሎች መበራከታቸውን እንደ ፖለቲካ፣ ሕጋዊ እና አስተዳደራዊ ስጋት ያዩታል ወይስ ይፈልጉታል ? የሚለውን ውሎ አድሮ መታዘብ ሳይሻል አይቀርም፡፡
የህወሓት አመራር ከደቡብ የሚነሡ የክልልነት ጥያቄዎችን ውድቅ ሲያደርግ ከርሞ አሁን የእነርሱ ደጋፊ ሆኖ ብቅ ማለቱ፣ ከመርሕ ይልቅ በኢሕአዴግ ውስጥ ያለው ሽኩቻ ውጫዊና ታክቲካዊ ቅጥያ ተደርጎ ሊታይ የሚችል ነው። ለጠቅላይ ሚንስትሩ ራስ ምታት ለመሆን ግን የሚያንስ አይመስልም።
በደኢሕዴን ደረጃም ስናየው በርካታ የሲዳማ ልሂቃን ከንቅናቄው ሲወጡ ደኢሕዴን ይዳከማል የሚል ስጋት ይፈጥራል፡፡ ወትሮም የሲዳማ ልሂቃን በደቡብ ክልል መንግስትም ሆነ በደኢሕዴን መዋቅር ቁልፍ ተዋናይ እንደነበሩ የሚታወቅ ነው፡፡ የሲዳማ የፖለቲካ ልሒቃን በራሳቸው ተጽዕኖ መብታቸውን ማስከበራቸው፣ ደኢሕዴንም ሆነ የክልሉ መንግስት ደካማ ሆነው እንዲታዩ የሚያደርግ ነው፡፡
ሌሎች ዞኖችም ጥያቄያቸውን አጠንክረው ለመግፋት እርሾ ስለሚሆንቸው፣ የደኢህዴን ከባድ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል፡፡ እንደ ደቡብ ኦሞ፣ ካፋ እና ቤንች ማጂ ያሉት ዞኖች በቆዳ ስፋት ከሲዳማ ዞን የሚልቁ ናቸው፡፡ የክልሉ መንግሥትም ገና ወደፊት ጠንክረው የሚመጡ አዳዲስ የክልልነት ግፊቶችን በድርጅታዊ አግባብ መቀልበስ የሚችልበትን መንግሥታዊ መዋቅር ያጣል፡፡ ደኢህዴን አካሄድኩት የሚለው ሳይንሳዊ ጥናት እንደሆነ ክልል የመሆንን ሕገ መንግሥታዊ መብት ሊደፈጥጥጥ አይችልም፡፡ እነዚህ ስጋቶችም የሰሞኑን የማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫውን የተድበሰበሰ እንዲሆን ያስገደዱት ይመስላል፡፡ ለዚህም ሳይሆን አይቀርም፣ ሲዳማ ክልል እንዲሆን ስለመወሰኑ በይፋ ደኢሕዴን ያልገለጸው፡፡ ይሄን አካሄድ መምረጡ ግን በሲዳማ ብሄርኞች ላይ ቅሬታ በመፍጠር ግንኙነቱን ይጎዳ እንደሆን እንጅ የሚጠቅመው አይደለም፡፡
በክልል ደረጃ የክልሉ አስተዳደራዊ አወቃቀርና አስተዳደራዊ ወሰኖችም ይቀየራሉ፡፡ በቅርብ ጊዜ ወዲህ ባንዳንድ ዞኖች የክልልነት ጥያቄዎችን ወደፊት የሚገፉ፣ ከደኢሕዴን ውጭ የሆኑ እንደ ዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ ያሉ የብሄረሰብ ፖለቲካ ድርጅቶች እየተፈጠሩ ነው፡፡ የሲዳማ ክልል መሆን ደሞ እንዲህ ያሉ ድርጅቶች በየዞኑ እንዲበራከቱ እርሾ የመሆን እድል አለው፡፡ የብሄረሰብ ፖለቲካ ደርጅቶች መበራከት ደሞ ዞሮ ዞሮ በቅድመ-ደኢሕዴን የነበረውን ሁኔታ ይመልሳል፤ ደኢህዴንም ሊፈራርስ የሚችልበትን እድል ያሰፋል፡፡
ሌላው የለውጡ ከባድ አሻራ የሚያርፈው ጌዲዖ ዞን ላይ ይሆናል፡፡ ሲዳማ ዞን ክልል ከሆነ ጌዲዖ ዞን ሙሉ በሙሉ ከደቡብ ክልል ስለሚቆረጥ ዕጣ ፋንታው ስጋት ላይ ነው፡፡ የጌዲዖ ቡና ሃብት አማላይ ከመሆኑ አንጻር ሲታይ፣ ምናልባትም የሲዳማ እና ኦሮሞ ብሄርተኞች ሊቀራመቱት ያሰፈስፉ ይሆን? የሚለው በቅርብ የምናየው ይሆናል፡፡ ይሄ ሁኔታ ደሞ ላለፉት ዐመታት በጅምላ መፈናቀል የተጎዳውን የጌዲኦ ሕዝብ ለሌላ ከባድ ሰቆቃ ማጋለጡ አይቀርም፡፡
አሁን ባለው አደረጃጀት ማንኛውም ብሄረሰብ አንጻራዊ ህልውናውን ማስጠበቅ የሚችለው የራሱ አስተዳደራዊ አከላለል ሲኖረው ስለሆነ በብሄረሰባዊ ማንነቱም ላይ ከእነ አካቴው የመጥፋት አደጋ ይደቀንበታል፡፡ ላሁኑ ደኢሕዴን ለጌዲዖ ዞን እና ለብሄረሰቡ ምን መፍትሄ እንዳሰበ ገና የታወቀ ነገር የለም፡፡ በርግጥ ፍቱን መፍትሄ መስጠትም አስቸጋሪ ይመስላል፡፡ ምናልባት ዞኑ በአዲሱ ሲዳማ ክልል ስር ተዋቅሮ፣ ቅማንቶች በአማራ ክልል እንዳገኙት ያለ የብሄረሰብ ዞን አስተዳደር ካገኘ ግን አንድ አማራጭ ሊሆንለት ይችላል፡፡
የሀዋሳ ዕጣ ፈንታ
የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ አጉልቶ ያወጣው አንዱ ጉዳይ የሀዋሳ ከተማ ዕጣ ፋንታ ነው፡፡በኢሕአዴግ፣ በክልሉና ደኢሕዴን ደረጃ ቀድሞ መሞከር የነበረበት ድርድርና ውይይት ባለመደረጉ አሁን ሀዋሳ የውዝግብ ማዕከል የምትሆንበት ጊዜ ደርሷል፡፡ ምርጫ ቦርድ በመግለጫው “የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች በሕዝበ ውሳኔው የሲዳማ ክልልነት የሚያረጋግጥ ከሆነ…” በማለት ዞኑ እና ክልሉ የሃብት ክፍፍል ስምምነት አድርገው እንዲያሳውቁት ጠይቋል፡፡
እዚህ ላይ የከተማዋ ሕዝበ ውሳኔ ቆጠራ ውጤት ራሱን ችሎ እንደሚታይ የሚጠቁም ነው፡፡ ክልልነቱን ብታረጋግጥስ ደቡብ ክልልም ሆነ ሲዳማ ዋና መቀመጫቸው አድርገዋት ይቀጥላሉ ወይስ ምን ይሆናል? የሚል ጥያቄ ይከተላል፡፡ አንድን ከተማ ሁለት ክልሎች ዋና መቀመጫቸው ማድረጋቸው ደሞ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ክልሉ ዋና መቀመጫውን ወደ ሌላ ከተማ ካዞረ ደሞ ዕጩ ዋና ከተሞች እነማን ይሆናሉ? የሚለው ትኩረት ሳቢ ነው፡፡ ሶዶ እንዳይሆን ዎላይታ ዞን ራሱ ክልል ለመሆን ጠይቋል፡፡ አርባ ምንጭም እንዳትሆን ጋሞ ዞን ክልል ለመሆን ወስኗል፡፡ ድምጻቸው ጎልቶ የሚሰማው የሲዳማ ልሒቃን እንደሆኑ አሁን ባላቸው አቋም ከሀዋሳ ንቅንቅ እንደማይሉ መገመት ይቻላል፡፡
የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ሲዳማ ክልል መሆኑን ካልደገፉስ? የሚል ጥያቄም መነሳት አለበት፡፡ ፍሬ ነገሩን ለህገ ባለሙያዎች ትተን፣ መግለጫውን እንደ ወረደ ስናየው ግን የከተማዋ ነዋሪዎች የሲዳማን ክልልነት ካልደገፉ፣ ቀሪው የሲዳማ ዞን ሕዝብ ቢደገፈው እንኳ ከተማዋ ለውጤቱ ተገዥ አትሆንም የሚል አንድምታ ያለው ነው የሚመስለው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዞኑ እና ክልሉ መካከል ዘርፈ ብዙዎቹ ድርድሮች በተባለው ጊዜ እና በስምምነት መፈጸም መቻላቸውንም ከወዲሁ ለመናገር አዳጋች ነው፡፡
ቦርዱ በመግለጫው የሕዝበ ውሳኔ ውጤት ከታወቀ በኋላ ስለ አናሳዎች መብት አጠባበቅ አንስቷል፡፡ ሲዳማ ዞንም ለአናሳ ቡድኖች መብት ሕጋዊና አስተዳደራዊ ማዕቀፍ አዘጋጅቶ እስከ ሐምሌ 19 እንዲያሳውቅ አሳስቧል፡፡ በዞኑ እና በሀዋሳ ያሉ የሌላ ብሄረሰብ ተወላጆች ግን ከሕዝበ ውሳኔው በፊትም የደኅንነት ስጋቶች እንዳሉባቸው ግምት ውስጥ መግባት ያለበት ነው፡፡
እንደሚታወቀው ባለፉት ወራት በከተማዋና በሌሎች የሲዳማ ዞን ከተሞች ደም አፋሳሽ ማንነት-ተኮር ግጭቶች ተቀስቅሰዋል፡፡ ግጭቶቹም የሌላ ብሄረሰብ ተወላጅ የሆኑትን በየከተማዋ ነዋሪዎች በተለይም የዎላይታና ጉራጌ ብሄረሰብ ተወላጆችን ከባድ ስጋት ውስጥ ጥለዋቸው ነው የከረሙት፡፡ የክልልነት ጥያቄው የፈጠረው መንፈስም የከተማዋን ጸጥታ ጎድቶታል፡፡ በሌላ በኩል ከተማዋ የሲዳማ ዞን መቀመጫ ከመሆኗም በላይ፣ የሲዳማ ኢጀቶዎች (ወይም ወጣቶች) የሲዳማን ክልልነት ለማወጅ ተከታታይ እና የተደራጀ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉባት የቆየች ከተማ በመሆኗ የሌሎች ብሄረሰብ ተወላጆች ድምጽ ሙሉ በሙሉ ተውጧል ማለት ይቻላል፡፡ ተራ ዜጎች ይቅርና የክልሉ ገዥ ፓርቲ ደኢሕዴን እንኳ በከተማዋ ለመሰብሰብ የደኅንነት ስጋት ስላደረበት በአዲስ አበባ ነው ሲሰበሰብ የከረመው፡፡
የሌላ ብሄረሰብ ተወላጅ የሆኑት ነዋሪዎቿ በሕዝበ ውሳኔው በነጻነት ሊሳተፉ የሚችሉበት ዕድል አለ ወይ?
ይህን የምንለው የከተማዋ የሌላ ብሄረሰብ ተወላጆች ከሲዳማዎች በቁጥር ብልጫ ያላቸው እንደመሆናቸው፣ ከአዲሱ ሲዳማ ክልል ይልቅ በነባሩ ደቡብ ክልል ውስጥ መቀጠልን እንደሚመርጡ ሰፊ ግምት ስላለ ነው፡፡ ለዚህም ነው የእነዚህን ወገኖች ድምጽ መስጠት የሲዳማ ብሄርተኞች ይፈልጉታል ተብሎ የማይጠበቀው፡፡ በድፍረት ድምጽ የሚሰጡ ካሉም ውጤቱ ከታወቀ በኋላ የደኅንነት ዋስትና እንዳያጡ ስጋት ሊያድርባቸው ይችላል፡፡ ምርጫ ቦርድ እስካሁን ሲሰራበት እንደነበረው የሕዝበ ውሳኔውን ድምጽ ቆጠራ ውጤት በብሄረሰብ ማንነት ከፋፍሎ መገለጹ የማይቀር ነው፡፡ እንደዚያ ከሆነ ከውጤቱ በኋላ “እናንተ ናችሁ የሲዳማን ክልልነት ተቃውማችሁ ድምጽ የሰጣችሁ” የሚሉ አደገኛ ፍረጃዎችንና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ማስከተሉ የማይቀር ነው፡፡ የክልሉ መንግሥት ደሞ በዚህ ቁመናው ከቀጠለ የእነዚህን ዜጎች ስጋት መቅረፍ መቻሉ በጣም አጠራጣሪ ነው፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]