ዋዜማ ራዲዮ- አምስት ሚሊየን ብር (ከ173 ሺህ ዶላር በላይ) የሚያወጣና ወደ ቤልጂየም ለመላክ እየተጓጓዘ ያለ ቡና በኦሮምያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ተዘረፈ።
ኩሩ ኢትዮጵያ (Kuru Ethiopia Coffee Development PLC) በተባለ ኩባንያ ወደ ቤልጂየም ለመላክ መነሻው ከአለም ገና ካለ መጋዘን በተሳቢ መኪና በሁለት ኮንቴይነር ተጭኖ ወደ ጅቡቲ ወደብ እየተጓጓዘ ያለ 39.9 ሜትሪክ ቶን ቡና በኦሮምያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ሎሜ ወረዳ ወደ ሶደሬ መዝናኛ መሄጃ መንገድ ላይ ዝርፊያ ተፈጽሞበታል።
ድርጊቱ የሆነው ሰኞ ሌሊት ለማክሰኞ አጥቢያ ነው። ዝርፊያ የተፈጸመበት ተሽከርካሪ የታርጋ ቁጥሩ 3-25301/06783 ሲሆን በተሳቢ መኪና በሁለት ኮንቴይነር 39.9 ሜትሪክ ቶን ቡና ጭኖም ነበር። የቡናው አይነትም ደረጃ ሁለት የታጠበ ሲዳሞ ደረጃ ሁለት ሲሆን ከ173 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ ዋጋ እንዳለው ታውቋል።ዝርፊያውን የፈጸሙት ግለሰቦች መሳርያ የታጠቁና በተሽከርካሪም የታገዙ ናቸው ። ዝርፊያው ሲፈጸምም ቡናውን እያጓጓዘ ባለው ሾፌር ላይ ድብደባ ደርሶበታል። (ዘገባው ከታች ይቀጥላል)
ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ ቡና ጫኝ ተሽከርካሪው ከሞጆ ጀምሮ ለአንድ ለሚያውቀው ሰው ሊፍት ሰጥቶ እንደነበረና አዳማ ከገቡ በሁዋላ ሹፌሩ ለመኝታ ፍለጋ ከመኪናው ሲወርድ ዝርፊያ ፈጻሚዎቹ ቪትስ መኪና ውስጥ አስገድደው አስገብተዋቸዋል።ድብደባው የተፈጸመው ሌሊቱን እዚሁ መኪና ውስጥ ነው ተብሏል።
ዝርፊያው ከተፈጸመ በሁዋላም ሁለት ኮንቴይነር የጫነውን መኪና ለተወሰኑ ሰአታት በድርጊቱ ፈጻሚዎች የተሰወረ ሲሆን በፖሊሶች ክትትል ቆይቶ ማክሰኞ ቀን ተገኝቷል። የድርጊቱ ፈጻሚዎች የተጠቀሙባት ቪትስ መኪናም ተገኝታለች።
ቡና የጫነው ተሽከርካሪ ሲገኝ በኮንቴይነሮቹ ውስጥ ሀምሳ ኩንታል ያህል ቡና ውስጡ ተገኝቷል። ስለጉዳዩ ማብራሪያ የጠየቅነው የኣአካባቢው ፖሊስ ድርጊቱ መፈፀሙን አምኖ ቡጉዳዩ ላይ ዝርዝር ማብራሪያ መስጠት እንደሚቸገር ነግሮናል። በጉዳዩ ላይ የተጠረጠረ አንድ ግለሰብም መያዙን ሰምተናል።
ቡና ላኪው ድርጅት በበኩሉ ፖሊስ ወንጀለኞቹን ለመያዝ ብሎም ቤልጂየም ላለው ገዢ ስለወንጀሉ ድርጊት ማስረጃ የሚሆን ማረጋገጫ አልሰጥም በማለት እንዳልተባበራቸው ይናገራሉ። ድርጊቱን በፖሊስ ማስረጃ ካላቀረቡ አመስት ሚሊየን ብር ኪሳራውን በውጪ ምንዛሪ ለመክፈል እንደሚገደዱም ስጋት አላቸው። ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ምርት ላይ እንዲህ አይነት ወንጀል መፈጸሙ የሀገሪቱን የንግድ ታማኝነት ያጠፋል።
ዋዜማ በተቻለ አዳዲስና ያልተሰሙ ዜናዎች የምታገኙበት ምንጭ ነው። ከታች በድምፅ የተሰናዳ ዝርዝር ዘጋባ አለን። አድምጡት።