ዋዜማ ራዲዮ- ከ3 ዓመት በፊት በርካታ ህጻናትን አፍነው የወደሱትና በርካታ ሰዎችን የገደሉት የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በድጋሚ በተደራጀ ሁኔታ ወደ ጋምቤላ መግባታቸው ተሰምቷል፡፡ ከየካቲት ወር ጀምሮም ጥቃት ሲፈፅሙ ነበር፡፡
በ2008 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን ካዘኑባቸውና በብሔራዊ ሀዘን ጭምር ካሳለፉባቸው ክስተቶች አንዱ በጋምቤላ ክልል የተፈፀመው ዘግናኝ ጥቃት ነበር፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ህጻናት ከወላጅ ጉያ ተነጥለው ታግተዋል፤ ብዙዎችም ተገድለዋል፡፡ የጥቃቱ አድራሾች ደግሞ አሁንም ድረስ ሊረሱ ያልቻሉት የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ- ደቡብ ሱዳን ድንበር የሚኖሩት እነዚህ ጎሳዎች ከማህበረሰባቸው ውጪ ባሉ ቦታዎች ተንቀሳቅሰው ከብት መዝረፍን ወይም ህፃናት ማገትን እንደቆየ ልማድና ጀብድ እንደሚመለከቱት የጋምቤላ ክልል ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ የጋምቤላ ክልልን እና ሙርሌዎችን የሚለየውን አኮቦ ወንዝ እየተሻገሩ መግባት ልማዳቸው ሆኖም ቆይቷል፡፡ ለዚህም ይመስላል ከ2008ቱ ጥቃት በኋላ እጅና ጠብ-ምንጃቸው ያልቦዘነው፡፡ በ2009 ወደ ጋምቤላ ክልል በመግባት የ18 ዜጎችን ህይወት አጥፍተዋል፡፡
በ2010 የካቲት ወር ወደ ክልሉ ያቀኑት የቀድሞው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመም ጉዳዩ ለክልሉ ነዋሪዎች አስጨናቂ መሆኑን አውስተው መንግስት በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰራ ቃል ገብተው ነበር፡፡ ችግሩ ግን በየአመቱ እየፈጠጠ መጥቷል፡፡ ዘንድሮም ከየካቲት እስከ መጋቢት አጋማሽ ባሉት ጊዜያት የሙርሌ ታጣቂዎች ተደጋጋሚ ጥቃት ፈፅመዋል፡፡
የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የአስተዳደርና ፀጥታ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ጎርዲን ኮኤንግ በተለይ ለዋዜማ እንደተናገሩት ከየካቲት ወር ጀምሮ ታጣቂዎቹ ወደ አኮቦ ወረዳ በመግባት 130 ከብት እና 204 ፍየሎች ዘርፈዋል፡፡ በተጨማሪም በመክዌ ወረዳ 1 ህፃን አግተው መዉሰዳቸውን ሀላፊው ተናግረዋል፡፡ በአኝዋ ዞን ጆር ወረዳ ባሉት ቶ ቁጥር 1 እና 2 ቀበሌዎች ደግሞ ከክልሉ ሚሊሻ ጋር ተኩስ ገጥመው ሁለት ታጣቂዎቻቸው ተገድለውባቸዋል፡፡
በቅርቡ ደግሞ ደቡብ ሱዳን ካለው ፒቦር ወረዳ ካሉ የአስተዳደር ሰዎች የመጣው መረጃ የክልሉ የፀጥታ ሀላፊዎች ጉዳዩን የበለጠ ትኩረት እንዲሰጡት አድርጓል፡፡ መረጃው የሙርሌ ታጣቂዎች ተደራጅተው ድንበር ለማለፍ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ድንበር አልፈው እየመጡ ያሉ ታጣቂዎችን ብዛት እርግጠኛ ሆኖ መናገር ባይቻልም እማኞች ቁጥሩ ከ2 ሺህ የማያንስ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡
ጥቃቱ በዋናነት ሊፈፀምበት ይችላል የተባለው በአኝዋ ዞን ጆር ወረዳ እና በሌሎችም ወረዳዎች ያሉ የፀጥታ መዋቅሮች የጥንቃቄ መልዕክት እንደተላለፈላቸውም ታውቋል፡፡ የ2008ቱን ጥቃት ከሀይል ክፍተት ጋር የተገናኘ መሆኑን የሚያስታዉሱት የክልሉ ነዋሪዎች የፌደራሉ መከላከያ ሀይል ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥላቸው ይፈልጋሉ፡፡ የክልሉ የአስተዳደርና ፀጥታ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ጎርዲን ኮኤንግ የሙርሌ ጎሳዎች ጥቃት ከአቅማችን በላይ ሊሆን ከቻለ የመከላከያን ድጋፍ እንጠይቃለን ሲሉ ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ [ተጨማሪ የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ]