Birtukan Midkesa

ዋዜማ ራዲዮ- ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድን እንዲመሩ መሾማቸው በሀገሪቱ የፖለቲካ ሽግግር አዲስ ምዕራፍ ነው። የግለሰቧ የጀርባ ታሪክ ለህግ ልዕልና ያላቸው ፅናትና በህዝብ ዘንድ ያላቸው አመኔታ ሹመቱን እንደ ትልቅ እርምጃ እንድንወስደው ግድ ይሉናል። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በንግግራቸው ተሹዋሚዋ ካሁን ቀደም የመሯቸውን ተቃዋሚ ድርጅቶች ከመጥቀስ ተቆጥበዋል፡፡ እስረኛ የነበሩ መሆናቸውንም እንዲሁ… ምናልባት የዕጩዋን ማንነት ፖለቲካዊ ገጽታ ላለመስጠት ፈልገው ሊሆን ይችላል፡፡

ሌላው ትኩረት የሳበው ነገር የፓርላማ አባላቱ ዕጩዋ ከፖለቲካ ፓርቲ በይፋ ስለመሰናበታቸው ደጋግመው ማንሳታቸው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ ግን በደፈናው ዕጩዋ ከፓርቲ አባልነት እንደለቀቁ አረጋግጠናል ከማለት ውጭ መቼ እንደለቀቁ ጊዜውን አልጠቀሱም፡፡ በምን አኳኋን እንደተጣራም አላብራሩም፡፡

የምርጫ ቦርድ አዋጅ የቦርዱ ሰብሳቢ እና ምክትሉ የሚሾሙት ከቦርዱ አባላት መካከል እንዲሆን ስለሚያዝ ሰብሳቢዋ በተናጥል መሾማቸው ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህን ያደረጉት ምናልባት ወይዘሪት ብርቱካን አዋጁን በማሻሻሉ ሂደት ቁልፍ ሚና እንዲጫወቱ ስለፈለጉ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይችላል፡፡ ጉዳዩ የሕግ ጥሰት አለበት ወይስ የለበትም? የሚለውን ለሕግ ባለሙያዎች እንተወው፡፡

በጎ ዕድሎች

ሕዝቡ በፖለቲካዊ ተሃድሶው ተስፋ የጣለበት ወቅት መሆኑ እና ሀገሪቱ ፖለቲካዊ ማሻሻያዎች እየወሰደች መሆኗ መልካም ዕድሎች ይሆኑላቸዋል፡፡

ምንም እንኳን ቦርዱ ወደፊትም አንዳንድ የማሻሻያ ሃሳቦችን ማቅረብ ቢችልም አሁን ማቋቋሚያ አዋጅ 532/1999 በመሻሻል ሂደት ላይ መሆኑ ሌላው ተስፋ ሰጭ ጅምር ነው፡፡ ገዥው ፓርቲም ከተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ላይ እየተወያየ መሆኑም እንዲሁ… መንግሥት አዋጆቹን እስከምን ድረስ ያሻሽለዋል? ለሚለው ጥያቄ ግን አሁን ከመላ ምት ያለፈ መልስ መስጠት አይቻልም፡፡ ላሁኑ ቦርዱ ወደ ኮሚሽን ይደግ፤ የራሱን በጀት ያስተዳድር የሚሉ ሃሳቦች እየተነሱ ነው፡፡ እናም በተለይ የቦርዱ አዋጅ ማሻሻያ ጥልቀት ለአዲሷ ሰብሳቢ ፈተና ወይም ዕድል ይዞላቸው የሚመጣ ነው የሚሆነው፡፡

እስካሁን ባለው አሰራር ግን የቦርዱን ከፍተኛ አመራር አባላት ዕጩዎች የሚያቀርቡት አራቱ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መሆናቸው የታወቀ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ ግን በንግግራቸው በቦርዱ አባላት ምልመላ ወይዘሪት ብርቱካን ቁልፍ ሚና እንደሚኖራቸው ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ ተጽዕኖ የመፍጠር ዕድላቸው አናሳ ቢመስልም ተግባራዊ ከሆነ ግን ሌላ ቦርዱ  ተዓማኒነት ሰዎች እንዲመራ የማድረግ ዕድል ይፈጥርላቸዋል፡፡

ቀደም ሲል በፍትህ ሥርዓቱ እና በተቃዋሚነት ፖለቲከኛነት የነበራቸው ሚናም የሀገሪቱን የምርጫ ፖለቲካ እና መዋቅር እንዲያውቁ ስላደረጋቸው ጥሩ አቅም እንደሚሆናቸው ይገመታል፡፡

ከበድ ያሉ ፈተናዎች

መንግሥት ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ ከማካሄዱ በፊት ሰፊ እና ምቹ ሀገር ዐቀፍ የፖለቲካ ምህዳር ይፈጥራል ወይ? ፍቃደኝነቱ እና ዝግጁነቱስ በትክክል አለው ወይ? የሚለው አንዱ ፈተና ነው፡፡ መቸም የፖለቲካ ምህዳሩ ካለሰፋ ምርጫ ቦርድ የቱንም ያህል ጠንካራ እና ገለልተኛ ቢሆን ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ አስቸጋሪ ነው የሚሆንበት፡፡ ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ እንደሆነ ለምርጫ ቦርዱ ገለልተኛ እና ብቁ ሃላፊ በመሾም ብቻ ሊረጋገጥ አይችልም፡፡ የገዠው ፓርቲ እና የበታች አመራሮች መልካም ፍቃደኛነት፣ የጸጥታ ሃይሎችን ገለልተኛነት፣ ጠንካራ ሜዲያ እና የፕሬስ ነጻነት መስፈኑ፣ የሕግ አውጭ እና ፍትህ አካላት ጥንካሬ፣ የሲቪል እና ሙያ ማህበራት ንቁ ተሳትፎ የመሳሰሉ ነገሮችን ሁሉ ይፈልጋል፡፡

ኢሕአዴግ ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ ለማድረግ ምን ያህል የፖለቲካ ፍቃደኛነት እንዳለውም አፋዊ አንጅ በተግባር ገና አልተፈተነም፡፡ ላሁኑ ግን ተጨባጭ ሁኔታው አመች የሆነለት ይመስላል፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች አሁንም ደካማ እና የተበታተኑ ናቸው፤ ከውጭ የገቡ የፖለቲካ ቡድኖችም የረባ እንቅስቃሴ አልጀመሩም፡፡ ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ተሃድሶ እየተገበረ መሆኑንም ሕዝቡ እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች አምነውለታል፡፡ እናም ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አካሂጄ በዚያውም ምርጫውን አሸንፋለሁ፤ ይሄም ባንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ይሆንልኛል ብሎ ያሰላ ይመስላል፡፡

የኢሕአዴግ እና መንግሥት መዋቅር መቀላቀል ሌላኛው የምርጫ እንቅፋት ነው፡፡ ይሄን መዘበራረቅ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሊፈቱት ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም እስካሁን ግን ያልጀመሩት የቤት ስራ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ የምርጫ ተቋሞች እና ምርጫው ከገዥው ፓርቲ ጣልቃ ገብነት ሊድኑ የሚችሉት ደሞ ሁለቱ መዋቅሮች ሲለያዩ ብቻ ነው፡፡ ይሄ ሳይሆን ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ የሚቻል አይመስልም፡፡ አሁን ጥያቄው ኢሕአዴግ ለዚህ ፖለቲካዊ እና መዋቅራዊ ችግር በመጭዎቹ ሁለት ዐመታት መፍትሄ አለው ወይ? ነው፡፡

አሁን ተዓማኒ፣ ገለልተኛ እና ጠንካራ ምርጫ ተቋም የመመስረቱ ነገር በወይዘሪት ብርቱካን ትክሻ ላይ ወድቋል፡፡ መቸም ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ ሳይወስኑ ይሄን ሃላፊነት ይረከባሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ የምርጫ ተቋሙን ገለልተኛ እና ተዓማኒ የማድረግ ጉዳይ ግን በእሳቸው ብቻ የሚወሰን አይደለም፤ በዋነኛነት የመንግሥትን ፍቃደኛነት ይጠይቃል፡፡

ቦርዱን ተቋማዊ ማድረግም ከበጀት ጋር የሚያያዝ በመሆኑ አንድ ፈተና ይደቅንባቸዋል፡፡ የምርጫ ቦርዱን ዋነኛው የዕለት ተለት አስፈጻሚ አካል ማለትም ሴክሬታሪያቱን እንደገና ማዋቀር እና እስከ ክልል እና የበታች መዋቅሮች ድረስ ጽህፈት ቤቶቸቹን ማዋቀር የእሳቸው ፋንታ ነው፡፡ በቦርዱ ሥልጣን ስር ያሉ የምርጫ ደንቦችን እና ሕግጋትን ማሻሻልም እንዲሁ…

ሌላው ፈተና ከዋና ሰብሳቢው ውጭ ያሉ ለቦርዱ የሚሾሙለት አመራር አባላት ሚና የይስሙላ ሆኖ መቆየቱ ነው፡፡ ቦርዱ አስቸጋሪ ፈተናዎች ተጋርጠውበት በነበረ ጊዜ እንኳ የቦርዱ አመራር አባላት እንደምን የጋራ ውሳኔ እንደሚሳልፉ በቅጡ ሳይታወቅ ነው የኖረው፡፡ የስብሰባ ሥርዓታቸው ምንድን ነው? ቃለ ጉባዔያቸው ምን ይላል? ሕጉ በሚፈቅድላቸው ጉዳዮች ሁሉ ውሳኔ ያሳልፋሉ ወይንስ ጉዳዮቹን ለዋና ሰብሳቢው ብቻ ይተዋቸዋል? በምን መልኩ ነው ውሳኔ የሚያሳልፉት? የሚሉት ጥቄዎች የተሟላ መልስ ማግኘት አይቻልም፡፡ በሙሉ ድምጽ የሚወስኑ ይሁን አይሁንም በቅጡ ተገልጾ አያውቅም፡፡ የተጣለባቸውን ከባድ ሃላፊነት ለመወጣት በመካከላቸው ምን የሥልጣን ክፍፍል እንደሚያደርጉ ግልጽ ሆኖ አያውቅም፡፡ እስከዛሬ በተደረጉ ሀገር ዐቀፍ ምርጫዎች ሁሉ አባላቱ አንዴ ከተሾሙ በኋላ በመገናኛ ብዙኻን እንኳ በቅጡ ቀርበው ሲናገሩ መስማት የተለመደ አይደለም፡፡ ለሜዲያም በጣም ሩቅ ናቸው፡፡

እናም አዲሷ የቦርዱ ሰብሳቢ እና የሚመሩት ሴክሬታሪያት ስኬታማ ሊሆኑ የሚችሉት ሌሎቹ ከፍተኛ አመራሮች ሥልጣን ከተጋሩ፣ ሃላፊነትን በብቃት መወጣት ከቻሉ፣ ለሕዝብ እና ባለ ድርሻ አካላት ቅርብ ከሆኑ እና ተጠያቂነትን መቀበል የሚችሉ ከሆኑ ብቻ ነው፡፡

አምና መካሄድ የነበረበት የአካባቢ እና ከተማ አስተዳደሮች ምርጫ በያዝነው ዐመት ከተካሄደ ምርጫውን ነጻ እና ፍትሃዊ አድርጎ ማሳየት የመጀመሪያው ፈተናቸው ይሆናል፡፡ በሀገራችን የምርጫ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ዋነኛ ትኩረት ማዕከሉ ላይ ሆነ እንጅ የአካባቢ ምርጫዎች ዋነኛ የዲሞክራሲያዊ ምርጫ መለኪያዎች ናቸው፡፡ ለዚህ ምርጫ ካሁኑ ገለልተኛ የምርጫ አስፈጻሚዎችን መመደብ ዋነኛ ሥራቸው ነው የሚሆነው፡፡ ይሄ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊ እና ተወዳዳሪነት የሚታይበት መሆን ከቻለ ግን እሳቸው የሚመሩት ቦርዱ ከሁለት ዐመታት በኋላ ለሚያስፈጽመው ሀገር ዐቀፍ ምርጫ ጥርጊያ ይፈጥርለታል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሀገሪቱ እየታየ ያለው መፈናቀል እና ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች ካልተቀረፉ የአካባቢ ምርጫን አስቸጋሪ ያደርግባቸዋል፡፡

ሌላው የቦርዱ ፈተና በቅርብ እየበዛ ከመጣው የክልልነት ጥያቄ ጋር ይያያዛል፡፡ በቅርቡ የሲዳማ እና ካፋ ዞን ምክር ቤቶች ክልል ለመሆን ወስነዋል፡፡ እነ ወላይታ እና ከምባታ ዞኖችም ተመሳሳይ ውሳኔ እንደሚያሳልፉ ከወዲሁ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ደሞ አንድ የብሄረሰብ ዞን ክልል ለመሆን ከወሰነ በኋላ መንግሥት ማድረግ የሚችለው ከሁለት ዐመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ ማካሄድ ስለሆነ ምርጫ ቦርድ ከክልል መንግሥታት ጋር በመተባበር ሕዝበ ውሳኔውን የማካሄድ ሃላፊነት አለበት፡፡ ሕዝበ ውሳኔ የምርጫን ያህል ውስብስብ ባይሆንም ያው በድምጽ መስጫ ሳጥን ነጻ እና ፍትሃዊ በሆነ ሁኔታ የሕዝብ ፍቃድ የሚገለጥበት በመሆኑ ቦርዱ ቢያንስ በሁለት ዐመታት ውስጥ ድርብ ድርብርብ ሥራ ይጠበቅዋል ማለት ነው፡፡

በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ መሠረት የተመዘገቡ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሕን ተከትለው እየሰሩ ስመሆኑ ማረጋገጥ የምርጫ ቦርዱ ሥልጣን ነው፡፡ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች ደሞ ሥራ ጊዚያቸውን ባጠናቀቁ አመራሮች ምትክ የተተኩ ሰዎችን የማሳወቅ፣ የኦዲት ክፍተት እና ቋሚ አድራሻ የሌላቸው መሆኑ እና ጠቅላላ ጉባዔ በጊዜው የማካሄድ ችግር ተደጋግሞ የሚነሳባቸው ናቸው፡፡ በዚህ ሳቢያ ብቻ ከሁለት ዐመት በፊት ቦርዱ የ14 ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶችን ምዝገባ ፍቃድ መሰረዙ ይታወሳል፡፡ አዲሷ ሰብሳቢ ደሞ በዚህ ረገድ ጠንካራ ቁጥጥር የማድረግ እና ምናባትም በርካታ የስም ብቻ ድርጅቶችን ሕልውና ሊያጠፉት እንደሚችሉ ከወዲሁ መገመት ይቻላል፡፡ መቸም ከ60 በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች መኖራቸው አንዱ የሀገራችን ወለፈንድ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ስለ ምርጫ ውድድር ሲነሳ አንዱ ቦርዱ መፈተሸ ያለበት ነገር ኢሕአዴግ እጁን በንግድ ውስጥ አስገብቷል ወይ? ካስገባ ምን ርምጃ ይወሰድበት? የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ በኢሕአዴግ ነጋዴ ድርጅት መሆን አለመሆኑን እና በእጁ የያዘውን ንብረት መመርመር እና ማወቅ አንዱ የቦርዱ ቀዳሚ ሥራ ሊሆን የሚገባው ነው፡፡ ይሄ ሳያደረግ ወደ ምርጫ መግባት በምንም መልኩ ፍትሃዊ ምርጫን ሊያረጋገጥ አይችልም፡፡

በቅርቡ ከውጭ ሀገር የገቡ የፖለቲካ ቡድኖች እስካሁን ለቦርዱ ቀርበው አልተመዘገቡም፡፡ አሁን እንደ ፖለቲካ ፓርቲ እየተንቀሳቀሱ ያሉት ከምርጫ ቦርድ የምዝገባ ሰርትፍኬት ሳይኖራቸው ነው፡፡ እናም ሕጋዊ መስመሩን ጠብቀው ባስቸኳይ እንዲመዘገቡ ማድረግ፣ ካልሆነ ግን ከፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲታቀቡ ማድረግ ወይዘሮ ብርቱካን የሚመሩት የአዲሱ ምርጫ ቦርድ ትኩረት እንደሚሆን መጠበቅ ይቻላል፡፡

ባጠቃላይ ሀገሪቱ ከሁለት ዐመታት በኋላ የዘርፉ ምሁራን “foundational election” (ፈር ቀዳጅ ምርጫ) የሚሉትን ምርጫ ማካሄድ ከቻለች የዲሞክራሲያዊ ሽግግር ተስፋዋ ፈር ሊይዝ ይችላል፡፡ ለዚህ ካሁኑ ፍንጭ የሚገኘው ቢያንስ የምርጫ ቦርድ አዋጅ እስከምን ድረስ ይሻሻላል? የሚለው ጥያቄ ሲመለስ ይናል፡፡ [ተጨማሪ የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ]

https://youtu.be/SVP6baFdzXI