ዋዜማ ራዲዮ- የሶማሌ ክልል የቀድሞ ፕሬዝዳንት አብዲ መሀመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ) በቁጥጥር ስር ውለዋል። የክልሉ ምክር ቤት ምንጮች እንደነገሩን አብዲ ኢሌ በጅጅጋ ከነበሩበት ቤተ መንግስት ተይዘው ተወስደዋል። ፕሬዝዳንቱን ለመያዝ በተደረገው ጥረት ተኩስ መሰማቱን እማኞች ይናገራሉ።
ዛሬ ማለዳ ከክልሉ ባለስልጣናት ጋር ምክክር መደረጉን የሚናገሩት አንድ የምክር ቤት አባል ስብሰባዊን ተከትሎ የመከላከያ ሰራዊት አባላት አብዲ ኢሌን በቁጥጥር ስር አውለዋል።
ስራዊቱና የክልሉ ፖሊስ በጋራ በሰሞኑ ጥቃት ተሳታፊ ናቸው የተባሉ ሌሎች ባልስልጣናትንም ለመያዝ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ከክልሉ ምክር ቤት አባላት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ባለፉት ቀናት በፕሬዝዳንቱና በፌደራል መንግስቱ መካከል ድርድር ሲካሄድ ነበር። አብዲ ኢሌ የክልል ፕሬዝዳንትነቱን ስልጣን ለቀው የፓርቲያቸውን ሊቀመንበርነት እንደያዙ ለመቆየት ተስማምተው ነበር።
በስፍራው ያሉ ምንጮቻችን አብዲ ኢሌ በኀይል ተገደው እጅ መስጠታቸውን ይናገራሉ።
አሁን የመከላከያ ሰራዊቱ አብዲ ኢሌን ወዴት እንደወሰዳቸው አልታወቀም።
እስካሁን በተደረገ አሰሳ ከስልሳ የማያንሱ በግድያና ዝርፊያ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ተይዘዋል።
ጅጅጋ ዛሬ ከሞላ ጎደል ፀጥታ ስፍኖባት ውሏል። ነዋሪዎች የተዘረፈባቸውን ንብረት በማፈላልግና የሟች ቤተሰቦችን በማፅናናት ወዲያ ወዲህ ሲሉ ውለዋል።
የፀጥታ ሰራተኞች በየአካባቢው እየዞሩ የሰዎችን ምስክርነት ሲሰሙና መረጃ ሲያሰባስቡ ነበር።
በወንጀል እንፈለጋለን ብለው የሰጉ ወጣቶች ከተማን ሌሊቱን ለቀው ሸሽተዋል።
ባለፉት ቀናት በጅጅጋና ድሬዳዋ በደረሰው ዝግናኝ ስብዓዊ እልቂትና ውድመት የፌደራል መንግስቱ ፈጥኖ እርምጃ አልወሰደም በሚል ትችት እየቀረበበት ነው።