ጠ/ሚ አብይ አህመድ ለቀድሞው ጠ/ሚ ኀማደ “ከፍተኛ የክብር ዲፕሎማ” እና ለወ/ሮ ሮማን ደግሞ “የእውቅና የምስክር ወረቀት” መስጠታቸውን አየን፣ ሰማን። ወደዝርዝሩ ሳንገባ፣ አንድ የአገር መሪ ተሰናባቹን በክብር ሲሸኝ፣ ለክብሩ የራት ግብዣ ሲያደርግ ማየት በጣም መልካም ነገር ነው። ለአገራችንም እጅግ እንግዳ ባህል ነው። የክብር ኒሻን ወይም ሜዳይ መስጠት ግን ፍጹም የተለየ ጉዳይ ነው። ሁለቱን ማምታታ አያስፈልግም።
ሕገ መንግሥቱ በኢትዮጵያ መንግሥት ስም የሚበረከቱ መሰል ክብሮችን የመስጠት ሥልጣን ለርእሰ ብሔሩ ሰጥቷል ብሎ ማሰብ ይቻላል። ፕሬዚዳንቱ “በሕግ መሠረት ኒሻኖችና ሽልማቶች ይሰጣል” ይላል። ትናትን ግን ፕሬዚዳንቱ ጭራሹንም ውጭ አገር ጉብኝት ላይ ናቸው። ጠ/ሚሩ በፓርላማው ውሳኔ ወይም በሕግ መሠረት ለፕሬዚዳንቱ አቅርቦ እንዲያሰጥም ተደንግጎለታል። ይህም የሆነ አይመስልም። እንደሚመስለኝና በኢሕአዴግ ቤት እንደተለመደው የኀማደ ሽልማት ሐሳብ ድንገት የመጣ ነው። ለተቋማዊ አሠራር አንዳችም ክብር በማይሰጠብት ባህል ለሚኖሩት ሰዎች፣ አንድ ሐሳብ ከመጣ ምራቅ ሳይውጡ ወዲያውኑ ወደተግባር መሯሯጥ የሚያስመሰግን እንጂ የሚያስተች አይደለም።
ይህን ለማረጋገጥ ሩቅ መሔድ አያስፈልገም። “በዲፕሎማው” እና “በምስክር ወረቀቱ” ላይ የተነበበው በቂ ነው። ጠ/ሚ ይህንን ሽልማት የሚሰጡት ከየት ባገኙት ሥልጣንና ማንን ወክለው እንደሆነ፣ የሚሰጠው ዲፕሎማና የምስክር ወረቀት በየትኛው ሕግ እንደተቋቋመ ወዘተ የተባለ ነገር የለም። ወጉ “ይኼኛው ሕግ በሚሰጠኝ ሥልጣን፣ በዚህኛው ሕግ/መመሪያ/ልማድ ስለሽልማት ወዘተ በተደነገገው መሠረት፣ ይህንና ያንን ላደረጉ ሰዎች የሚሰጠውን ክብር፣ ለዚህ ለዚህ ተግባርህ ሰጠሁህ/ሸለምኩሽ” ማለት ነበር። ትራምፔት በመንፋት ሕግ፣ ሥርአት እና ሥነ ሥርአት (ሪቹዋል) ማቋቋም አይቻልም። ለመሆኑ ስለመሰል ሽልማቶች የሚደነግግ፣ በአዋቂዎች የተዘጋጀና ሕግ ሆኖ የጸደቀ ነገር አለን? “ከፍተኛ የክብር ዲፕሎማ” የሚለውን ስያሜ ከየት አመጣችሁት ወይስ መንገድ ላይ ፈጠራችሁት? ከ“ከፍተኛ የክብር ዲፕሎማ” ውጭ ያሉት የሽልማት አይነቶችና ደረጃቸው ምን ይመስላል? እስቲ የተጻፈ ነገር እንዳለ ጠቁሙኝ። እንደውጉማ የሽልማት ስያሜ ብቻ ሳይሆን አይነትም በሕግ መወሰን አለበት። እንዲያው ገበያ የወጣ ሰው ቆሌው እንዳመለከተው የገዛውን መሸለም የመንግሥት ወግ አይደለም።
የግርግሩን አስቂኝ ውጤት ለማየት በእንግሊዝኛ ስለሽልማቱ የተዘገበውን ማየት ይበቃል። “Ethiopia bestows highest national honor on ex-PM” ይላል። ይህንን በሽተኛ ትርጉም መጀመሪያ ያቀረበው አካል ማን እንደሆነ ባልውቅም ሌሎቹም እንደወረደ ሲቀባበሉት ያስገርማል። “ከፍተኛ የክብር ዲፕሎማ” የሚለውን “highest national honor” ብሎ ለመተርጎም ሁለቱ ስያሜዎች በሁለቱ አገሮች ባህልና ሕግ ውስጥ ያላቸውን ትርጉምና ክብደት መረዳት ያስፈልጋል። ይህን እንዳናደርግ ግን በኢትዮጵያ በኩል የታወቀ ትርጓሜ የለም። ታዲያ ተርጓሚው ከየት አመጣው? “ከፍተኛ የክብር ዲፕሎማ” የሚለውን “highest national honor” ብሎ የተረጎመ ሰው አማርኛም እንግሊዝኛም በሚገባ እንደማያውቅ መገመት ይቻላል። ስለክብር ሜዳዮችና ማእረግ ባህል ምንም ግንዛቤ ያለውም አይመስልም። አለዚያም ማምታታቱን ለፖለቲካ ፍጆታ ሆን ብሎ አድርጎታል።
ወግ ያለው፣ በሰጪውም በተቀባዩም፣ እንዲሁም በሕዝቡ የሚከበር ነገር ከፈለጋችሁ በቅድሚያ ሕግ፣ ሥርአት እና ሥነ ሥርአት አቋቁሙ። ከግርግርና ከዘማቻ ባህል ውጡ። ለዚህ ደሞ ከባዶ መነሣት የለባችሁም። ቀድምቶቹ ጥሩ መነሻ የሚሆኑ ተሞክሮዎችን ትተውልን አልፈዋል። መለስ ብሎ የዘመነ ቀኀሥንና ቀዳሚዎቻቸውንም ተሞክሮ መቃኘት ነው። በአገራችንን ልዩ ልዩ ባህሎችም የሚቀሰም ነገር አይጠፋም። የቤቱ ለማይጥመው ደሞ ለንደንን ወይም የኮንግረስ ቤተ መጻሕፍትን ማየት ነው። ጎረቤታችን ኬንያ እና ናይጄሪያም የተድራጀ ሕግ አላቸው። ሌላው ቀርቶ ለሽልማት የሚያጭ፣ የሚመረምር የጉምቶዎች ጉባኤም ያስፈልጋል፤ እንዳሁኑ በሞቅታ ኒሻን እንዳይታደል። ዝርዝሩ ብዙ ነው። ለመማር ጊዜ አለ።
ሌሎቻችን ተስማማንም አልተስማማንም፣ ሕግና ሥርዓት ቢኖር ኖሮ ለኀማደም ይሁን ለሌላ ሰው ሽልማት መስጠት ይቻል ነበር። ጠ/ሚ አብይ ሽልማቱን በመስጠት ውስጥ ፖለቲካዊና አገራዊ ግቦች እንዳሉት መገመት ይቻላል። ሆኖም፣ ስለሕግ የበለይነትና ተቋማዊ አሠራር ከሰበኩ አይቀር፣ ሽልማቱን አቆይተው ሕጉንና ሥርአቱን ቢያስቀድሙ ለራስቸውም ለአስተዳደራቸውም ክብር ይሆንላቸው ነበር። አሁን የተደረገው ግን ብሔራዊ ባንክ የማያውቀው ብር አትሞ እንደመስጠት ነው፤ ዋጋም ሕጋዊ እውቅናም የለውም።
የአሁኑ ሽልማት ለኀማደ ይገባ ነበር ወይ የሚለው ጥያቄ የሚመጣው ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው። የትኛው ሽልማት? በሕግና በሥርአት ያልታወቀ ሽልማት ከጓደኛ ስጦታ በምን ይለያል? ጥሩ የሥራ ባልደረባ ሽኝት ነበር። አዲሱ መሪ ለቀዳሚው የክብር ግብዣ ማድረጉ መልካም ነው። ይኸው ነው።
በኢትዮጵያ ስለሚሰጡ የክብር ሽልማቶች ከዚህ ማስፈንጠሪያ የተወሰነ መረጃ ማግኘት ይችላሉ-https://www.royalark.net/Ethiopia/orders.htm