- እንደሞባይል በግመል ተጭነው ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ መድኃኒቶች ተበራክተዋል
- ዜጎች መድኃኒት ፍለጋ እየተንከራተቱ ነው
ዋዜማ ራዲዮ- ከውጭ ምንዛሬ ጋር በተያያዘ አገሪቱ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቷን የሚያሳብቁ ምልክቶች መታየት ከጀመሩ ሰንበትበት ብሏል፡፡ የውጭ ምንዛሬ መሳሳትን ተከትሎ አገር ውስጥ የግንባታ ዕቃዎች የዋጋ ንረት መፈጠሩን በዘገብን በሳምንታት ውስጥ ችግሩ ከብረታ ብረት የግንባታ ዕቃ ወደ ነፍስ አድን መድኃኒቶች መዛመቱ የአገሪቱ ፈተና ስለመብዛቱ አመላካች ሆኗል፡፡
የዋዜማ ዘጋቢዎቻችን በተዘዋወሩባቸው ፋርማሲዎች ባለፉት ዐስርተ ዓመታት ተከስቶ የማያውቅ የመድኃኒቶች እጥረት መታየቱን ለማረጋገጥ ችለዋል፡፡ ሁነኛ መድኃኒቶችን ጨምሮ ጤናን ለመጠበቅ ተብለው የሚታዘዙ አልሚ ንጥረ ነገሮችም ከገበያ ተሰውረዋል፡፡
ወተትና ሌሎች ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን የያዘውና ለምታጠባ እናትና ለእርጉዝ ሴት ተዘውትሮ የሚታዘዘው “ሊብቶማማ” አንዱ ጣሳ ከመንፈቅ በፊት 100 ብር ይሸጥ ነበር፡፡ አሁን ዋጋው ወደ 300 ብር አሻቅቧል፡፡ ዋጋው ማሻቀቡ ብቻ አይደለም ችግሩ፡፡ ቀደም ባሉ ጊዜያት ከፋርማሲም አልፎ በየሱፐርማርኬት እንደልብ ይገኝ እንደበረና አሁን ግን “ሊብቶማማን” ያለበትን አውቃለሁ የሚል ጠፍቷል፡፡
“በፍለጋ እግሬ ቀጠነ፤ ‘ምናልባት የእናቶችና ሕጻናት ሆስፒታሎች ውስጥ ጠይቅ’ ተብዬ በስንት ውጣ ዉረድ እዚህ ጌታሁን በሻህ ጋ ሁለት ጣሳ በስድስት መቶ ብር ገዛሁ፤ ለዚያውም በስንት መከራ…” ብሎናል ባለቤቱ ነፍሰጡር እንደሆነች የነገረን ግለሰብ፡፡ በመጨረሻ ሊብቶማማን ማግኘት የቻለው ከሴማህ የእናቶችና ሕጻናት ክሊኒክ ነው፡፡ ሊብቶማማ አልሚ ምግብ የሱፐርማርኬት ሸቀጥ ከመሆን አልፎ በጥቁር ገበያ የሚታደን መሆኑ የችግሩን ስፋት የሚያመላክት ነው፡፡
የግመል መድኃኒት
በአሁኑ ጊዜ በመድሀኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለ ስልጣን ከዋና ዋና የመድኃኒት ዝርዝር ውስጥ የተካተቱና ኾኖም ግን ከገበያ ፈጽሞ የተሰወሩ መድኃኒቶች ቁጥር ከ20 እንደማያንስ የሚናገሩ የመድኃኒት ቅመማ ባለሞያዎች ታካሚዎች ከጥቁር ገበያ ወይም ውጭ ከሚኖሩ ዘመዶቻቸው ብቻ ማግኘት የሚችሏቸውንና በመደበኛ ግብይት የማይገኙ መድኃኒቶች ዝርዝር በከፊል ነግረውናል፡፡
ለካልሺየም እጥረት በመርፌ መልክ የሚታዘዘው ካልሺየም ግሉኮኔት፣ ለልብ ህመም የሚታዘዘው ፕሮፕራኖሎል ከገበያ ከጠፉ ሰነባብተዋል፡፡ የደም መርጋትን ለማስወገድ በመርፌ የሚታዘዘው ሄፓሪንና ኢኖክዛፓሪን አንድ መርፌ በጥቁር ገበያ 300 ብር መድረሱንም ሰምተናል፡፡ የአፍንጫ መታፈንን ተከትሎ የሚታዘዘው ስዊዘርላንድ ሠራሹ ኦትሪቪን ናሳል ድሮፕ ቀደም ሲል ከመቶ ብር ጀምሮ ገበያ ላይ እንደልብ ይገኝ እንደነበረና አሁን ግን ፈጽሞ ማግኘት እንዳልተቻለም ታውቋል፡፡
በ”አር ኤች ፋክተር” መለያየት ጽንስ ያለጊዜው እንዳይወርድ የሚያግዘውና በተለምዶ ሾተላይ ለሚባለው ችግር የሚታዘዘው አንቲ-ሮ-ዲ-ኢሚኖግሎቢን (Anti RHO-D Immunoglobulin) በጥቁር ገበያ ከ3ሺህ እስከ 5ሺህ ብር በድርድር እየተሸጠ መሆኑም ተነግሮናል፡፡
ተፈላጊነታቸው እምብዛምም ሆኖ ነገር ግን ብዙ ፈላጊ ስለሌላቸው ብቻ በብዛት የማይመረቱ መድኃኒቶችም በዶላር ምክንያት ወደ አገር ቤት ስለማይገቡ በጥቁር ገበያ እየተቸበቸቡ እንደሆነ ይነገራል፡፡ “አንቲ ሎክሲን ዝገት የነካው ብረት ሲወጋን የሚታዘዘ መድኃኒት ነው፡፡ በፍሪጅ መቀመጥ ያለበት መድኃኒት ቢሆንም በበረሃ ተንገላቶ እየገባ ለገበያ እየቀረበ ነው” ይላል ዋዜማ የነጋገረችው የፋርማሲ ባለሞያና የመድኃኒት ደላላ፡፡
ለደም ግፊት የሚታዘዙ ሀይድራላዚንም ከገበያ ከተሠወሩት አንዱ ነው፡፡ ለደም ማነስ የሚታዘዘው ሀይማፕ ሲራፕ (Haem up syrup) አገር በቀሉ ካዲላ ብቻ የሚያመርተው ሲሆን በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት አሁን በበቂ ማምረት እንዳልቻለ ሰምቻለሁ ይላል ይኸው የመድኃኒት ባለሞያ፡፡
ለጨጓራ በሽታ የሚታዘዙት ስዊዘርላንድ ሰራሹ ኔክሲየም (በስሪት ስሙ ኢሶመፐራዞል) (Esomeprazole) 14 ፍሬዎችን አልፎ አልፎ በግል የመድኃኒት መደብሮች እስከ 3መቶ ብር ከፍሎ ማግኘት ቢቻልም አሁን አሁን ግን እንደልብ ለማግኘት ወደ ጥቁር ገበያ መዝለቅ አስፈላጊ ሆኗል፡፡
ቲንየም አንቲባዮቲክ በሐኪም ጥብቅ ትዕዛዝ ብቻ በማኅተምና ፊርማ ወጪ ተደርጎ የሚገኝ፣ በጥንቃቄ የሚወሰድ መድኃኒት ሲሆን አንዱ ቫይል በ400 ብር በጥቁር ገበያ መሸጥ ተጀምሯል፡፡ ይህ መድኃኒት ሱስ የማስያዝ እድሉ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ወደ ጥቁር ገበያ መቀላቀሉ እንደ አገር አሳሳቢ ነው ይላሉ ባለሞያዎች፡፡
ከላይ ከተዘረዘሩት መድኃኒቶች በተጨማሪ ለሚለበልብ ስሜት የሚታዘዘው ፈሌክሲካም፣ ለሳል የሚታዘዘው ሜዶቨንት ሽሮፕ፣ ለደም ግፊት የሚታዘዘው ፉሪዴንክ፣ ለሕመም ማስታገሻ የሚታዘዘው ግሮፌናክ በሙሉ አገር ውስጥ ባሉ ፋርማሲዎች ማግኘት ዘበት እየሆነ መምጣቱም ተነግሯል፡፡
“ጣፊያ ኢንሱሊን አያመርትም፤ አገር ኢንሱሊን አታስገባም”
ሕይወት አድን ከሚባሉ መድኃኒቶች የሚመደበው ኢንሱሊን ከ2 ሚሊዮን የሚልቁ ኢትዮጵያዊ የስኳር ሕመምተኞችንና ቤተሰቦቻቸውን ክፉኛ እያስጨነቀ ነው፡፡ የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ‹‹አታስቡ! በቂ ክምችት አለኝ›› ቢልም ለጊዜው የሚያምነው ማግኘት አልቻለም፡፡
ሸገር ሬዲዮ፣ ኢቢሲ እና ፋና ቲሌቪዥን ጣቢያዎች በቅርቡ በሠሯቸው ተደጋጋሚ ዘገባዎች የስኳር ሕሙማን ኢንሱሊን እጥረት እንዳጋጠማቸውና በተለይም ከገጠሪቱ ኢትዮጵያ ለሕክምና ወደ ከተማ የመጡ ታካሚዎች እንደወትሮው ለሦስት ወራት የሚሆን ኢንሱሊን ሸምተው ወደ አገራቸው መመለስ እንዳልቻሉ መስክረዋል፡፡ አንዳንድ ታካሚዎች ኢንሱሊን እስከናካቴው ሊጠፋ ይችላል በሚል እሳቤ በቀን መውሰድ ያለባቸውን የኢንሱሊን መጠን ቀንሰው እየተወጉ እንደሆነም ለተጠቀሱት የመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል፡፡
በመንግሥት ሆስፒታሎችና በሕዝብ የመድኃኒት መደብሮች አካባቢ ሁኔታውን ለማጣራት ከሁለት ሳምንት በፊት ባደረግነው ሙከራ ኢንሱሊን ከገበያ አለመጥፋቱንና ሆኖም ግን ክምችቱ እየተመናመነ መሆኑን በመረዳት ሥጋት የገባቸው ፋርማሲዎች ታማሚዎች ከሚጠይቁት መጠን ግማሹን ብቻ መስጠት ጀምረው እንደነበረ ለማረዳት ችለናል፡፡ ካለፈው ሳምንት ወዲህ ግን የመድኃኒት ፈንድ አገሪቱ ለ11 ወራት የሚሆን በቂ የኢንሱሊን ክምችት እንዳላት በመግለጹ ሁኔታዎች መሻሻልን አሳይተዋል፡፡
“ዜጎች መንግሥትን የማያምኑበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ በቂ ክምችት አለ እያልናቸው በቻሉት አቅም ሁሉ በርከትከት አድርገው ነው እየገዙ ያሉት፡፡ እነሱ ሲያከማቹ ደግሞ እጥረት ይፈጠራል” ትላለች በፒያሳ ከነማ ፋርማሲ ውስጥ የምትሠራ የመድኃኒት ባለሞያ፡፡
የኢንሱሊን ከገበያ ጠፍቷል የሚለው የሚዲያ ጩኸት ገፍቶ ቢመጣም በመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ተቀባይነት ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ከመንግሥት በኩል ሁሌም እንደሚሰማው ‹‹እጥረት የለም፣ እጥረቱን የፈጠረው የፍላጎት መጨመር ነው፤ እጥረቱ ጊዝያዊ ነው፤ እጥረቱን የፈጠሩት ስግብግብ የመድኃኒት ነጋዴዎች ናቸው›› የሚሉ እርስበርሳቸው የሚምታቱ መግለጫዎች ዛሬም እየተሰሙ ይለኛሉ፡፡
የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ከሁለት ወራት በፊት ስምንት የመድኃኒት አስመጪዎችን መድኃኒት መጋዘን በማጎር እጥረት እንዲፈጠር አደርጋችኋል፣ ለዋጋ ንረትም ምክንያት ሆናችኋል ብሎ ፍርድ ቤት የገተራቸው የዛሬ ሁለት ወር ገደማ ነበር፡፡ ጉዳያቸው ዛሬም አልተቋጨም፡፡
በቀናት ልዩነት የተከሳሽ መድኃኒት አቅራቢዎችን ቁጥር ወደ 19 ከፍ ብሎም ነበር፡፡ ከነዚህ ተከሳሾች ውስጥ አንድም የአገር ውስጥ መድኃኒት አምራች የለበትም፡፡ በኢትዮጵያ በዜጎችና በውጭ ካምፓኒዎች ሽርክና የተቋቋሙ 22 አገር በቀል የመድኃኒት አምራቾች በአሁኑ ጊዜ በሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡ በ20 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በቻይና ባለሐብቶች የተቋቋመው ሂውማንዌል ፋርማሱቲካል በአማራ ክልል፣ ሀገረማርያም ተመርቆ ሥራ የጀመረው ከጥቂት ወራት በፊት ነበር፡፡
“ተከሳሾቹ መድኃኒት መደበቅ ብቻም ሳይሆን ከአንድ መድኃኒት እስከ መቶ ፐርሰንት ጭማሪ አድርጎ በመሸጥም ተወንጅለው ነበር፡፡ ከተከሳሾቹ መሐል ሀየላ፣ ማክ፣ በከር፣ አምባ፣ አፍሪ ሜድና ጄኔቲክ ፋርማሱቲካል ይገኙበታል፡፡
ከስኳር ታማሚዎች ቁጥር የተነሳ አሁን የሚዲያዎችን ትኩረት የሳበው የኢንሱሊን መድኃኒት መሰወር ይሁን እንጂ በየሆስፒታሉ በርካታ የመድኃኒት ዝርያዎች ከጠፉ ሰነባብተዋል፡፡ ነገር ግን የኢንሱሊንን ያህል አነጋገሪ መሆን አልቻሉም፡፡
“እኔ እስከማውቀው ኢንሱሊን አልጠፋም፤ እንደውም ከሌላው መድኃኒት ይልቅ በሽ…በሽ ነው፤ ሰው መድኃኒቶቹን ‘በብራንድ ኔም’ ስለሚያውቃቸው ነው የጠፋ የመሰለው፡፡” የሚለው ዋዜማ ያነጋገረችው ፋርማሲስት “ብዙ ሰው “ኢንሱላታርድ” ካልሰጠከው “ጁስሊን” ብትሰጠው እሺ አይልም፡፡ የተለያየ ንግድ ስም ያላቸው አንድ አይነት መድኃኒቶች እንደሆነ ብታስረዳቸውም አይሰሙህም፡፡” ይላል፡፡
“ኢንሱሊን በከነማ፣ በቀይ መስቀል እና በሁሉም ሆስፒታሎች በአንድ ወር ብቻ 410ሺ ቫይል ተሠራጭቷል፡፡ ኾኖም ታካሚዎች መድኃኒቱ ይጠፋል በሚል ከሚያስፈልጋቸው በላይ ይገዛሉ፡፡ የግል ፋርማሲዎችም መድኃኒቱ ሲጠፋ ጠብቀው በጥቁር ገበያ ለመሸጥ ሆን ብለው ያከማቻሉ፡፡ እጥረቱ የሚፈጠረው በዚህ ምክንያት ይመስለኛል፡፡” ይላል ዋዜማ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ በስፋት ያነጋገረችው፤ በፋርማሲ በዲግሪ ከግል ኮሌጅ ተመርቆ በመድኃኒት ማሻሻጥና ድለላ ሥራ የተሠማራ ባለሞያ፡፡ ይኸው ባለሞያ እንደነገረን ከሆነ ብዙ ለማጠራቀምና እጥረት ሲፈጠር አውጥቶ ለመሸጥ በሚሞክሩ ሰዎች የተማረረው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል “ከራሴ ሆስፒታል ላልተመረመሩ መድኃኒቱን አልሸጥም” የሚል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
የመድኃኒት የገበያ ሠንሠለት
የመድኃኒት ሥራ የትርፍ ሕዳግ ከ15 እስከ 20 በመቶ ብቻ ነው፡፡ አንድ ኩባንያ ራሱ አስመጥቶ፣ ራሱ ጅምላ አከፋፍሎ፣ ራሱ ካልቸረቸረው መንግሥት ይሁንታ በሰጠው የትርፍ ሕዳግ ብቻ ሠርቶ የሚያመረቃ ትርፍ ማግኘት አይችልም ይላሉ በዘርፉ የሚውተረተሩ ደላሎች፡፡ ፋርማሲዎች የተወሰኑ መድኃኒቶችን ከመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ በወረፋ መግዛት ይችላሉ፡፡ ኾኖም አብዛኛው ግብይታቸው የሚዘወረው የመድኃኒት አስመጪዎች በሚያሰማሯቸው በዘርፉ የሰለጠኑ ደላሎች ነው፡፡
“አዲስ ብራንድ መድኃኒት ለማስተዋወቅ ለሐኪሞች ብዙ ብር መክፈል ያስገልጋል፡፡ በፋርማሲ የተመረቁ ደላሎች በየፋርማሲው እየሄዱ ማስተዋወቅ አለባቸው፡፡ ሥራው የሚሠራውም በዱቤ በማከፋፈል ነው፡፡” የሚለው የመድኃኒት የሽያጭ ባለሞያ፣ አሁን በቁጥር በብዛት የተከፈቱ ፋርማሲዎች ሁሉም የዱቤ ተጠቃሚዎች ካልሆኑ መድኃኒት ለመረከብ ፍቃደኞች አይሆኑም ሲል ያብራራል፡፡
እነዚህ ሁኔታዎች መድኃኒት ደብቆ እጥረት ሲፈጠር ብቻ አውጥቶ በመሸጥ ሞቅ ያለ ትርፍ ለማግኘት የሚደረገውን ሙከራ እንዲስፋፋ አድርገውታል፡፡ የግል መድኃኒት ቤት የሚሠሩ ፋርማሲስቶች አንድን መድኃኒት ‹‹የለም›› ካሉ በኋላ የደንበኛውን አቅም ገምግመው ‹‹እስኪ ከውጭ የሚያመጡ ሆስተሶች ስላሉ ምናልባት ልሞክርዎ፤ ስልክዎትን ይስጡኝ›› ይላሉ፡፡ ይህ የሚደረገው መድኃኒቱን ከጥቁር ገበያ አምጥቶ በውድ ለመቸብቸብ እንደሆነ ይነገራል፡፡
ዋዜማ ያናገረችው ባለሞያ የመድኃኒት ሽያጭ ሰንሰለቱ ክትትል እንደማይደረግበት ጠቅሶ በተለይም ሥነምግባር የጎደላቸው የሕክምና ባለሞያዎች ጄኔሪክ ኔም ከመጻፍ ይልቅ ብራንድ ኔም በመጻፍ ታካሚዎችን ለእንግልት ይዳርጋሉ ይላል፡፡ “አንድ ታካሚ ሐኪሙ ካዘዘለት የመድኃኒት ስም ውጭ ልስጥህ ብትለው የምታጭበረብረው ነው የሚመስለው፡፡” ሲል ያብራራል፡፡ የዴንማርኩ ኢንሱላታርድ በጠፋበት ወቅት የሆነውን በማስታወስ፡፡ ሐኪሞች በብራንድ ስም መድኃኒት እንዳያዙ ቢደረግ የሚል አስተያየትም ይሰጣል፡፡
የግል ጤና ተቋማት መድኃኒት የሚያገኙት ከግል አስመጪዎች ነው፡፡ የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ መድኃኒት የሚያከፋፍለው ለመንግሥትን የሕዝብ ጤና ተቋማት ብቻ ነው፡፡ አንዳንድ የተመረጡ መድኃኒቶችን ብቻ ለግል ያቀርባል፡፡ የግል አስመጪዎች እንደበፊቱ ዶላር ስለማያገኙ በበቂ መጠን መድኃኒት አያስገቡም፡፡ የሚገቡ መድኃኒቶች ውስን ስለሆኑ የግል ፋርማሲዎች እጥረት እንዲፈጠር ያሏቸውን መድኃኒቶች ይደብቋቸዋል፡፡ ሰው መድኃኒቱን ሲያጣ ግራ ስለሚገባው፣ የሕይወት ጉዳይም ስለሚሆንበት የተጠየቀውን ገንዘብ ይከፍላል፡፡ የዶላር እጥረቱ ጥቁር ገበያው ሁነኛ የመድኃኒት አቅርቦት መስመር እንዲሆን አግዞታል፡፡
አንዳንድ የጠፉ መድኃኒቶች በደላሎች እጅ እንዴት ሊገቡ የሚችሉባቸውን መንገዶች ያነጋገርነው የመድኃኒት ባለሞያ ሲያብራራ፤ ” አንደኛው ከመንግሥት ሆስፒታልና ፋርማሲ በድብቅ በማውጣት ሲሆን፣ ሁለተኛው መድኃኒቶቹን በድንበር በኩል በግመል በማስመጣት” እንደሆነ ያብራራል፡፡ በግመል የሚገቡት ለጤና አደገኛ እንደሚሆኑም አልሸሸገም፡፡
“አብዛኛው መድኃኒት ፀሐይ ከነካው ፈዋሽነቱ ይጠፋል፤ ፍሪጅ ውስጥ መቀመጥ የነበረበት መድኃኒት በግመል ጀርባ በበረሃ መጥቶ በውድ ሲሸጥ ምን ሊከሰት እንደሚችል አስበው፡፡ ታማሚዎች መድኃኒቱን ማግኘታቸውን እንጂ እንዴት እንደገባ አያውቁም፡፡” ሲል ያብራራል፡፡ እነዚህ መድኃኒቶች “ዳካ” ሳይመዘግባቸው፣ ዱካቸው ሳይታወቅ አገር ውስጥ ስለሚገቡ ፎርጅድ የሕንድ መድኃኒት የሚሆኑበት አጋጣሚም ብዙ ነው፡፡
በፓኬጂንግ እና ሌብሊንግ ላይ የተጠመዱ ፋብሪካዎች
መንግሥት በገቢ ንግድ ከጨከነ ሰንብቷል፡፡ በራሱ ሜጋ ፕሮጀክቶች መጨከን ከጀመረ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ በመድኃኒት ግን ጨክኖ አያውቅም፡፡ አንዲት አገር መድኃኒት ማስገቢያ የውጭ ምንዛሬ ላይ መሰሰት ከጀመረች የዛች አገር ጥርስ ተነቃንቋል ማለት ነው፡፡ ሰሞኑን እየታየ ያለውም ይኸው ነው፡፡
አገሪቱ ከሚያስፈልጋት የመድኃኒት ፍላጎት 80 ከመቶውን የምታሟላው አንጡራ የውጭ ምንዛሬዋን ከስክሳ ከውጭ በማስገባት ነው፡፡ ከ15 እስከ 20 በመቶ የሚሆነውን የመድኃኒት አቅርቦት አገር ውስጥ በማምረት ላይ የሚገኙት ዘጠኝ ፋብሪካዎችም ቢሆኑ አብዛኛውን የመድኃኒቱን ግብአት ለመሸፈን የውጭ ምንዛሬን ይሻሉ፡፡
ማንኛውም መድኃኒት የብዙ ንጥረ ነገር ድምር ነው፡፡ በድምሩ Active እና inactive ንጥረ ነገሮች ingredient ውህድ ተደርጎ ነው የሚመረተው፡፡ ከፈዋሹ ንጥረ ነገር ባሻገር መድኃኒቱ ሆድ ውስጥ ከገባ በኋላ ቶሎ እንዲበተን የሚያደርጉ ንጥረ ነገሮች (Disintegrant)፣ የፈዋሹ መድኃኒት ማቀፊያዎች (bulking agent)፣ ለጣዕም የሚጨመሩ ንጥረ ነገሮች (sweetening agent)፣ ሳይበላሸሽ እንዲቆይ (reservative) ወዘተ መድኃኒቱን ለማምረት አስፈላጊ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ከውጭ የሚገቡ መሆኑ የምንዛሬን አስፈላጊነት ያጎላዋል፡፡
በዚህም ምክንያት ዛፍ፣ ሜድቴክ፣ አዲግራት፣ ጁልፋር፣ ካዲላ፣ አዲስ ፋርም፣ ፋርማ፣ ሜድ ሶል ሁሉም የዶላር ያለህ እያሉ ነው፡፡ ገዘፍ ያሉ የአገር ውስጥ የመድኃኒት አምራቾች በቁጥር ዘጠኝ ብቻ ሲሆኑ ከዓመታዊ የመድኃኒት ፍጆታ በነዚህ አምራቾች መሸፈን የቻለው ከ20 በመቶ አይዘልም፡፡ እነዚህ ፋብሪካዎች ከ380 እጅግ ወሳኝ የሆኑ የመድኃኒቶች ዝርዝር ውስጥ በአገር ውስጥ መመረት የሚችሉት 65ቱ ብቻ ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ መድኃኒት አምራች ናቸው ለማለት የሚከብደውም ለዚሁ ነው፡፡ ባይሆን በፓኬጂንግና ሌብሊንግ የተጠመዱ ብንላቸው ይቀላል፡፡
በአንጻሩ መንግሥት በየዓመቱ ለመድኃኒት የሚያወጣው ወጭ በከፍተኛ ሁኔታ እየናረ ሲሆን ባለፈው ዓመት ብቻ የስድስት ቢሊዮን ብር የመድኃኒት ግዢ አከናውኗል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅትን ከመሰሉ አጋር ድርጅቶች ከዚህ ገንዘብ የማይተናነስ የመድኃኒት ድጎማም ተደርጎለታል፡፡ በድምሩ የከ15 ቢሊየን ብር በላይ ለመድኃኒት ተከስክሷል፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖም ፍላጎት አልተሟላም፡፡
በአሁኑ ወቅት ከሦስት መቶ የማያንሱ የተመዘገቡ ጅምላ መድኃኒት አቅራቢዎች በአገሪቱ ይገኛሉ፡፡ የመድኃኒት አቅርቦት በየዓመቱ በ20 በመቶ ቢጨምርም አሁንም ፍላጎት ሊሟላ አልቻለም፡፡ አንዱ ምክንያት በአገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ የመጣው ተላላፊ ያልሆኑ ደዌ ነው የሚሉ ባለሞያዎች አሉ፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ምንዛሬ ጭንቀቱን በዘላቂነት ለማስወገድ እንደ ጨርቃ ጨርቅ ኢንደስትሪው ሁሉ የፋማሱቲካል ኢንደስትሪ ፓርክ ለማቋቋም ወስኖ በፍጥነት ወደ ተግባር መግባቱ ይታወሳል፡፡ በኢትዮጵ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና በዶክተር አርከበ እቁባይ አመራር ቂሊንጦ አቅራቢያ በ5.5 ቢሊዮን ብር በቻይናው ሲቲሲኢ እየተገነባ ያለው የመድኃኒት ፓርክ ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት እየተገነባ ይገኛል፡፡ ፍሬ እስኪያፈራ ግን ረዥም ዓመታትን መፈለጉ አይቀርም፡፡
የውጭ ምንዛሬ- አዙሮ የሚጥል በሽታ
መድኃኒት ፋብሪካ የሚገነቡ ባለሐብቶች ማሽን መቶ በመቶ ከቀረጥ ነጻ ያስገባሉ፣ የታክስ እፎይታ ይሰጣቸዋል፤ 70 በመቶ ያለ ማስያዣ ብድር ያገኛሉ፡፡ በጨረታ ጊዜ የተወዳዳሪነት የዋጋ ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ 50 በመቶ ምርታቸውን ለወጪ ንግድ ካቀረቡ የ3 ዓመት ግብር ነጻ ይደረጋሉ፡፡ ያም ሆኖ ብዙ ፋብሪካዎች የኢትዮጵያ ነገር አይማርካቸውም፡፡ የሁሉም ምክንያት ተመሳሳይ ነው፡፡ ‹‹ርካሽ ጉልበት አለ፤ አልሰለጠነም፤ ሰፊ ገበያ አለ፤ ዶላር ግን የለም›› ይላሉ በአንድ ድምጽ፡፡
እውነት አላቸው፡፡
በኢትዮጵያ የተሠማሩ በርካታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በሕግ የተፈቀደላቸውን የትርፍ ገንዘብ በዶላር ከብሔራዊ ባንክ ለመውሰድ እንዳልቻሉ ይታወቃል፡፡ ከነዚህም መካከል አንዱ ዳንጎቴ ሲሚንቶ ነው፡፡ በተመሳሳይ በአገሪቱ ግዙፉ የቢራ ጠማቂ ሃይኒከን በዓመታት ውስጥ ያተረፈውን ገንዘብ በዶላር ከአገር ለማውጣት አለመቻሉ ሲነገር ቆይቷል፡፡ መንግሥት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ከቢራ ጠማቂው አመራሮች ጋር ባደረገው ድርድር ከአገር ለማውጣት ያልቻሉትን ግዙፍ የዶላር ክምችት ለፋብሪካው ማስፋፊያ እንዲውል፣ ይህንኑ ለማሳለጥም ንግድ ባንክን ጨምሮ ሁሉም የግል ባንኮች ያላቸውን ጥሪት ቆነጣጥረው በመዋጮ 40 ሚሊዮን ዩሮ ለሃይኒከን ኤል ሲ መክፈቻ እንዲያውሉ ከብሔራዊ ባንክ መመሪያ እንደተሰጣቸው፣ ይኸው መመሪያም ከዶክተር አርከበ እቁባይ እንደተላለፈ ሳምንታዊው ፎርቹን ጋዜጣ በጃንዋሪ 30 ዕትሙ ጽፎ ነበር፡፡
የኋላ ኋላ ‹‹እኔ ትዕዛዝ አልሰጠሁም፤ ሥልጣኑ የብሔራዊ ባንክ ነው›› የሚል ማስተባበያ ከአርከበ እቁባይ እንደደረሰውም ይኸው ጋዜጣ ጽፏል፡፡ ከዚህ የዶላር መዋጮ ነጻ እንዲሆን የተደረገው ደቡብ ግሎባል ባንክ ብቻ ሲሆን አዋሽ ባንክ ትልቁን መዋጮ እንዲሰጥ ግዳጅ ተጥሎበት ነበር፡፡ ‹‹ለመድኃኒት የሌለውን ዶላር ለቢራ ጠማቂ አምጡ ተባልን!›› ሲል መገረሙን የገለጸው የዚሁ ዘገባ አካል የተደረገ አንድ የባንክ ሠራተኛ የምንዛሬ እጥረቱ መንግሥትን እንዳሰከረው የሚጠቁም ሐሳብ አንጸባርቋል፡፡
ባንኮች ዶላር አዋጡ የሚል መመሪያ ሲደርሳቸው በአንድ ዓመት ውስጥ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሆነም ተዘግቧል፡፡ ከወራት በፊት ለኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ደርጅት ተመሳሳይ የዶላር ክፍያ መዋጮ የግል ባንኮች የውዴታ ግዴታ መመሪያ ተላልፎላቸው ነበር፡፡
የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ አገሪቱ የሚያስፈልጓትን የመድኃኒት ዝርዝር መዝግቦ ግዢ ፈጽሞ ያቀርባል፡፡ ኾኖም ሁሉም መድኃኒቶች በዚህ መሥሪያ ቤት በኩል አያልፉም፡፡ ሁሉንም መድኃኒት የማቅረብ አቅሙም የለውም፡፡ በመሆኑም ኤጀንሲው በአገሪቱ ዋና ዋና የጤና ችግሮችን መሠረት ያደረገ ግዢ ይፈጽማል፡፡ የመድኃኒት ግዢው የሚካሄደው የጤና ተቋማት ለዚህ መሥሪያ ቤት በሚያቀርቡት የፍላጎት ዝርዝር መሠረት ነው፡፡
ኤጀንሲነው በሚቻለው ሁሉ 17 ቅርንጫፎችን ተጠቅሞ መድኃኒት ግዢ ኮማንድ ፖስት አቋቁሞ የሚቻለውን ሁሉ ሞክሮ ባይሞላለት “የኅብረተሰቡ መድኃኒት የመጠቀም ልምድ መጨመር ነው እጥረት እየፈጠረ ያለው” እስከማለት ደርሶ ያውቃል፡፡ ኤጀንሲው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጀመረው ዘመናዊ አሰራር በየጊዜው የግዢ ጨረታ ከማውጣት ይልቅ አንድ የመድኃኒት አቅራቢ ለሦስት ዓመት እንዲፈራረም በማድረግ በጨረታ ሂደት የሚባክነውን ጊዜ ለማሳጠር እየሞከረ ይገኛል፡፡ ኾኖም መድረስ የሚችለው የሕዝብና የመንግሥት የጤና ተቋማትን ብቻ በመሆኑ ጥረቱ ግመሽ ጎዶሎ አደርጎበታል፡፡
“በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለቀዶ ጥገና የሚውሉ ክሮች ጠፍተዋል እንዳንባል እሰጋለሁ” የሚለው የራስ ደስታ ዳምጠው ሆስታል ሀኪም “እንደልብ የሚገኙ የሐኪም ጓንት፣ አንቲ ፔይን፣ አንቲ ባዮቲክ አንቲ ኤነፌክሽን፣ የባክቴሪያ ኤንፌክሽን ለማከም የሚውሉ የመርፌ ሜሮፔኔም፣ ቫንኮማይሲን ስንጠይቅ ጠብቁ እየመጣ ነው መባል ተጀምሯል፤ ያስፈራኛል” ይላል፡፡
“አስበው እንግዲህ፤ ኢትዮጵያ ከሰሐራ በታች በስኳር ሕመምተኞች ብዛት አንደኛ ናት፡፡ ከ2 ሚሊዮን በላይ የስኳር ህመመትኛ ያለባት አገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ መንግሥት ኢንሱሊን በምንዛሬ ምክንያት ጠፋ ካለ ዜጎችን በጅምላ ጨራሽ መሣሪያ ከመግደል በምን ይተናነሳል” ሲልም ይጠይቃል፡፡