ዋዜማ ራዲዮ- ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ውስጥ ውስጡን ሲብላላ የከረመው የአባል ድርጅቶቹ ሽኩቻ አደባባይ ከወጣ ሳምንታት ተቆጠሩ። ገዥው ፓርቲም ልዩነት መከሰቱን አልሸሸገም፣ የስራ አስፈፃሚው ስብሰባ ገና ግማሽ መንገድ ሳይጓዝ መግለጫ አውጥቶ ድርጅቱን ለማደስ ያለውን ቁርጠኝነት አትቷል።
እውነታው ግን ወዲህ ነው። ፓርቲው መልሶ ሊጠግነው የማይችል ልዩነት ውስጥ ነው። ሊያደርግ የሚችለው ነገር ቢኖር በውስጡ የነበረውን ያልተመጣጠነ የሀብትና የስልጣን ክፍፍል በማሸጋሸግ ልዩነቱን ማርገብ ብቻ ይሆናል። ይህም ቢሆን ችግሩን ከመሰረቱ ሊያሰወግድ እይችል ይሆናል። ተከተዩ ዘገባችን ክፍፍሉን ድርጅቱ ሊያስተካክለው የማይችል አዲስ ቅርቃር ውስጥ ከቶታል ይለናል። ሀኒ ሰለሞን ከቻላቸው ታደሰ ጋር በዚህ ሳምንቱ የዋዜማ መፅሄት ያደረጉትን ውይይት በፅሁፍ አቅርበነዋል። ከግርጌ ደግሞ በድምፅ የተቀናበረውን ማድመጥ ትችላላችሁ።
ሀኒ ሰለሞን– ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ስሞኑን እያደረገ ባለው የሥራ አስፈፃሚ ስብሰባ የከረሩ ልዩነቶች እና ክፍፍል ጭምር መኖሩን የሚያረጋግጥ መግለጫ አውጥቷል፡፡ ለመሆኑ በአጭሩ ድርጅቱ እንዲህ ወዳለው ቀውስ እንዲገባ ምክንያት የሆኑት ጉዳዮችን እስኪ አስታውሰን?
ቻላቸው ታደሰ- ረቡዕ ዕለት ሥራ አስፈጻሚው ገና ስብሰባውን ሳይጨርስ ነበር በመሃሉ መግለጫ ያወጣው፡፡ ይሄም ነገሮች ከቁጥጥሩ ውጭ እንዳልወጡ ወዳጅም ጠላትም እንዲያውቁለት መፈለጉን ነው የሚያሳየን፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከወር በፊት በግንባሩ አባላት መካከል መጠራጠር መኖሩን አስተባብለው የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ለመጀመሪያ ጊዜ አምኗል፡፡ መጠራጠሩ እና አለመተማመኑም በኦሕዴድ እና ሕወሃት እንዲሁም በብአዴን እና ሕወሃት መካከል እንደሆነ ግልጽ ከሆነ ቆይቷል፡፡ ላለመተማመኑ ምክንያት የሆኑትን ጉዳዮች እና በምን መስኮች ዙሪያ እንደሆነም ባይገለጽም በድርጅት እና መንግስት ደረጃ ከሚነሱት የፖለቲካ ስልጣን ባለቤትነት እና ፍትሃዊ ሃብት ክፍፍል ሌላ የፌደራሉ እና ክልል መንግስታት ግንኙነት መዛባት ጭምር እንደሚሆኑ መገመት ይቻላል፡፡
ሀገሪቱ ለገጠማት ችግር ዋናው ተጠያቂ የብሄር ፌደራላዊ ሥርዓቱ ነው የሚለውን ገዥ ሃሳብ ይዘን ወደ ዝርዝር ነባራዊ ምክንያቶች ስንመጣ ኢሕአዴግ መንግስታዊ አስተዳደሩን ከተጨባጭ ሀገራዊ ሁኔታዎች እና ከጊዜ ጋር ማጣጣም የማይችል ግትር ድርጅት መሆኑ ነው የምናገኘው፡፡ ህዝባዊ አመጽ ከተነሳበት በኋላ እንኳ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን በማጎልበት፣ ዴሞክራሲያዊ እና ሰብዓዊ መብቶችን በማክበር፣ ገለለትኛ ተቋማትን በመፍጠር፣ የሕግ የበላይነትን በማስጠበቅ እና የፍትህ አገልግሎት ረገድ፣ በመልካም አስተዳደር፣ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር፣ ከመንግስት ሁለንተናዊ ጣልቃ ገብነት ነጻ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ምህዳርን በማስፋት ወዘተ አንዳችም መሻሻል አላደረገም፡፡ እንዲያውም በብዙ መስኮች ማሽቆልቆል ነው ያሳየው፡፡
ለዚህ ምክንያቱ ግን የፖለቲካ ፍላጎት ወይም ቁርጠኝነት ማጣት ነው የሚለው ጊዜው ያለፈበት ነገር ነው፡፡ ይልቁንስ የሀገሪቱን ቀውስ በተሟላ ሁኔታ ተረድቶ ዘላቂ መፍትሄ የሚያመነጭ መዋቅርም ሆነ የፖለቲካ አመራር የሌለው መሆኑ ነው ሊሰመርበት የሚገባው፡፡ ለዚህም ነው ድርጅቱ ከአቶ መለስ ዜናዊ ህልፈት በተለይም ደሞ ካለፉት ሦስት ዐመታት ወዲህ ከመንግስታዊ ሥራው ይልቅ በውስጣዊ የፓርቲ ሽኩቻ ብዙ ጊዜውን እና ጉልበቱን እያባከነ ያለው፡፡
ኢሕአዴግ ብዙ ብሄረሰቦች እና ብዝሃ የፖለቲካ አመለካከቶች ያሉባትን ሀገር ባንድ የተወናበደ ሃሳብ ጨፍልቆ መግዛት መፈለጉ ራሱንም ሆነ ሀገሪቱን ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡ ቀደም ሲል “የችግሩ ምንጭ የላይኛው የመንግስት አመራር ነው” ሲል ኖሮ በቀደምለት ደሞ ወደ ድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ አጥብቦታል፡፡ የችግሩ ምንጭ የሆነው አካል በጥቅሉ ሥልጣኑን ይዞ ባለበት ሁኔታ እንዴት መፍትሄ እንደሚያመጣ ግልጽ አይደለም፡፡ ቢያንስ መንግስትን ለገጠሙት ችግሮች እንኳ የሚንስትሮች ምክር ቤት ሚና ተረስቶ ጠቅላይ ሚንስትሩ በፓርቲ ስብሰባ ነው ተጠምደው የሚታዩት፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የድሮ ሥራ አስፈጻሚ አባላትን እና አመራሮችን በስብሰባ እያሳተፈ ያለው ለምንድን ነው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ በድርጅቱ ሕገ ደንብ መሰረት የድርጅቱን የዕለት ተለት ሥራዎች የሚከውነው ይኸው ሠላሳ ስድስት አባላት ያሉት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ቢሆንም ያሁኑ ድርጊቱ ግን ሀገሪቱ፣ ኢሕአዴግ እና መንግስት የገቡበትን ቀውስ መፍታት እንዳልቻለ ነው የምንረዳው፡፡ እነዚሁ ሰዎች ግን ሀገሪቱ አሁን ለገባችበት ቀውስ መሰረቱን የጣሉ በመሆናቸው ሁነኛ መፍትሄ የማመንጨት እድላቸው ዝቅተኛ መሆኑን መርሳት የለብንም፡፡
ድርጅቱ በተለይ ክፍፍል ውስጥ በገባበት ሰዓት ሥራ አስፈጻሚው በድምጽ ብልጫ እንደሚወስን ነው የሚጠበቀው፡፡ እዚህ ላይ ግን ተጋባዦቹ አሮጌ አመራሮች እየተሳተፉ ያሉት በድምጽ ነው ወይስ ያለ ድምጽ? የሚለው ጥያቄ አልተመለሰም፡፡ ከአራቱም አባል ድርጅቶች ይውጣጡ አይውጣጡም አልታወቀም፡፡ በድምጽ ሆነም አልሆነም ሃሳቡን ያመነጨው ሕወሃት እንደሆነ እና በኦሕዴድ እና ብአዴን ላይ የሃሳብ የበላይነት ለመያዝ የቀየሰው ዘዴ እንደሆነ መገመት አያስቸግርም፡፡ ኦሕዴድን አሁን እየመሩት ያሉት በትጥቅ ትግሉ ሂደት ያልተሳተፉ አዳዲስ ፖለቲከኞች መሆናቸው ለዚህ ጥሩ እድል ይፈጥርለታል፡፡ ባጠቃላይ ስብሰባው የቀውስ ጊዜ አስቸኳይ ስብሰባ ወይም በእንግሊዝኛው “crisis meeting” እንጂ በድርጅቱ ሕገ ደንብ መሠረት እየተካሄደ ያለ መደበኛ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ አድርጎ መውሰድ የሚቻል አይመስለኝም፡፡
ሌላው የፓርቲው አወቃቀር እና የተዛባው ውስጣዊ የሃይል ሚዛኑም አሁን ለገባበት ችግር እነደ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ የብሄር አደረጃጀቱ በዋናነት ሥርዓቱን ለፖለቲካ ሙስና፣ ለፖለቲከኞች ሃብት ቅርምት፣ ለኪራይ ሰብሳቢነት እና ለብሄር ተኮር ግጭት ነው ያጋለጠው፡፡ ይህም ውስጣዊ ቅራኔ እየፈጠረበት ነው፡፡ ውህድ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ የሚሆንባቸውን እድሎች ደሞ ከሞላ ጎደል ቀድሞ አባክኗቸዋል፡፡
ሀኒ ሰለሞን– ክፍፍሉ የፖለቲካ አመራሩን ብቻ ሳይሆን የፀጥታ ተቋማትንም የሚመለከት እንደሆነ ተመልክተናል። በኦሮሚያ ክልል የፌደራሉ መንግስት ኃይሎች እንዳይንቀሳቀሱ ክልሉ ሲከለክል ነበር። እንዲህ አይነቱ አለመግባባት ወደ ለየለት አንጃ ሊሸጋገር ይችላል የሚል ስጋት ያላቸው አሉ። የፀጥታ ሀይሎቹ አወቃቀርና ተጠሪነት እንዲሁም ያላቸው ትጥቅ ላይ የሚነሱ ጉዳዮች እንዳሉ ከወራት በፊት አንስተን ነበር። እስቲ አሁን ያለውን ሁኔታ ንገረን?
ቻላቸው ታደሰ- ፍጥጫው ከፖለቲካ አልፎ የፌደራሉን እና ክልል ጸጥታ ሃይሎችንም መሳሪያ እስከማማዘዝ ደርሷል፡፡ በፌደራል መንግስቱ ጸጥታ ሃይሎች ላይ መንገዶችን መዝጋት ወይም አቁሞ መጠየቅ መደጋገሙንም እየሰማን ነው፡፡ በትክክልም ፖለቲካዊ ውጥረቱ ወደ ጸጥታ ሃይሎች መጋባቱ የሚጠበቅ ነው፡፡
አሁን እንደምናየው በክልል ደረጃ በሚከሰቱ የብሄረሰብ ግጭቶች ውስጥ የህዝብን ደኅንነት እና ህገ መንግስቱን የመጠበቅ ሃላፊነት ያለባቸው የክልል እና ፌደራል ጸጥታ ሃይሎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተሳታፊ እየሆኑ ነው። ከምንም በላይ የፌደራል መከላከያ ሠራዊቱ ከተቋቋመለት የሀገር አንድነት የመጠበቅ ተልዕኮው በመውጣት በየቦታው የሚካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎችን በመበተን ሥራ ጭምር የመሰማራቱ ነገር በዚሁ ከቀጠለ የመንግስትን ከባድ ውድቀት ከማሳየት አልፎ ወደፊት ጎራ የለየ ከባድ ግጭት ሊቀሰቅስ የሚችል ነው፡፡
ድርጅታዊ ቅራኔ ሁነኛ መፍትሄ አገኘም አላገኘም በሰላማዊ ፖለቲካዊ መድረኮች እየታየ ሊቀጥል ይችላል እንበል፡፡ የጸጥታ ሃይሎች እንዴ መሳሪያ መማዘዝ ከጀመሩ ግን ወዲያውኑ የብሄረሰብ መልክ ስለሚይዝ እና ሕገ መንግስቱን መጠበቅ የሚባለው ገዥ መርህ ወደ ጎን ተገፍቶ ዘርፈ ብዙ ወደሆነ እና ማባሪያ ወደሌለው ግጭት ውስጥ ነው የሚገቡት፡፡ በዚህ ላይ ደሞ ኢሕአዴግ ጸጥታ ሃይሎችን በድርጅታዊ እና ብሄረሰብ ፖለቲካ ስላጠመቃቸው እና የሠራዊቱ አዛዦችም ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ስላላቸው ወደዚህ አዘቅጥ ለመውረድ አይከብዳቸውም፡፡ ባሁኑ ጊዜ እኮ ከወገንተኛ ፖለቲካ የጸዳ የጸጥታ ሃይል አይገኝም፡፡ እንደቀላል ነገር ታለፈ እንጂ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከወር በፊት ህገ መንግስታዊ ይዘት ያለው የፖሊስ ሃይል ገና አልገነባም ብለው መናገራቸው ይህንኑ ነው የሚያረጋግጥልን፡፡ መንግስት በመከላከያ ሠራዊቱ ጥገኛ እየሆነ መምጣቱም በዋናነት በፌደራል ፖሊስ ላይ እምነት ማጣቱን ይጠቁማል፡፡
የኦሮሚያ ክልል መንግስት የጨለንቆው ተቃውሞ ሰልፍ ከክልሉ አቅም በላይ እንዳልነበረ እና የፌደራሉ መከላከያ ሠራዊትም ጣልቃ እንዲገባ አለመጠየቁን መግለጹም ባንድ በኩል ፌደራል መንግስት የመላ ሀገሪቱን ጸጥታ ለማማከል የሄደበት ያለውን ርቀት ሲያሳይ በሌላ በኩል ደሞ ከክልሉ መንግስት ጋር የገባበትን ፖለቲካዊ ፍጥጫ ያሳያል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ “የመከላከያ ሠራዊት አባላት የጨለንቆን ግጭት ጨምሮ ተልዕኳቸውን እየፈጸሙ ባሉበት ወቅት ያጋጠሙ ክፍተቶች ካሉ አሠራሩን ተከትሎ መንግሥት ያጣራል” ሲሉ መግለጸቸው የተፈጸመውን ጅምላ ግድያ የማይመጥን በእጅጉ የተለሳለሰ አነጋገር ነበር፡፡ የተማከለ ወታደራዊ እዝ ላለው ሠራዊት ግን ግድያውን የፈጸሙትን ወታደሮችን ማንነት እና ግድያውን ለምን እንደፈጸሙ ማወቅ በጣም ቀላሉ ነው፡፡ እዚህ ላይ ግን ዋናው ጥያቄ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዡ የመከላከያ ሠራዊቱ አዛዦች ተጠርጣሪ የሠራዊቱን አባላት ለህግ አሳልፈው እንዲሰጡ የማድረግ አቅም አላቸው ወይ? የሚለው ነው፡፡ አነጋገራቸው የሚጠቁመን አቅሙ የሌላቸው መሆኑን ነው፡፡
በሌላ በኩል የጨለንቆው ግድያ እንዴት ሊፈጸም እንደቻለ የፌደራሉ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ወይም ከፌደራሉ እና ኦሮሚያ ክልል የተውጣጣ ልዩ የጋራ አጣሪ ቡድን መሆን ሲገባው መንግስት ግን አጣርቶ ርምጃ እንዲወስድ ሃላፊነቱን ያሸከመው ራሱ ለሚመራው ብሄራዊ የፀጥታ ምክር ቤቱ ነው፡፡ ሌላው ቢቀር ክስተቱ በመርህ ደረጃ ለሕገ መንግስቱ ታማኝ የሆነውን መከላከያ ሰራዊት የሚመለከት ስለሆነ በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ወይም ፓርላማው በሚያቋቁመው ገለልተኛ አካል ነው መጣራት የነበረበት፡፡ ይህ አካሄድ መንግስትም ሆነ ኢሕአዴግ ከኦሮሚያ ክልል እና ኦሕዴድ ጋር የገቡበትን ቅራኔ ጠቋሚ ነው፡፡
አሁን ባንድ በኩል ከወራት በፊት በሱማሌ እና ኦሮሚያ አዋሳኝ ክልሎች የደረሰውን ግድያ እና መፈናቀል ፈጥኖ መከላከል ባለማቻሉ የተወቀሰው ሰራዊት አሁን በጅምላ ግድያ እየተወነጀለ ነው፡፡ በሌላ በኩል በክልል ደረጃ የሚከሰቱ የብሄር ግጭቶች ፌደራላዊ ሥርዓቱን ከመሠረቱ እስካልነቀነቁት ድረስ ኢሕአዴግ የህግ ተጠያቂነት ባለማስፈን ጭምር ሲያስታምማቸው እናያለን፡፡ ይሄ ምን ያሳየናል? ብንል መንግስት ከጸጥታ ጥበቃ ያለፈ ስውር ፖለቲካዊ አላማ እንዳለው ነው የምንታዘበው፡፡ በተለይ ክልሎች ጸጥታቸውን መቆጣጠር የማይችሉ አቅመ ቢሶች እንደሆኑ አድርጎ በማሳየት የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ የሚችለው ራሱ ብቻ መሆኑን እና ለዚህም መፍትሄው የተማከለ የጸጥታ አወቃቀር መሆኑን ማሳየት የሚፈልግ ይመስላል፡፡
ባጠቃላይ መደበኛ ጸጥታ ሃይሎች ከብሄረሰብ ውግንና ርቀው የሕዝቡን ደኅንነት ማስጠበቅ ካልቻሉ ወይም ተቋማዊ አንድነታቸው ከተናጋ ምን ሊከሰት ይችላል? ብለን እንጠይቅ፡፡ አሁን ባለው አካሄድ በርበርስ ግጭት በታመሱ ብዙ አፍሪካዊያን ሀገሮች እንደታየው ማህበረሰቦች በየአካባቢያቸው ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል ሲሉ በእንግሊዝኛው “self-defence units” ወይም “vigilante” የሚባሉ ሕገወጥ ታጣቂ ቡድኖችን እንዲፈጠሩ በር የመክፈት እድሉ ከፍ ያለ ይመስለኛል፡፡ የብሄር አደረጃጀቱም ለዚህ ምቹ ነው፡፡ ድርቱም ሆነ መንግስ የገቡበት ቀውስ ፖለቲካዊ መፍትሄ ሳይገኝለት የጸጥታ አያያዝን ማማከል ብቻ ችግሩን ያባብስ እንደሆነ እንጂ መፍትሄ አያስገኝም፡፡ ለዚህም ነው እኮ ከአንድ ወር በፊት በብሄራዊ የጸጥታ ምክር ቤቱ የተነደፈው የተማከለ ሀገራዊ የጸጥታ አጠባበቅ እቅድ እስካሁን ውጤት ያላመጣው፡፡
ሀኒ ሰለሞን– ገዥው ፓርቲ ከዚህ በኋላ ድሮ ወደነበረበት ሁኔታ ይመለሳል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ በአሁኑ የፖለቲካ ቀውስ ምን አዲስ ነገር ይወለዳል ብሎ መጠበቅ ይቻላል?
ቻላቸው ታደሰ- በርግጥ ኢሕአዴግ ወደነበረበት የሚመለስበት እድል ያከተመ ይመስላል፡፡ ይህ የሆነው ግን እንደ ኦሕዴድ እና ብአዴን ካሉት አባል ድርቶች ቀድሞ ህዝቡ አንኳር ጥያቄዎችን በማንሳቱ እንደሆነ መረሳት የለበትም፡፡
በኦሕዴድ እና ብአዴን ተመጣጣኝ የሥልጣን ባለቤትነትን እና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ጥያቄን ሊያነሱ እንደሚችሉ ይገመታል፡፡ ችግሩ ካሁኑ መሠረታዊ መፍትሄ ካልተሰጠው ውሎ አድሮ ድርቱን በማዕበል ማጥለቅለቁ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በተለይ የፓርላማ አባላት ጠቅላይ ሚንስትሩ ማብራሪያ ካልሰጡ ስብሰባ አንቀመጥም ከሚለው አቋማቸው አልፈው ተጨማሪ ጥያቄዎችን ካነሱ እና ከስራ አስፈጻሚው ጋር መናበብ ከቻሉ በድርጅቱ የሃይል ሚዛን ሁነኛ ተጽዕኖ የሚያሳርፍ አንድ ትልቅ ጅማሮ አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡ እኩል ቁጥር ያለው ስራ አስፈጻሚው ውሳኔ የሚያስተላልፈው በድምጽ በመሆኑ በተለይ ኦህዴድ ብቻ የሚያቀርበው ሃሳብ ተጽዕኖ የመፍጠር እድሉ አናሳ ነው የሚሆነው፡፡ የግንባሩ ህገ ደንብ ደሞ ማንኛወም አባል ድርጅት ከራሱ ጥቅም በፊት የግንባሩን እንድነት እና ጥቅም ማስቀደም እንዳለበት ያዛል፡፡
ያም ሆኖ አሁንም በግንባሩ ውስጥ ያለውን ያልተመጣጠነ የሃይል ሚዛን ከመሰረቱ የሚቀይር ውሳኔ ላይኖር ይችላል፡፡ በተለይ ሕወሃት በተጓዳኝ አዲሱን ሊቀመንበሩን ወደ ትግራይ በፍጥነት በማዛወር ክልሉን እና ራሱን ወደ ማጠናከር ማዘንበሉን እናያለን፡፡ በቅርቡም የሕወሃቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረ ጺዮን በሰጡት መግለጫ የህወሃት/ትግራይ የበላይነት እንደሌለ ሆኖም ግን የጥቃት ኢላማ እየሆነ ያለው የትግራይ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ፌደራላዊ ሥርዓቱ ጭምር መሆኑን መግለጻቸው ነባራዉ ሀኔታውን የመጠበቅ ፍላጎት እንዳልተቀየረ ነው የሚያሳየን፡፡ እንዲያውም የትግራይን ህዝብ ከፌደራላዊ ስርዓቱ ጋር አጣምረው መናገራቸው ብቸኛ የፌደራላዊ ሥርዓቱ ተቆርቋሪዎች እና ጠባቂዎች ሕወሃት እና የትግራይ ህዝብ መሆናቸውን ለመናገር ይመስላል፡፡ ይህም ጉዳዩን ወደ ብሄር በመመንዘር ኦሕዴድን እና ብአዴንን በጠባብ ብሄርተኝነት መክሰስ እንዲያመች መሆኑ ነው፡፡
አሁን ባለው ቅራኔ ወደ ህብረ ብሄራዊ ውህደት ፓርቲ ስለመቀየር መወያየት መቻሉ አጠራጣሪ ነው፡፡ አሁን ሥራ አስፈጻሚው ካልተወያየበት ደሞ በመጋቢቱ ጉባዔ ሊታይ አይችልም፡፡
ስብሰባው ባጠቃላይ የጸጥታ ሃይሎችን እና የፌደራላዊውን መንግስቱን አወቃቀር የበለጠ ከማማከል እንዲሁም የክልል መንግስታትን ስልጣን ከመሸርሸር ያለፈ ለሀገሪቱ ችግሮች መሰረታዊ ማሻሻያ የሚያመጣ አይመስልም፡፡ ከመግለጫውም የምናየው የድርጅቱን ውስጣዊ ዴሞክራሲያዊ ባህል እና ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የሚባሉ ዘዴዎችን ማጥበቅ መታሰቡን ነው የምንታዘበው፡፡ እነዚህ ደሞ ለውጥ ፈላጊ ሃይሎችን ለመጨፍለቅ የሚያውላቸው ስልቶቹ ናቸው ፡፡
https://youtu.be/AKlAWjvyAiQ