ዋዜማ ራዲዮ- 12 ወለል ከፍታ፣ 60ሺ ካሬ ስፋት ያለው ሒልተን አዲስ አበባ የአገሪቱ የመጀመርያው ባለ ኮከብ ሆቴል ነው፡፡ 50 ዓመቱን እየደፈነ ያለው ይህ ዕድሜ ጠገብ ሆቴል ወደ ግል ባለሐብቶች በጨረታ ይተላለፋል የሚል ዜና ከተሰማ አንድ ዓመት ደፍኗል፡፡ ሆኖም እስከዛሬም ተግባራዊ እንቅስቃሴ አልተካሄደም፡፡
ሆቴሉ የብዙ ቢሊየነሮችን ቀልብ መሳቡ መንግሥት ዐይኑን ሳያሽ ጠቀም ባለ ዋጋ ሊሸጠው እንደተዘጋጀ ሲነገር ሰንብቷል፡፡ ኾኖም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ከዛሬ ነገ ጨረታ ያወጣል ቢባልም ላለፉት ስድስት ወራት አንድም ተግባራዊ እንቅስቃሴ አልተካሄደም፡፡ የዱባዩ አልባዋርዲ፣ የሆንግኮንጉ ሻንግሪላና ሌሎች ሰባት የሩቅ ምሥራቅ የሆቴል ሰንሰለቶች የአገር ቤቱ ሰንሻይንን ጨምሮ ቀደም ሲል በጨረታው ለመሳተፍ ፍላጎት አሳይተዋል፡፡
አልባዋርዲ በሆቴል ገበያ አንድ እግሩን ወደ ኢትዮጵያ ያስገባው ከኩዌቱ አልካራፊ ኩባንያ መስቀል አደባባይ የሚገኙትን ባለ 4 እና ባለ 5 ኮከብ መንትያ ሆቴሎች በሰባት መቶ ሚሊዮን ብር ከገዛ በኋላ ነው፡፡ አሁን በጅምር ቀርተው የነበረቱን ሆቴሎቹን ግንባታ አጠናቆ የዉጭ ገጽታቸውን በነጭ ቀለም አድምቆ ዉስጣዊ ቀሪ ማጠናቀቂያ ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡
ከወዳጃቸው ከአቶ አብነት ገብረመስቀል ጋር በመሆን ከወራት በፊት በሒልተን ጉብኝት ያደረጉት የሳኡዲው ቢሊየነር ሼክ ሙሐመድ አላሙዲ የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽነር የሆኑትን ዶክተር ይናገር ደሴን ‹‹ተደራድሬ ልግዛችሁ›› የሚል ጥያቄን አቅርበውላቸው እንደነበር ተሰምቷል፡፡ እስከ 7 ቢሊየን ብር ለመክፈል እንደሚደፍሩ ጭምር በመግለጽ፡፡ ዶክተር ይናገር የሒልተን ሆቴል ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ናቸው፡፡
ሒልተን ይሸጣል ከተባለ አንስቶ እስካሁን ለምን ጨረታ ሳይወጣ ቀረ የሚል ጥያቄ ለውስጥ አዋቂዎች ያነሳችው ዋዜማ ጉዳዩ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተረድታለች፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅትን የጠቀለለው አየር መንገድ በሆቴልና ቱሪዝም ላይ በልበ ሙሉነት እንድሠራ ከተፈለገ ሒልተን ለኔ ተላልፎ ሊሰጠኝ ይገባል የሚል ጥያቄ ማንሳቱ ተወስቷል፡፡
በሐምሌ 2009 የመጀመርያ ሳምንት የተሰበሰበው የአቶ ኃይለማርያም ሥራ አስፈጻሚ የኢትዮጵያ አየር መንገድንና የኤርፖርቶች ድርጅትን በአንድ ለመጨፍለቅ የቀረበለትን ረቂቅ አዋጅ ማጽደቁ ይታወሳል፡፡ መንግሥት ከዚህ ዉሳኔ ላይ መድረስ የቻለው የኤርፖርቶች ድርጅት በብዙ ዉጭ ምንዛሬና በብድር የሚገቡ አውሮፕላኖችን የሚያስተናግድ የመሠረተ ልማት ሥራ በፍጥነት፣ በቅልጥፍናና ዓለማቀፍ ዉድድርን ለማሸነፍ በሚረዳ መልኩ ሊያካሄድ ባለመቻሉና ለዚህ የሚያበቃ ቁመና ላይ ባለመሆኑም ጭምር ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ሠራተኛ ሳይቀነስ የመዋቅር ማስተካከያ ማካሄድ አስፈላጊ ሆኗል፡፡
አየር መንገድና ኤርፖርቶችን የሚጠቀልለው አዲሱ መዋቅር የአቪየሽን ቡድን የሚል መጠርያ የሚኖረው ሲሆን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ከሚንቀሳቀስባቸው ዘርፎች መካከል ቱሪዝምና የሆቴል ልማት ይገኙበታል፡፡ ለዚህም ነው ሥራ አስፈጻሚው አቶ ተወልደ ሒልተን ይሰጠኝ እያሉ እየወተወቱ ያሉት ተብሏል፡፡ ሒልተን የአቪየሽን ቡድን ዉስጥ ከገባ ዘመናዊ አስተዳደርን በመጠቀም አገሪቱ ላይ ሰፊ የቱሪዝም ሥራዎችን ለመሥራት ያስችለናል ይላሉ የሥራ አስፈጻሚውን ጥያቄ የሚደግፉ የሀሳቡ አቀንቃኞች፡፡
አየር መንገዱ በዚህ ወቅት በቦሌ ጫፍ ከሚሊንየም አዳራሽ ፊትለፊት አዲስና ግዙፍ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ገንብቶ እያጠናቀቀ ይገኛል፡፡ በአገሪቱ ባልተለመደ ፍጥነት ቻይና ናሽናል ኤሮ ቴክኖሎጂ እየገነባው የሚገኘው ይህ ሆቴል ቀድሞ 4 ኮከብ ደረጃ ታሳቢ ተደርጎ የተጀመረ ነበር፡፡ በ40ሺ ካሬ ላይ ያረፈው ይህ የአየር መንገድ ሆቴል በአሁኑ ሰዓት የማጠናቀቂያ ሥራዎች እየተሠሩለት ይገኛሉ፡፡
አየር መንገዱ ከዓመታት በፊት በግዮን ሆቴል ላይ ተመሳሳይ ‹‹የተላልፎ ይሰጠኝ›› ጥያቄ ማንሳቱ ይታወሳል፡፡ ኾኖም መንግሥት ተከታታይ ጨረታዎችን አውጥቶ ግዮንን ለመሸጥ ሙከራው በተለያዩ ምክንያቶች ዉጤታማ ሳይሆንለት ሲቀር ግዮን ሆቴል ከታችኛው ቤተመንግሥትና ከፍልዉሀ ጋር ተቀላቅሎ ወደ ከተማ ፓርክነት እንዲለወጥ ዉሳኔ አሳልፏል፡፡ በዚህም የተነሳ በአሁኑ ወቅት የርዕሰ ብሔሩ መቀመጫ ወደ ሽሮ ሜዳ በመዛወር ላይ ይገኛል፡፡
ሒልተን አዲስ አበባ በአሜሪካዊው ቻርለስ ዋርነር እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1960ዎቹ አጋማሽ የተደዘነ ሲሆን የብሉይ ኪነሕንጻን ሥነ ዉበት የያዘና የላሊበላ ዉቅር አብያተ ክርስቲያንን መሠረት አድርጎ የተገነባ ነው፡፡ ዋናው የሆቴሉ መግቢያም ሆነ መዋኛው በመስቀል ቅርጽ የተሠሩ ሲሆን በዉጭ ገጽታው ላይ የሚታዩ ትንንሽ የጌጥ መስኮቶች ደግሞ የላሊበላ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚገኙ ማጮለቂያዎችን ይወክላል፡፡
ሒልተን በአሁኑ ሰዓት በሠራተኛውና በማኔጀመንቱ መካከል ከፍ ያለ ዉዝግብን እያስተናገደ የሚገኝ ሲሆን የሆቴል ደረጃውም ወደ ሦስት ኮከብ ወርዷል፡፡