Book Cover- Shenkuteዋዜማ ራዲዮ- ሁሉም አገር አንድ ጀግና ሊወልድ ይችላል፡፡ አንድ ቤተሰብ እንዴት ሙሉ ጅግና ይወልዳል? የሸንቁጥ ቤተሰብ የሚገርመን ለዚህ ነው፡፡ ቀኛዝማች ሸንቁጥ ደራጅ ከወይዘሮ ማሚቴ ሙሉነህ የወለዷቸው እነ ተሾመ ሸንቁጥ፣ ኃይሌ ሸንቁጥ፣ አበበ ሸንቁጥ፣ ይነሱ ሸንቁጥና ጥላሁን ሸንቁጥ ጣሊያንን ሲያራዉጡ የኖሩ የአንድ እናት የአንድ አባት ልጆች ናቸው፡፡ ከሰሞኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ የሸለመን መጽሐፍም ይህንኑ ነው፡፡ የሸንቁጥ ልጆች ይሰኛል፣ በርዕሱ፡፡ 

###

ይህ መጽሐፍ ታሪካዊ ነው፡፡ አጻጻፉም ጭምር፡፡ ሰሞኑን ለገበያ ይቅረብ እንጂ የተጠነሰሰው በ1937፣ መጋቢት ወር ላይ ነው፡፡ ያኔ በጽሕፈት ሚኒስትር የታሪክና ቤተ መንግሥት ዜና ማሰናጃ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ብላታ መርስሄ ኀዘን ወልደቂርቆስ ደብዳቤ ይጽፋሉ፡፡ ለማን? ለደጃዝማች ተሾመ ሸንቁጥ፡፡ ምን ብለው? በ5ቱ ዓመታት የአርበኝነት ዘመን በርሳቸውና በሌላው አካባቢ የሚታወቀውን ታሪክ እንዲያዘጋጁ፡፡ ማን? ደጃዝማች ተሾመ ሸንቁጥ፡፡

ደጃዝማች ተሾመ ያኔ ትዕዛዙን ይፈጽሙ አይፈጽሙ የታወቀ ነገር የለም፡፡ ኾኖም እርሳቸው እንደጻፉት የሚገመት ባለ 93 ገጽ አንድ የታሪክ ረቂቅ ይገኛል፡፡ (አምባሳደር) ዓለማየሁ አበበ ሸንቁጥ ከዘመን በኋላ ያን ረቂቅ መሠረት አድርገው ሌሎች የአርበኞችን ቃልና ተያየዥ ሰነዶች ጨማምረው የመጽሐፍ ቅርጽ ያሲዙታል፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ በረቂቁ ይመሰጣል፡፡ የሸንቁጥ ልጆች ይወለዳል፡፡

የሚገርመው ጸሐፊው በአራት ዓመታቸው የአርበኝነት ሕይወትን በስሱ ተመልክተዋል፡፡ በሰማንያ ዓመታቸው መጽሐፍ የኅትመት ብርሃን ዐየ፡፡

ለሸንቁጥ ልጆች ድርሳን ልባስነት የተመረጠው ምስል ለአንባቢያን እንግዳ አይደለም፡፡ ከእዚህ ቀደም ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም “አዳፍኔ” ለተባለው መጽሐፍ በጀርባ ልባስነት ተጠቅመውበታል፡፡ምስሉ በመረሃቤቴ አውራጃ ይደመቆ ተራራ ላይ ወራሪውን የፋሽስት ኃይልን ያንቀጠቀጡ ትንታግ አርበኞች የድል አድራጊ ስሜትን ተላብሰው የተነሱት ግርማ ሞገስ ያለው ፎቶ ነው፡፡በምስሉ ወስጥ ከታቀፉት ጥቁር አናብስት መሀል ደግሞ የታሪኩ ዋና ተዋናያን ተሾመ ሸንቁጥ እና ልጅ አበበ ሸንቁጥ ይገኙበታል፡፡

ለአርበኝነት ወደ አገር ቤት መመለስ

ልጅ አበበ ሸንቁጥ በወቅቱ በቀለም ከተራመዱ እፍኝ ከማይሞሉ ሊኅቃን መሀል የሚደመሩ ነበሩ፡፡ግብጽ ሀገር ድረስ ሄደው አስኳላን የበጠሱ ግሩም ሊኅቅ ናቸው፡፡በፓስታ እና በቴሌኮሚኒኬሽን ድርጅት ውስጥ በኃላፊነት የሥራ ዘርፍ ሀገራቸውን እና ወገናችን እያገለገሉ ጥቂት ዓመታትን እንደሰነበቱ ጣሊያን ለዳግም ወረራ ማይጨው ላይ ጦርነት መክፈቱ ተሰማ፡፡ወራሪው ኃይል ሳይውል ሳያድር ከመሀል ሀገር እግሩን መተክል እንደማይሳነው ወለል ብሎ ሲታያቸው፣ ጓዝ ንብረታቸውን እና ብቸኛ ፍሬያቸውን ዓለማየሁ አበበ ሸንቁጥ(በኋላ አምባሳደር እና የመጽሐፉ አሰናጅ)ን አንደ ጆሮ ጌጥ አንጠልጥለው ለነፃነት ተጋድሎ ከትውልድ ቀያቸው መርሃቤቴ ተከተቱ፡፡ምንአልባትም በወቅቱ እንደነበሩ ባንዳዎች ግብዝነት ዘልቆ  ቢገባቸው ኖሮ ቆላ ሳይወርዱ ደጋ ሳይወጡ ጣሊያን በሚጥልላቸው ዳረጎት በሎሌነት ሕይወት ለማዝገም ራሳቸውን ያዘጋጁ ነበር፡፡ልጅ አበበ ሽንቁጥ ግን ዘመናቸውን የቀደሙ ጉምቱ ባለታሪክ ስለነበሩ ለሀገራቸው ነፃነት አምስት ዓመት ሙሉ በጋራ ተረተሩ ለመባጅት እና ወራሪውን ፀጉረ ልውጥ ኃይል ለመሸንቆጥ ተሰናዱ፡፡

ሸንቁጥ ከስም በላይ ርቆ የሚሄድ ግሩም የግብር መገለጫ ነው፡፡ስያሜው እንደው ለይስምላ መጠሪያ እንዳልሆነ በመጽሐፉ መግቢያ ላይ የተብራራው ትንታኔ ማሳያ ይሆናል፡፡ ደስታ ተክለወልድ ዘ ሀገረ ወግዳ እንደ መዝገበ ቃል ሽንቁጥ ማለት ሸነቀጠ ከሚል ግስ የወጣ ተኮሳተረ፣ቀለጠፈ ሲል ይተረጉመዋል፡፡ሸንቁጥ ወይም ሸንቁጤ ሲሆን የሰው ስም ሆኖ ያገለግላል፡፡ሸንቁጥ ማለት ጠላታችንን ግረፍ ማለት ነው ብሎታል፡፡

ስምን መላክ ያወጠዋል የሚለው ብሂል ከሸንቁጥ ልጆች አሀዱ ብሎ የጀመረ ይመስላል፡፡ሸንቁጥ ደራጅ በአድዋ ጦርነት ላይ ከባድ ጀብዱ የሠሩ ጀግና ኢትየጲያዊ ነበሩ፡፡የእኝህ ጉምቱ አዛውንት አብራክ ያፈራቸው ተሾመ ሸንቁጥ፣ኃይሌ ሸንቁጥ፣አበበ ሸንቁጥ፣ይነሱ ሸንቁጥና ጥላሁን ሸንቁጥ በመርሃቤቴ አካባቢ ለሀገራቸው ነፃነት የከፈሉት መስዋዕትን በእዚህ አጭር ድርሳን ላይ ከጅምሩ እስከመቋጫው ይተነተናል፡፡ ለምሳሌ ገጽ 13 የቤተሰቡን አጠቃላይ ተጋድሎ በአጭሩ እንዲህ ያስቃኘናል፤

ከጀኔራል ናዚና ከዱካ ደ አውስታ ታር የነበረው ጁሴፒ ማረሊዮ የተባለ ጣሊያናዊ የታሪክ ጸሐፊ “ፍራቴሊ ሸንቁጥ” ወይም “ወንድማማቾቹ የሸንቁጥ ልጆች”በሚል ርዕስ በጻፈው ጽሑፍ ላይ፤ በመርሃቤቴ ተመሳሳይና ተወዳዳሪ ከማይገኘላቸው ጥቂት የጦር ሰዎች መካከል በላይኛው መስመር ላይ ይገኛሉ ሲል ያደንቃቸዋል፡፡

እኛም ይህን ቤተሰብ አለማድነቅ አንችልም፡፡ ለምን ማለት ጥሩ ነው፡፡ ግራዝማች ተሾመ ሸንቁጥ (በጦር ሜዳ በጠላት ጥይት ሰውነታቸው እንደ ወንፊት የተበሳሳ (በኋላ ደጅዝማች) ልጅ ኃይሌ ሸንቁጥ(በጦር ሜዳ በጀግንነት ሲዋጉ ከባድ የመቁሰል አደጋ ስለደረሰባቸው በጠላት ኃይል አንገታቸው ተቀልቶ ራሳቸው የተወሰደ)፣ልጅ አበበ ሸንቁጥ (እጅግ በርካታ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸው ለተዓምር የተረፉ(በኋላ ደጅአዝማች)፣ልጅ ይነሱ ሸንቁጥ (በጦር ሜዳ ተሰውተው ከአረመኔው የፋሺስት ጦር ጋር ተባባሪ የነበረው የራያና አዘቦ ዘማች አማካይነት ሰውነታቸው ተቆራርጦ የተወሰደ)፤ ልጅ ጥላሁን ሸንቁጥ(በጦር ሜዳ ተሰውተው አንገታቸው በጠላት ተቆልቶ ሬሳቸው)የተወሰደ በመኾናቸው፡፡

ጣሊያን ኢትዮጲያን የመውረሯን ዕቅድ በሌሎች የሀገሪቱ ሕዝቦች ዘንድ ቅቡልነት እንዲያገኝ የመረጠችው ስልት ፀረ ሸዋ አማራ አገዛዝን መስበክ ነበር፡፡ ይህ በፀጉረ ልውጥ ወራሪ ኃይል እንደዋዛ የተነዛው የጨቋኝ-ተጨቋኝ ብሔር ቁርኝትን(oppressor -oppressed dichotomy) መሠረት ያደረገ ማደናገሪያ ፕሮፓጋንዳ ውሎ አድሮ በኢትዮጵያ ፓለቲካዊ ምህዳር ላይ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ሊተከል ችሏል፡፡ከ1960ዎቹ ወዲህ በመጡ ዘዉግ ተኮር ፓለቲካ ግምባሮች ላይ የጣሊያንን ፕሮፖጋንዳ እንደወረደ በማጥለቅ ዳይኮቶሚያዊው ቅኝቱን እንደዋንኛ ማታጊያ ስልት ተጠቅመውበታል፡፡ ለማሳያ ያህል ገጽ 8 ላይ ከሰፈረው የጣሊያን ፕሮፖጋንዳ በመጽሐፉ ተጠቅሷል፡፡

“…ወደ ኢትዮጲያ የምሄደው አገሪቱን ለመያዝና በቅኝ ግዛትነት ለማስተዳደር ሳይሆን ሕዝቧን ከጨቋኙ የፊውዳል ስርዓትና ከሸዋ ተገዥነት ለማላቀቅና ለማሰልጠን ነው ብሎ ጄኔራል ዲ ቦኖ የተናገረው ምን ያህል በቅጥፈት ዓለምን ለማሳመን እንደጣሩ የሚያሳይ ነበር፡፡ “

የባንዳ ሕያውነት

የሰሜኑ በዝብዝ ካሳ በአጼ ቴዎድሮስ ላይ በሰሩት ሸፍጥ ምክንያት ባንዳነት በሀገራችን አፈር ላይ እንዲበቅል ዘር ተዘራ፡፡በሀገራችን ሰማይ ላይ የባንዳ ጎህ ቀደደ፡፡ ይህ መጽሐፍ ስለ ባንዳነት ብዙ ይላል፡፡ በቅድሚያ ግን ስለ ባንዳ ታሪካዊ ዳራ  የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም አዳፍኔ  በገጽ 8 ላይ ከተነተነው በጥቂቱ እናስታውስ፡፡

ሕዝብ ህልውናን የሚጠብቀውን ጀግንነት እና አርበኝነት እያወደሰ እና እያሞገሰ እየሸለመና እያከበረ መኖርን ባህሉ አደረገ፡፡ይህ ባህል ጀግንነትና አርበኝነትን ማክበር ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብንም እርበእርሱ የሚመዛዘንበትና የሚከባበርበት መለኪያ ሆኖት ቆየ ፤ትዳርም ሆነ ንብረት፣ተሰሚነትም ሆነ ኃላፊነት ክብር መፍለቂያ ጀግንነትና አርበኝነት ነበሩ፡፡ከአሥራ ዘጠኛው ምዕተ ዓመት ግን በኋላ አጼ ዮሐንስ የሆኑት በዝብዛ ከሳ ይህንን የቆየውን ሕልውና ሕግ ሽረውታል፡፡ (በባንዳነት)

በዝብዝ ካሳ የከፈቱት ምዕራፍ በዘመናት ሒደት ፍሬ አፍርቶ እና ጎምርቶ በአምስት ዓመቱ የጣሊያን ወራራ ወቅት ባንዳነት የውርደት፣የተለመጥማጭነት እና የሎሌነት መለዮነቱ ቀርቶ በክብር ቀና ብለው የሚሄዱበት ተመራጭ ስብዕና ሆኖ አረፈው፡፡ ባንዳ ለሃገር ለወገኑ ቅንጣት ያህል ርህራሄ ያልፈጠረበት፣ የሰውነት ክብሩን የሸጠ ጥቅም ያወረው ገብዝ ፍጡር ነው፡፡

የሸንቁጥ ልጆች ከሌሎች መሰል ድርሳናት ከሚለይበት አብይ ነጥብ አንዱ የባንዳን አይነት እና መጠን በተገቢው ደረጃ ለመፈተሸ መቻሉ ነው፡፡ነገሩን ወለፈንዲ የሚያደርገው ከባንዳ ባሕል ጋር ኩታገጠም ለመሆን ፓለቲካዊ፣ታሪካዊ እና መልካምድራዊ ነባራዊ ሁኔታዎች የሚያግደው የሸዋ አካባቢ በእዚህ በካይ ማንነት መጠመቁ ነው፡፡የሸንቁጥ ልጆች ጉሮሮ ለጉሮሮ እየተናነቁ የሚጠሉት ግዳይ ብዙውን እጅ የሚሸፍነው የባንዳ ሰራዊት እንደሆነ በእየምዕራፍ የተቀመጡት የትግል ታሪኮች በቂ ናቸው፡፡

ኮላሽ ምሽግ የድል ማማ፣አመጻ ዋሻ የሰቆቃ ደብር

ኮላሽ ምሽግ በሸንቁጥ ልጆች ተጋድሎ ታሪክ ላይ በጉልህ የሚነሳ የትግል አውድ ነው ፡፡ፍልሚያውን የመሩት ልጅ አበበ ሸንቁጥ ናቸው፡፡ሠራዊታቸው የጠላትን ጦር እንደህል እያበራየ ለአርበኝነቱ ትግል ወሳኝነት ያለውን እና ገዥ መሬት የሆነውን ኮላሽ ምሽግን ተቆጣጠረ፡፡የአበበ ሸንቁጥ ሠራዊት ኮላሽ ምሽግን ሲቆጣጠር በጠላት ሠራዊት ዘንድ የደረሰው ኪሳራ ከቁጥር በላይ ነበር፡፡በእዚህም ምክነያት በጠላት ካምፕ ዘንድ የሸንቁ ልጆች ዝና ይበልጥ ናኘ፡፡በድሉ ደስታውን መቆጣጠር የተሳነው ሀገሬው ይህንን ስንኝ ለጀብዳቸው ገጠመላቸው፣

             መውዜሩን ነዳፊ የበረሃ ጊንጥ

             ኮላሽ ላይ ብቅ አለ አበበ ሸንቁጥ

             መከራ አረገዘ ጣሊያን ያዘው ምጥ

             በየምሽጉ ሥር ዋለ ሲራወጥ፡፡

##########