ዋዜማ ራዲዮ- አዲስ አበባ የሀገራችን መዲና ከመሆን ባሻገር የአፍሪቃ ህብረትና የተለያዩ አለም ዓቀፍ ተቋማት መቀመጫ ናት። ከተማይቱ ባለፉት ሀያ አመታት በእጅጉ ተለውጣለች። አዳዲስ ህንፃዎች ተገንብተዋል። ይሁንና አዲስ አበባ በብዙ መስፈርቶች ስሟን በበጎ ለማስጠራት አልተቻላትም። የውሀ የመብራት የትራንስፖርት የመኖሪያ ቤት የቆሻሻ አወጋገድና የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ከተማይቱ ከዕለት ዕለት አስከፊ ፈተና እየገጠማት ነው። ከችግሮቹ አንዱ ከተማይቱን የሚያስተዳድሩት ባለስልጣናት ከተማይቱን የሚያውቋት አለመሆናቸው ነው። ሙስናና ገዥው ፓርቲ በአዲስ አበባ ላይ የያዘው የተዛባ አቋምም የአዲስ አበባን መፃዒ ዕድል ድንግዝግዝ አድርጎታል። ዳንኤል ድርሻ ያሰናዳውን እነሆ ።
130 ዓመት ዕድሜ ስላስቆጠረችው አዲስ አበባ ከዓለም አቀፍ ተቋማት የተለያዩ መረጃዎች ይሰጣሉ፡፡ ሮክፌለር ፋውንዴሽን ከሠሞኑ “ከችግር ቶሎ የሚያገግሙ 100 ከተማዎች” መሐል አዲስ አበባ ትገኛለች በማለት ከሌሎች 11 የአፍሪካ ከተማዎች ተርታ አሠልፏታል፡፡ በሮክፌለር ምርጫ የተደሰቱት ከንቲባ ድሪባ ኩማ በ“እንኳን ደስ ያለን” መልዕክት ተጠምደው ሠንብተዋል፡፡ “ሲ 40” (አርባዎቹ ከተማዎች) የተባለ በሜክሲኮ ሲቲ የሚገኝ ቡድን፣ በዲሴምበር 2016 መጀመሪያ፣ አዲስ አበባ ለአየር ብክለትና አካባቢ ጥበቃ ባበረከተችው አስተዋጽኦ ተሸላሚ መሆኗን ገልጿል፤ የሲ 40 ከንቲባዎች ለስብሰባ ሲገናኙ ሽልማቱ እንደሚበረከትም አሳውቋል፡፡ አሳዛኙ ነገር፣ ሌላ ተቋም ባካሄደው ፍተሻ ሸላሚዋ ሜክሲኮ ሲቲም ሆነች ተሸላሚዋ አዲስ አበባ ከዓለማችን 10 ቆሻሻ ከተማዎች ምድብ ውስጥ መካተታቸው ነው፡፡
አዲሳባ ምን አላት?
በአየር ብክለት፣ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት፣ የመጸዳጃ ቤትና ንጹሕ ውሃ አቅርቦት፣ በሕክምና፣ አረንጓዴ ልማት፣ ለተላላፊ በሽታዎች ባለማጋለጥ ዙሪያ በ215 ከተማዎች በተካሄደ ጥናት አዲስ አበባ ከውራዎቹ ስድስት ከተማዎች መካተቷ ተገልጾ ነበር፡፡ በፎርብስ ማጋዚን መረጃ መሰረት ከአዘርባይጃኗ ባኩ፣ ከዳካ (ባንግላዴሽ)፣ ከአንታናናሪቮ (ማዳጋስካር)፣ ከፖርት ኦ ፕሪንስ (ሐይቲ)፣ ከሜክሲኮ ሲቲ (ሜክሲኮ) በመቀጠል የአፍሪካ ርዕሰ መዲና የዓለማችን 6ኛዋ ቆሻሻ ከተማ ደረጃን አግኝታለች፡፡ በ1600 የዓለማችን ከተማዎች የተካሄደ የዓለም ጤና ድርጅት ጥናት አዲስ አበባ ወደ ዘመናዊነት ለመጠጋት ከሚያስችላት መስፈርት በብዙ ርቃ መገኘቷን ያመላክታል፡፡
በ450 ከተማዎች ላይ ሠፋ ያለ ጥናት የሠራው ሜርሠር (MERCER) የተሰኘው ማዕከል ከሠሞኑ ይፋ እንዳደረገው… ለኗሪዎቻቸው አይበጁም፣ የከተማ ልማት ችግር ይስተዋልባቸዋል ካላቸው ምቹ ያልሆኑ ሥፍራዎች አዲስ አበባን በ24ኛ ደረጃ አስቀምጧታል፡፡ ሜርሠር ለመሥፈርትነት የተጠቀመባቸው እና አዲስ አበባ ተፈትና ከወደቀችባቸው ነጥቦች ወስጥ… የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ወንጀል፣ የሕግ የበላይነት፣ የባንክ አገልግሎት፣ የመገናኛ ብዙሃንና ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት፣ ሴንሰርሺፕ፣ የሕክምና አገልግሎት፣ የቆሻሻና ፍሳሽ አወጋገድ፣ መጸዳጃ ቤትና ንጹሕ ውሃ፣ ለተላላፊ በሽታዎች ተጋላጭነት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ትራንስፖርት፣ ቲያትር፣ ሲኒማና ስፖርት ማዕከላት መኖር፣ የመኖሪያ ቤት፣ የተፈጥሮ አደጋን የመቋቋም ቅድመ ዝግጅት፣ የአካባቢ ጥበቃ… የመሳሰሉት ተጠቅሰዋል፡፡
በዓለም ጤና ድርጅትና ሜርሠር ጥናት 37.9 ነጥብ የተሰጣት አዲስ አበባ በዓለማችን አሳሳቢ የመጸዳጃ ቤት ችግር ካለባቸው ከተማዎች በቀዳሚነት ተጠቅሳለች፡፡ በከተማይቱ የሚፈሱ ወንዞች ንጽሕናቸው ያልተጠበቀ፣ ለተዛማች በሽታዎች የተጋለጡ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ከሆስፒታሎችና ፋብሪካዎች የሚለቀቁ ፈሳሾችና ኬሚካሎች ለመጠጥ አገልግሎት የሚውሉ ወንዞችን ሳይቀር በመበከል ላይ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ቢሮ አካሂዶት በነበረ ለከተማይቱ መጠጥ አገልግሎት የሚውለው የአባ ሳሙኤል ሐይቅ 50 % (ማለትም ገሚሱ) በአረም ተሸፍኗል፡፡ ችግሩ አሳስቦኛል ያለው የከተማ አስተዳደሩ፣ ያልተማከለ አሰራርን በመተግበር አስሩ ክፍለ ከተማዎች ተከፋፍለው ወደ ማጽዳት ሥራ እንዲገቡ ትዕዛዝ ማስተላለፉን ቢያሳውቅም እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ መመልከት አልተቻለም፡፡ ሁኔታው ያሳሰበው የሚመስለው መንግስታዊ ያልሆነው “ሐቢታት ኢትዮጵያ” ወንዞቹን ለማጽዳት የሚያስችል ጥናት መጀመሩን ባለፈው ጥቅምት ወር አሳውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ጥም ይበረታል
“የአፍሪካ የውሀ ማማ” እየተባለች በምትሞካሸው ሃገር… ዋና ከተማ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ ማግኘት አዳጋች ነው፡፡ የከተማ አስተዳደሩ የንጹሕ ውሃ ሽፋን 97 % ደርሷል ይበል እንጂ በአፍሪካ ሕብረት መቀመጫዋ ከተማ የጉድጓድ ውሀ ተጠቃሚ ማሕበረሰብ ብዛት ጥቂት የሚባል አይደለም፡፡ የቧንቧ ውሃ በሳምንት… ባስ ሲልም በወር አንዴ ማግኘትም የተለመደ ሆኗል፡፡ ከማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው የአዲስ አበባ ሕዝብ ብዛት ከ100,000 ወደ 2.7 ሚሊየን ለማደግ የፈጀበት 50 ዓመት ብቻ ነው፡፡ እ.አ.አ በ2020 ማለትም ከሶስት ዓመት በኋላ ይሕ አሃዝ በእጥፍ እንደሚጨምር “ዩኤን ሃቢታት” ይገልጻል፡፡ ሌሎች መረጃዎች ደግሞ በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ነዋሪ ከ4.5 ቢበልጥ እንጂ እንደማያንስ ይጠቁማሉ፡፡
የአ.አ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን… በከተማዋ የንጹሕ መጠጥ ውሃ ሽፋን 97 % መድረሱን ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ከ15 ዓመት በፊት በቀን 204 ሺህ ሜትር ኩብ የነበረው የከተማይቱ የንጹሕ መጠጥ ውሃ ፍላጎት የዛሬ ሁለት ዓመት ወደ 431 ሜ.ኩ ጨምሯል፤ በ2020 ደግሞ ፍላጎቱ ወደ 1.1 ሚሊየን ሜ.ኩ ያሻቅባል፡፡ ይሕ ሲሰላ የሕዝብ ብዛቱና የውሃ አቅርቦቱ ፈጽሞ ለንጽጽር የሚበቃ አይደለም፡፡ በአቃቂ ወንዝ ተፋሰስ ለምትገኘው አዲስ አበባ… ከጉድጓዶች ውጪ ዛሬም ዋነኛ የውሃ ምንጮች ከ40ና 50 ዓመት በፊት የተሰሩት ለገዳዲ፣ ገፈርሳ፣ አባ ሳሙኤል ናቸው፤ ለለገዳዲ ግድብ ውሃ አቅርቦት የተገነባው ድሬ ግድብም አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ሁለት አሰርት ዓመታትን አሳልፏል፡፡ የአ.አ ውሀና ፍሳሽ ባለሥልጣን መስሪያ ቤት… ከ5 ዓመት በፊት 85 ሊትር የነበረውን ዕለታዊ የውሀ የነፍስ ወከፍ ፍጆታ በቅርቡ ወደ 100 ሊትር አሳድጋለሁ የሚል ስሌት ቢያሠላም ሕዝቡ ከቁጥሩ ያተረፈው ነገር የለም፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናትም የተባለው የ97 % ሽፋን የሌለ መሆኑን ያጋልጣል፤ በዩኒቨርሲቲው የአ.አ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲቲዩት ባደረገው ጥናት ተጣርቶ ወደ ሕዝቡ ከሚላከው ውሃ 37 % ለተገልጋዩ ሳይደርስ መንገድ ላይ ባክኖ ይቀራል፡፡ ለብክነቱ ዋናው ምክንያት ደግሞ የበሰበሱ ቧንቧዎች ናቸው፡፡ 5000 ኪሎ ሜትር ከሚደርሰው የአዲስ አበባ ቧንቧ ግማሽ ያሕሉ ከተዘረጋ 25 ዓመት አልፎታል፡፡
የፍሳሽም ሆነ ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓቱ ኋላቀርና የዘመናዊ ከተማ ልማትን የተከተለ አይደለም፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተዘጋጀው የቆሬ ቆሼ መጣያ በመሙላቱ ቆሻሻ የሚጣልበት ጠፍቶ… በከተማይቱ የቆሻሻ ክምር መመልከት የተለመደ ነው፡፡ ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ወጥቶበታል የተባለው የሠንዳፋ ‹‹ሳኒተሪ ላንድ ፊል›› ለአንድ ሳምንት ብቻ አገልግሎት ሰጥቶ ተዘግቷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ቆሻሻ መጣያው የተዘጋጀው በአርሶአደሮች ይዞታ በመሆኑ በተቀሰቀሰ ሕዝባዊ ተቃውሞ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በአማራጭ እጦት የቆሬ ቆሻሻ በትራክተር ከታረሰ በኋላ ወደ አገልግሎት ቢመለስም ከጊዜያዊ መፍትሔነት የሚዘል ግን አይደለም፡፡ የአፍሪካ መዲናዋ ያለ ዘላቂ ቆሻሻ ማስወገጃ እስከመቼ እንደምታዘግምም የሚታወቅ ነገር የለም፡፡
ጭለማ ብርቅ አይደለም
ለዓመታት የዘለቀው “ያልታወጀ” የኤሌክትሪክ ኃይል ፈረቃ በቅርብ ጊዜ መፍትሔ የሚያገኝ አይመስልም፡፡ አዲስ አበቤም ያለ መብራትና ኤሌክትሪክ መዝለቁን ተለማምዷል፡፡ በነፍስ ወከፍ የኤሌክትሪክ ዕደላ ኢትዮጵያ ከአሕጉሪቱ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ነው የምትገኘው፡፡ የመብራት ኃይል መስሪያ ቤት ለ20 ዓመት የሚዘልቅ የከተማይቱን ኤሌክትሪክ ማስተር ፕላን እያዘጋጀ መሆኑን ከገለጸ ረዥም ጊዜ ተቆጥሯል፡፡ ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ 3.5 ሚሊየን ዶላር የአዲስ አበባና ዙሪያዋን የኤሌክትሪክ ሥርጭት ችግር ለመፍታት ያስችላል የተባለው የማስተር ፕላኑ የመጨረሻ ረቂቅ ከተዘጋጀ ከአንድ ዓመት በኋላ መዲናይቱ በኃይል እጥረት መታመሷ ቀጥሏል፡፡
መሰረታዊ የሆነው የኢንተርኔት አገልግሎት ሸገር ላይ ቅንጦት ሆኗል፡፡ ከ3 % ያላለፈ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ባላት ሃገር… ቀርፋፋና የተገደበውን አገልግሎት የፖለቲካዊ ግለት ሲጨምር ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ ይደረጋል፡፡
ሀምሳ አመት ስንት ነው?
የመኖሪያ ቤት እጥረት የአዲሳባ የማይፈታ ችግር መስሏል፡፡ የ2015 የናይት ፍራንክ መረጃ (2015 Knight Frank Wealth Report) አዲስ አበባ በዚህ ረገድ የ3.8 ዕድገት ማሳየቷን ይግለጽ እንጂ የነዋሪው ፍላጎትና የሚሰራው የቤት መጠን ግን ፈጽሞ የሚጣጣም አልሆነም፡፡ መንግሥት ከግል ሪል ስቴት ባለቤቶች ጋር በመሆን በየዓመቱ 100 ሺህ ቤት ለመስራት ዕቅድ መያዙን በቅርቡ የገለጸ ሲሆን፣ የተመድ መረጃ ደግሞ ችግሩን ለመፍታት ቢያንስ 300 ሺህ አዳዲስ ቤቶችን መሥራት እንደሚገባ ይጠቁማል፡፡ አሁን በተያዘው የመንግሥት አካሄድ ግን በአዲስ አበባ ከተማ ከ10 ዓመት በፊት ለተመዘገቡ የጋራ መኖሪያ ቤት ፈላጊዎች ብቻ ቤት ሠርቶ ለማዳረስ 50 ዓመት ያስፈልጋል፡፡
የትራንስፖርት ችግር የመዲናይቱ ሌላ መታወቂያ ሆኗል፡፡ ከሥራ መግቢያ መውጫ ሠዓት ውጪ ረዣዥም የታክሲና አውቶቡስ ሠልፎችን መመልከት እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ የተጠና እና የተደራጀ የትራንስፖርት ሲስተም አለመዘርጋት ነዋሪውን ለእንግልት ዳርጓል፡፡ በቅርቡ ወደ አገልግሎት የገቡ ሜትር ታክሲዎችን ሳይጨምር በአዲስ አበባ ከ12 በላይ ወንበር ያላቸው 11 ሺህ አውቶቡሶችና ከ11 ወንበር በታች ያላቸው 23 ሺህ ታክሲዎች ቢገኙም ቀውሱን መታደግ አልቻሉም፡፡ በሙስና እና የተዝረዘረከ አሠራር አገልግሎት ላይ ከሚገኙት በብዙ እጥፍ አውቶቡሶችን ጋራዥ ውስጥ ያከማቸው አንበሳ አውቶቡስም የስምሪት አድማሱን ቢጨምርም ከከተማው ሕዝብ ዕድገት አንጻር የሚመጣጠን አገልግሎት ማቅረብ አልቻለም፡፡ በሜቴክ የሚገጣጠሙ አውቶቡሶች ዳገት መውጣት ተስኗቸዉ በየጎዳናው መቆማቸው የተለመደ ሆኗል፡፡ ከተማይቱን ለሁለት ከፍሏል የተባለው የቀላል ባቡር አገልግሎት ይሕ ነው የሚባል መፍትሔ አላመጣም፡፡ የሃገር ውስጥ ጋዜጦች እንደገለጹት ከ40 ባቡሮች ውስጥ 23 ያሕሉ ተበላሽተው በመለዋወጫ ዕጦት ከአገልግሎት ውጪ ሆነዋል፡፡
እንግዶቹ አስተዳዳሪዎቻችን
ኢትዮጵያ ከናይጀሪያ በመቀጠል በከተማ ነዋሪ ብዛት ከአሕጉሪቱ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ብትገኝም… መንግሥት ለዓመታት ለከተማ ልማት ፖሊሲ አለመስጠቱ የተወሳሰበ ችግር ማስከተሉን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በከተማይቱ የተሠሩ በርካታ ሕንጻዎችና መንገዶች ከዲዛይን እስከ ግንባታ ችግር የሚታይባቸው፣ ደረጃቸው የወረዱ ስለመሆናቸው አስረጂዎችን መዘርዘር ይቻላል፡፡ መንግሥት የከተማይቱን ችግሮች ዘላቂነት ባለው መልኩ ለመፍታት ከመነሳት ይልቅ በጊዜያዊ መፍትሔ የሕዝብ ተቃውሞን ለማለሳለስ ምርጫው ያደረገም ይመስላል፡፡ የከተማ ልማትን በተመለከተ… የሚሰሩ አነስተኛ ሥራዎችን በማያቋርጡ ፕሮፓጋንዳ ለመሸፋፈን መሞከሩ ተደጋግሞ እንደታየው መንግሥትን ዋጋ ማስከፈሉ አይቀሬ እንደሚሆን የሚጠቁሙ አሉ፡፡ አገዛዙ ግን ለከተማይቱ ችግር መፍትሔ ከማበጀት ይልቅ ስለ ከተማ ልማት አንዳች ዕውቀት የሌላቸውን የሥርዓቱ ካድሬዎች በአዲስ አበባ ላይ ማፈራረቁን መርጧል፡፡ አዲስ አበባ ዛሬም ድረስ የታቀፈቻቸው እነዚህን መሰል ዘርፈ ብዙ ችግሮች… መንግሥት ለመለወጥ ከበቂ በላይ ምክንያቶች እንደነበሩ በምርጫ 97 መልዕክት አስተላልፋ እንደነበር በርካታዎች አይዘነጉትም፡፡