ዋዜማ ራዲዮ-የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና መታሰር በኢትዮጵያና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል አንድ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት አማካሪ ገለፁ።
በመጪዎቹ ቀናት የአሜሪካ ዲፕሎማቶች ለኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ቅሬታና ጥያቄ ለማቅረብ እየተሰናዱ መሆኑን ያመለከቱት አማካሪው አርብ ዕለት በተደረገ ውይይት የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ተከታታይ እርምጃዎች ለመውሰድ ማቀዱን አመልክተዋል።
“የዋሽንግተን አስተዳደር የኢትዮጵያን መንግስት ላለማስቆጣት በብዙ ጉዳዮች ላይ ለዘብተኛ አቋም ነበረው፣ ይህ ግን የሚቀጥል አይመስለኝም” ብለዋል ላለፉት አስራ ስድስት አመታት በአፍሪቃ ጉዳይ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤቱን ያማከሩት ዲፕሎማት።
በአሜሪካ የስልጣን ሽግግር የሚደረግበት ወቅት ቢሆንም አዲሱ አስተዳደር ጉዳዩን በበለጠ ትኩረት ይመለከተዋል ብለው እንደሚገምቱ እኝሁ አማካሪ ለዋዜማ ተናግረዋል።
“የዶ/ር መረራ መታሰር ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ የተከሰተውን ህዝባዊ አመፅ ለመፍታት የኢትዮጵያ መንግስት እየሄደበት ያለው መንገድ ‘አስመሳይነት’ እንጂ ፈፅሞ ችግሩን የሚፈታ እንዳልሆነና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተገን በማድረግ በዜጎች ላይ የሚፈፀመው አፈና ሀገሪቱንም ሆነ በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ወደተሻለ መንገድ የሚያደርሱ አይደሉም” ይላሉ ዲፕሎማቱ።
“ከመጪዎቹ ቀናት ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግስት የማሻሻያ እርምጃ እንዲወስድ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ይደረጋል። ማሻሻያ ለማድረግ ፈቃደኛ ካልሆነ ግን ጠንከር ያለ እርምጃ መውስድ አስፈላጊ መሆኑን ከመግባባት ተደርሷል” ይላሉ አማካሪው።
“የፀጥታ ትብብራችንን እንደመደራደሪያ ማቅረብ የሚያዋጣ አይደለም ……. ለተሻለች ኢትዮጵያ- ህዝብን ማዳመጥና ጥያቄውን የሚመጥን ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል” ሲሉ ያክሉበታል።
“ከወራት በፊት ዶ/ር መረራን እዚህ ዋሽንግተን ዲሲ አግኝቼው ነበር፣ ለኦሮሞ ህዝብ ጥያቄና ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሂደት መወሰድ ባለበት እርምጃ ላይ ምኞቱን አጋርቶኛል። መንግስት ይህን አይነት አስተያየቶችን ለመስማት ካልፈቀደ ሀገሪቱን ወደባሰ ቀውስ ይገፋታል” ብለዋል።
ዶ/ር መረራ በአውሮፓ ህብረት በተዘጋጀ ስብሰባ ላይ የአርበኞች ግንቦት ሰባት መሪ ከዶ/ር ብርሀኑ ነጋ በአንድ አዳራሽ ተገኝተዋል ተብለው ወደሀገር ቤት ሲመለሱ መታሰራቸው ይታወሳል።
የአውሮፓ ህብረት የዶ/ር መረራን መታሰር በማውገዝ መግለጫ ያወጣ ሲሆን የኢትዮጵያን መንግስት በዝግ ዲፕሎማሲ ለመጫን ሙከራ እያደረገ መሆኑ ተሰምቷል።
በርካታ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎችም በኢትዮጵያ የተባባሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት መላ እንዲበጅለት እየወተወቱ ነው።