የመንግስትን መስመር የሚከተሉ በርካታ የሚዲያ ተቋማትን የመደገፍና የማደራጀት ስራ ይከናወናል
ዋዜማ ራዲዮ- ከትጥቅ ትግል በኋላ የዛሬ 22 ዓመት በአዲስ መልክ ሥራ የጀመረው የቀድሞው ሬዲዮ ፋና፣ (የአሁኑ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት) በአገሪቱ ታሪክ የመጀመርያው “የግል” የቴሌቪዥን ጣቢያ ለመሆን ተቃርቧል፡፡ በአንቴናና በሳተላይት በመታገዝ ከአገር ዉስጥ ሙሉ የቴሌቪዥን ፈቃድ አግኝቶ በመላው ዓለም የሚደርስ ሥርጭት ለመጀመር ጫፍ መድረሱም ተሰምቷል፡፡ ይህም ማለት ብዙዎቹ የአማርኛ የሳተላይት ጣቢያዎች እንደሚያደርጉት ፕሮግራማቸውን አገር ዉስጥ ቀድተው ከሁለተኛ አገር ማሰራጨት ሳያስፈልገው እዚህ አገር ቤት ኾኖ የቀጥታ ሥርጭት ማካሄድ ያስችለዋል፡፡
ኾኖም ጣቢያው ለሥርጭት ዝግጅት ማድረግ የጀመረው ብሮድካስት ባለሥልጣን የቴሌቪዥን ፈቃድ መስጠት ከመጀመሩ እጅግ ቀደም ብሎ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህም ሊኾን የቻለው ጣቢያው ፈቃድ ከመጠየቁ አስቀድሞ የቴሌቪዥን ሥርጭት እንዲጀምር ከአንዳንድ የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ከፊል ይሁንታ በማግኘቱ ነበር፡፡
ይህን ይሁንታ በመንተራስም የፋና ብሮድካስቲንግ እህት ኩባንያ የኾነው ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል በአገር ዉስጥ ምንም አይነት የቴሌቪዥን ፍቃድ ሳይጠይቅ በናይልሳት የሙከራ ሥርጭት ለመጀመር የደፈረው፡፡ ድርጅቱ ይህን ያደረገው ለይስሙላ እንኳ ከሁለተኛ አገር ፍቃድ ሳያገኝና ቢሮ ሳይከፍት እዚሁ አገር ዉስጥ ባለው ጽሕፈት ቤቱ አማካኝነት ነበር፡፡ ይህ ክስተት በጥቅሉ የብሮድካስት ባለሥልጣን የቁጥጥርና የፍቃድ ሚና ላይ ጥያቄ እንዲነሳ አድርጎ ቆይቷል፡፡ ብሮድካስት ባለሥልጣን የሳተላይት ስርጭቶችን የመቆጣጠር እንዲሁም ፍቃድ የመስጠት ሥልጣን አለው ወይ? ሥልጣኑስ የት ድረስ ነው የሚለው አሁን ድረስ ብዙዎችን እያነጋገረ ያለ ጉዳይ ነው፡፡
ኢቲቪ አያዋጣም
በርከት ያሉ ድርጅቶች ፍቃድ ከባለሥልጣኑ መውሰድ ሳያስፈልጋቸው ዋና መቀመጫቸውን በሁለተኛ አገር በማድረግ በአገር ዉስጥ ወኪሎቻቸው በመታገዝ ብቻ ስርጭት ማካሄድ ችለዋል፡፡ ይህ ሁኔታ የሕዝብ ዐይንና ጆሮ ላይ ሙሉ ቁጥጥር እንዲያደርግ ታልሞ የተቋቋመውን መሥሪያ ቤት የበይ ተመልካች እንዲሆን ሳያስገድደው አልቀረም፡፡ መንግሥት የልማት አጀንዳዬን እያወኩብኝ ነው የሚላቸውን የሳተላይት ጣቢያዎች ሥርጭታቸውን ለማወክ የሄደበት ርቀት የታሰበውን ዉጤት እንዳላመጣለት መረዳት የጀመረ ይመስላል፡፡
ከሁለተኛ አገር በተገኘ ፈቃድ የሚሰራጩ ጣቢያዎችን ሁሉ በሕገወጥነት በመፈረጅ ማስቆም የሚቻል እንዳልሆነ በመገንዘብ ይመስላል ከአንዳንዶች ጋር የአብረን እንስራ ጥያቄ እስከማቅረብ ደርሷል፡፡ ገዢው ፓርቲ ሕዝብ ዘንድ እንዲደርሱለት አጥብቆ የሚሻቸውን አበይት መልዕክቶች ተወዳጅ በሆኑ ቻናሎች በፕሮግራም ልዉዉጥ መልክ እንዲሰራጩለት መሻቱ አልቀረም፡፡ በምትኩም ድርጅቶቹ ከመንግሥት ጣቢያ የሚፈልጓቸውን ዝግጅቶች እንዲያስተላልፉ፣ ከማስታወቂያ ገቢም በከፊል እንዲቋደሱ ሐሳም ማቅረቡ ተሰምቷል፡፡
ይህ ድርድር እንደቀጠለ ኾኖ በመንግሥት እንደ ሁለተኛው አማራጭ የተያዘው አቅጣጫ ተወዳዳሪ መኾን የሚችሉ አገር በቀል የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ማቋቋም ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አብዛኛው የአገር ቤት ተመልካች በአማርኛ ወደሚሰራጩ የሳተላይት ሥርጭቶች ፊቱን ሙሉ በሙሉ ማዞሩን ተከትሎ ለፋናና መሰል ተቋማት የቴሌቪዥን ፈቃድ የመስጠቱ ሂደት ከታሰበው ጊዜ ቀደም እንዲል ሆኗል ይላሉ የዉስጥ አዋቂዎች፡፡ ቀድሞም መንግስታዊ ያልሆኑ የሳተላይት ስርጭቶችን መገዳደር የሚችሉ አገር በቀል ሚዲያዎች እንዲኖሩ በመንግሥት በኩል ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበረና አሁን በዚህ ደረጃ የሚዲያ ፉክክሩ እያየለ በመምጣቱ ዋልታና ሬዲዮ ፋና በአስቸኳይ ወደ ሥራ እንዲገቡ አስፈልጓል፡፡
በተለይም የወጣቱ ልብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሸፈተ በመምጣቱ በይዘታቸው የወጣቱን ቀልብ ማሸነፍ የሚችሉ፣ ተአማኒነታቸው ያልሟሸሸ፣ የመንግሥትን የልማት ዘመቻና ሰፊ ጥረት ለሕዝብ ማስገንዘብ የሚችሉ ማራኪ ፕሮግራሞችን ወደ ሕዝብ እንዲደርሱ ማድረግ የሚችሉ ጣቢያዎች በተቻለው ፍጥነት ወደ ሥርጭት እንዲገቡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ አቅጣጫ መሰጠቱ ተመልክቷል፡፡ በቅርብ ዓመታትም በርከት ያሉ፣ የመንግሥትን ድምጽ መወከል የሚችሉ፣ ዉግንናቸውን ለገዢው ፓርቲ ያደረጉ “የግል” ሚዲያዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ሊደረግ ይችላል ይላሉ የቅርብ ምንጮች፡፡
በዚህ ረገድ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ለመንግሥት ወዳጅ እንደኾኑ ለሚታሰቡ ባለሐብቶችና ባለሞያዎች ሲሆን የራሳቸውን ሚዲያ እንዲያቋቁሙ ልዩ ትብብር እንዲደረግላቸው ከመግባባት ላይ ተደርሷል ተብሏል፡፡ የመንግሥትን አቋም በመደገፍ የሚታወቁ ጋዜጠኞች በጋራ ተሰባስበው ተጽእኖ መፍጠር የሚችል ጠንካራ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያ እንዲያቋቁመኑና እንዲመሩ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በፊናቸው እነዚህን ሚዲያዎች ማስታወቂያ በመስጠት እንዲደግፉ ምክረ ሐሳብ ቀርቧል፡፡
የኢቢሲ አጋር
ይህ በእንዲህ እያለ መንግሥት የ‹‹ኢቢሲ››ን ቁመና የያዘና በይዘቱ ላቅ ያለ፣ ፈር ያልለቀቁ የሐሳብ ሙግቶችን ማስተናገድ የሚችል፣ ኢቢሲን የሚያግዝ ግዙፍና ተወዳዳሪ አዲስ የመንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢያ ለማቋቋም እቅድ እንዳለው ተሰምቷል፡፡ የሐሳቡ አፍላቂም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደሆኑም ተብራርቷል፡፡ ይህ ግዙፍ ጣቢያ እውን እስኪሆን ድረስ ዋልታ፣ ፋና ብሮድካስቲንግና ድምጸ ወያኔ ፈጥነው ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረጋልም ተብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢቢሲ ምንም እንኳ እስከዛሬ የተጓዘበት ረዥም ጉዞ አበረታች ቢኾንም አሁን ላይ ጣቢያው ሕዝቡን በሚመጥን ቁመና ላይ እንደማይገኝ፣ በዚህም ምክንያት የወጣቱን ልብ ማሸነፍ የሚችል ሌላ ደጋፊ ሚዲያ እንደሚያስፈልገው በተለያዩ መድረኮች ሲያንፀባርቁ ቆይተዋል፡፡ በዚህ የተነሳ አዲስ አማራጭ ሚዲያ እንዲቋቋም ከፍ ያለ ፍላጎት አላቸው፡፡ ምናልባትም አዲሱ ተሿሚ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ቅድሚያ ከሚያስፈጽሟቸው አጀንዳዎች አንዱ ይህንን አማራጭ ሚዲያ ማቋቋም ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ እስከዚያው በቅርቡ ፍቃድ የተሰጣቸው የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ወደ ሥራ ገብተው ክፍተቱን ይሸፍናሉ ተብሏል፡፡ ከነዚህ ሦስት ድርጅቶች ቀዳሚ የሚኾነው ፋና ብሮድካስቲንግ ነው፡፡
ዋልታና ፋና አንድም ሁለትም፣ ነጋዴም ፓርቲም
ፋና ሬዲዮ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ኾኖ በኢህአዴግ አራት አጋር የልማት ድርጅቶች መዋጮ መመስረቱ ራሱን የመጀመርያው የግል የንግድ ሬዲዮ ጣቢያ አድርጎ እንዲቆጥር አስችሎታል፡፡ በቀጣይ እንደእቅዱ ከተጓዘ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ የቴሌቪዥን የሙከራ ሥርጭት ይጀምራል፡፡ ይህም ጣቢያውን በኢትዮጵያ ዉስጥ ፍቃድ አግኝቶ ወደ ሥራ የገባ የመጀመርያው የግል የንግድ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንዲሆን ያስችለዋል፡፡
ጣቢያውን በባለቤትነት የያዙት የትግራዩ ትእምእት፣ የአማራው ጥረት፣ የኦሮሚያው ቱምሳና የደቡቡ ወንዶ ናቸው፡፡ በፕሬዚደንትነት እየመሩት የሚገኙት ደግሞ የሕወሓት አባል የኾኑት አቶ ወልዱ ይመስል ናቸው፡፡ አዲስ ለሚከፈተው ቴሌቪዥን ጣቢያ ምናልባት ፋና ብሮድካስቲንግን በምክትል ሥር አስኪያጅነት ሲያገለግሉ የቆዩትና ዘለግ ላለ ጊዜ በጋዜጠኝነት ያገለገሉት አቶ ብሩክ ከበደ በዳይሬክተርነት ሊመደቡለት እንደሚችሉ ይገመታል፡፡ አቶ ብሩክ የቴሌቪዥን ጣቢያው እውን እንዲሆን ከጥንስሱ ጀምሮ ክትትል ሲያደርጉ የነበሩና ልምድ ለመቅሰም በርከት ወዳሉ አገሮች በቅርብ ጊዜያት ጉዞ እንዳደረጉ፣ አዳዲስ አሰራሮችን ይዘው እንደመጡ ይታወቃል፡፡
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በፓርቲ የልማት ድርጅቶች ባለቤትነት መመዝገቡ የፓርቲ ልሳን ቢያሰኘውም የመጀመርያው የግል የንግድ ሬዲዮ ጣቢያ መሆኑ ጥያቄ ዉስጥ እንዲገባ ፍላጎት የለውም፡፡ ለዚህም ማሳያ ከዓመታት በፊት ሸገር ሬዲዮ ጣቢያ ራሱን የመጀመርያው የግል ሬዲዮ ጣቢያ ብሎ በማስተዋወቁ “ሬዲዮ ፋና” ለብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን ቅሬታውን አሰምቶ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ፋና ብሮድካስቲንግ በአሁኑ ሰዓት ሦስት በአጭር፣ አንድ በመካከለኛና፣ ዘጠኝ በኤፍ ኤም ሞገዶች ሥርጭቱን በመላ አገሪቱ ያስተላልፋል፡፡
ከሁለት ወር በፊት ከሁለት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ የፈጁና ለሥርጭት የሚሆኑ እቃዎች ከዱባይና ከቻይና ተገዝተው ወደ አገር ዉስጥ የገቡ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በጣቢያው 10ኛና 11ኛ ፎቅ ላይ የመሣሪያዎች ተከላ በአንድ የሕንድ ኩባንያ አማካኝነት እየተካሄደ ይገኛል፡፡ የሚገነባው ስቱዲዮም ደረጃውን የጠበቀና እጅግ ዘመናዊ የሚባል እንደሆነ ተነግሮለታል፡፡
ፋና ሬዲዮ አክሲዮን ማኅበር ከሁለት ዓመት በፊት የቴሌቪዥን ሥርጭት የመጀመር ሐሳብ ይዞ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ያደርግ እንደነበረና ያን ጊዜ ፈቃድ እንደሚሰጠው ቃል ተገብቶለት በመዘግየቱ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የአየር ሰዓት በመከራየት ፕሮግራሞችን በጊዜያዊነት ለመጀመር እቅድ ነድፎ ይሠራ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በቅርቡ ለአዳዲስ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጣቢያዎች ፈቃድ ሲታደል የፓርቲ ልሳን እንደሆኑ ለሚታመኑት ዋልታ፣ ድምጸ ወያኔና ፋና በቀዳሚነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ቴሌቪዥን ጣቢያ ለመክፈት በወቅቱ የማመልከቻ ሰነድ የወሰዱ 28 ኩባንያዎች የነበሩ ሲሆን መለኪያውን አሟልተው የቀረቡት ግን አምስት ብቻ ናቸው፡፡ የማጣሪያ ሂደቱ በሁለት ዙር የሚጠናቀቅ ሲሆን የመጀመርያው ዙር ማጣሪያ ፍቃድ ጠያቂዎቹ ከየትኛውም የፖለቲካና የኃይማት ድርጅት የማይወግኑ መኾናቸውን ማረጋገጥን ያካትታል፡፡ ድምጸ ወያነ፣ ፋና ብሮድካስቲንግና ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል በዚህ ረገድ ነጻ መሆናቸው ተረጋግጦ ፈቃድ እንደተሰጣቸው የብሮድካስት ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ልኡል ገብሬ ለፎርቹን ጋዜጣ ተናግረው ነበር፡፡
ብሮድካስት ባለሥልጣን እዚህ ግባ የማይባል ወርሃዊ መጽሔት ለመጀመር የሚያስችል ፍቃድ ለመስጠት እንኳ የባለቤቶቹን የጀርባ ታሪክ ጊዜ ወስዶ እንደሚያጠና ይታወቃል፡፡ በርካታ ግለሰቦችም ፕሬስ ለመጀመር ፍቃድ ማግኘት ተስኗቸው እርግፍ አድርገው መተዋቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ፍቃድ ማግኘት ከዚህ በብዙ እጥፍ እንደሚከፋ መገመት አያዳግትም፡፡
ፋና ብሮድካስቲንግ ትኩስ ዜናዎችን በየሰዓቱ ለሕዝብ በማድረስ፣ በድረገጹ ተከታታይ የዜና ሽፋን በመስጠት፣ የገዢው ፓርቲ ልሳን ከሆኑ ሚዲያዎች ሁሉ የተሻለ አቋም ላይ የሚገኝ ጣቢያ ነው፡፡ የቴሌቪዥን ሥርጭቱም ይህንኑ መልክ ይዞ የሚቀጥልና በዋናነትም የዜና ጣቢያ እንዲሆን ዝግጅት እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡ ጣቢያው በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር ትኩስ ዜናዎችን በቀጥታ በየሰዓቱ ወደ ሕዝብ ለማድረስ እንዲያስችለው ራሱን በአዲስ የሰው ኃይል በማደራጀት እየሠራ ነው፡፡ በቅርቡም ከአንድ መቶ ሐምሳ በላይ የሚሆኑ ሪፖርተሮችንና የካሜራ ባለሞያዎችን መልምሎ ወደ ሥልጠና አስገብቷል፡፡
የምስል ክምችት ክፍሉን ለማጠናከርም ከእህት ኩባንያው ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጋር በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል፡፡ ዋልታ በርካታ የዘጋቢ ፊልም ቅጂዎች ያሉትና በምስል ክምችት ጥራቱ የሚመረጥ የሚዲያ ተቋም ነው፡፡
ካፒታሉ መቶ ሚሊየን ብር የደረሰው ፋና ብሮድካስቲንግ አምስት መቶ የሚጠጉ ሠራተኞች ሲኖሩት ከነዚህ ዉስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ጋዜጠኞች ናቸው፡፡
ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደ ፋና ሁሉ በአራት የኢህአዴግ የልማት ድርጅቶች መዋጮ የተመሠረተ ሲሆን ድርጅቶቹ እያንዳንዳቸው 29.9 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ አላቸው፡፡
ዋልታና ፋና ተዳቅለው የመሠረቱት “ዋፋ ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን አክሲዮን ማኅበር” ሦስተኛው እህት ተቋም ሲሆን በንግድና ትዕይንት መሰናዶ ላይ የሚሠራ፣ ዓለም አቀፍ የንግድ ባዛሮችን በመንግሥት አቅጣጫ መሠረት የሚያዘጋጅ አዲስ ድርጅት ነው፡፡ ፋናና ዋልታ በዋፋ ፕሮሞሽንና ማርኬቴንግ ላይ የ49 በመቶና የ51 በመቶ ድርሻ አላቸው፡፡ የዋፋ ሥራ አስኪያጅና የዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ሥራ አስኪያጅ ባልና ሚስት ናቸው፡፡