በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚያደርጋቸው መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቹ የሚታወቀው ማኅበረ ቅዱሳን ሰሞኑን አዲስ የኢንሳይክሎፔዲያ ፕሮጀክት መጀመሩን አስተዋውቋል። ፕሮጀክቱ በዓይነቱ የመጀመሪያ በመኾኑና ምንም እንኳን ጅማሬው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን የሚመለከት ኢንሳይክሎፔዲያ የማጠናቀር ስራ ቢኾንም ቤተክርስቲያኒቱ በኢትዮጵያ ባላት ትልቅ የታሪክ፥ የባሕልና፥ የሥነ ጥበብ አስተዋጽኦ ምክንያት የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ዜና ኾኗል።
መዝገቡ ሀይሉ በድምፅ ያሰናዳውን እዚህ ያድምጡ አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ
ኢትዮጵያ እንደ ማንኛውም የኢንሳይክሎፔዲያ መጠቁም አንድ ርዕስ ኾና ጥቂት ገጾች በሚሸፍን ትንታኔ ከመገለጽ አልፋ በስሟ የተመሰረተ እና ዋነኛውን ጉዳዩን በኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ ያደረገ የኢንሳይክሎፔዲያ መድብል የኖራት በቅርቡ ነው። በእርግጥ ይህ እ ኤ አ በ2014 የተጠናቀቀው ኢንሳይክሎፔዲያ ኤትዮፒካ ከረጅም ዘመን የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር በኋላ በመምጣቱ የዘገየ ቢመስልም ኢትዮጵያ እንዲህ ባለ የእውቀት መዝገብ በለቤትነት ተራ መሰለፏ ከዓለም ጥቂት እድለኛ አገራት አንዷ እንድትኾን አድርጓታል። ይህን ታሪካዊ ሊባል የሚችል ስራ ያበረከተልን የጀርመኑ ሀምቡርግ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናት ማእከል ነው።
ከ 50 አገራት የተውጣጡ ከ 500 በላይ የኢትዮጵያ ጥናት ምሑራን አስተዋጽዖ ያደረጉበት ኢንሳይክሎፔዲያ ኤትዮፒካ ሐሳቡ ከመነጨበት እ ኤ አ ከ 1994 ጀምሮ 20 ዓመት የተደከመበት ትልቅ ስራ ነው። በ 5 ጥራዝ የተጠናቀቀው ይህ ኢንሳይክሎፔዲያ በኢትዮጵያ የታሪክ፥ የባሕልና፥ የስነጥበብ ጉዳዮች ላይ የቀረበ የተሟላ የጥናት ውጤት መድበል ነው። ኢንሳይክሎፔዲያውን ለመግዛት በየጥራዙ 78 ዩሮ (ወደ 2000 ሺህ ብር ገደማ በድምሩ ወደ 9 ሺህ 600 ብር ) በመጠየቁ ምክንያት በየግለሰቡ እጅ እንደ ልብ የሚገኝ ማጣቀሻ ሳይኾን በቤተመጽሐፍት የተወሰነ ሊያደርገው ይችላል። ይዘቱን ለብዙዎች በቀላሉ ለማድረስም እንደ ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ ሁሉ በድረገጽ ቀርቦ በቀላሉ ሊገኝ የሚችል ማጣቀሻ ኾኖ እንደሚቀርብም በጉጉት ይጠበቃል።
ይህን በኢንሳይክሎፔዲያ ኤትዮፒካ የተጀመረውን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ኢንሳይክሎፔዲያ የማዘጋጀት ጅምር ማኅበረ ቅዱሳን ወደ ሌላ አዲስ ደረጃ ሊያሸጋግረው መነሳቱን አብሥሯል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ብቻ የሚመለከት አዲስ የኢንሳይክሎፔዲያ ጅምር አስተዋውቋል። ያውም በአማርኛ ቋንቋ። ይህ አዲስ ጅማሬ በብዙ መልኩ ለብዙዎች የሚያስደስት ዜና ነው። ለኦርቶዶክስ ክርስትና ተከታይ ምእመናንና ካህናት የቤተክርስቲያናቸውን ትውፊት፥ የእምነት መሠረትና አስተምህሮ ጠቅልሎ የያዘ የመረጃ ምንጭ በዚህ ኢንሳይክሎፔዲያ አማካኝነት መቅረቡ ትልቅ ድጋፍ እንደሚኾንላቸው ከወዲሁ መገመት ይቻላል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በኢትዮጵያ የፖለቲካ፥ የታሪክና የባሕል ሒደት ላይ የነበራት ጉልህ አስተዋጽዖ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ምእመናን ያልኾኑ ሌሎችም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከቤተክርስቲያኒቱ ጋር የተቆራኘውንና ለኢትዮጵያ ጥናት ወሳኝ የኾኑ ጉዳዮች የሚመረምሩበት ወሳኝ የመረጃ ማጣቀሻ ኾኖ የሚያገለግል የመረጃ ምንጭ ሊገኝ መቻሉ በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ አይደለም። በዚህም ላይ እስከዛሬ ባልተለመደመልኩ የኢንሳይክሎፔዲያው ይዘት ሙሉ በሙሉ በአማርኛ ቋንቋ የሚዘጋጅና በኢትዮጵያውያን ምሑራን ብቻ የሚሰራ መኾኑም ታሪካዊ ተድርጎ ሊቆጠር የሚገባው ሙከራ ኾኖም ይታያል።
በኢንሳይክሎፔዲያ የሚቀርቡ መረጃዎች ብዙውን ጊዜ ብቃት ባለቸው የየዘርፉ ምሑራን የሚዘጋጁ የጥናት ውጤቶች ከመኾናቸው የተነሳም ስለየሚያነሱት ጉዳይ የሚሰጡት መረጃ የሐሳብና የጥራት ልዕልና ያላቸው ኾነው መቅረብ ይጠበቅባቸዋል። ምንም እንኳን የዚህን ኢንሳይክሎፔዲያ ስራ ያስጀመረውና በገንዝብም የሚደግፈው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያለ መንፈሳዊ ማኅበር ቢኾንም በኢንሳይክሎፔዲያው የሚካተቱት መረጃዎች ሙያዊ ብቃታቸውን የጠበቁና በየዘርፉ ምሑራን የሚሰሩ የጥናት ጽሑፎች እንደሚኾኑ እንደሚጠበቅም በዚሁ የኢንሳይክሎፔዲያ ዝግጅት ውስጥ አስተዋጽዖ የሚየደርጉት ዶክተር መርሻ አለኸኝ ለዋዜማ ገልጸዋል። ዶክተር መርሻ ጨምረው እንደገለጹት ማኅበረ ቅዱሳን የሐሳቡን መነሻ ካመነጨና አስፈላጊ ነገሮችን ካሟላ በኋላ የኢንሳይክሎፔዲያው ዝግጅት ክፍል ከማኅበሩ ቁጥጥር ነፃ በመኾን ሙሉ በሙሉ ራሱን ችሎ የሚሰራ እንዲኾን ተደርጓል።
በእርግጥም በኢንሳይክሎፔዲያው ዝግጅት ውስጥ እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቦላቸው ሙሉ ድጋፋቸውን እየሰጡ ያሉትን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሑራን በተለይም ፕሮፌሰር ባዬ ይማምንና ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለን ማካተቱ ማኅበሩ ይህን የሚያረጋግጥ ትልቅ ርምጃ እንደወሰደ ጠቋሚ ነው። እነዚህ ሁለት ምሑራን በኢንሳይክሎፔዲያ ኢትዮፒካ ዝግጅት ውስጥና በኢትዮጵያ ጥናት ዘርፍ ያላቸው ልምድ ለዚህ አዲስ የኢንሳይክሎፔዲያ ዝግጅት ትልቅ እሴት እንደሚኾን ይጠበቃል።
የኢንሳይክሎፔዲያው ዝግጅት ገና ጅማሬ ላይ ያለ ከመኾኑ የተነሳ አጠቃላይ ይዘቱ ምን ሊኾን እንደሚችል ከወዲሁ መገመት ቢያስቸግርም ከሌሎች ተመሳሳይ የሐይማኖት ተቋማት ኢንሳይክሎፔዲያዎች ጋር የሚያመሳስለው ብዙ ነገር እንደሚኖር መገመትም ይቻላል። ልዩነቱ ቤተክርስቲያኒቱ እስከ ዛሬ በሌሎች ከተሰሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን የሚመለከቱ ጥናቶች በተለየ ስለራሷ እምነትና አስተምህሮ የተለየ መረጃ ልትሰጥ የምትችልበት ሊኾን መቻሉ ላይ ነው። እግረ መንገዱንም ቤተክርስቲያኒቱ ስለነበራት የታሪክ የባሕልና የጥበብ አስተዋጽዖ በቤተክርስቲያኒቱ እይታ እንዴት እንደሚገለጽ ማሳየቱም የሚጠበቅ ጉዳይ ነው። ሌሎች እምነቶችንና ባሕሎችን በተመለከተም የቤተክርስቲያኒቱ እይታ መንጽባረቁም ሌላው የይዘቱ አካል ሊኾን ይችላል።
የኢንሳይክሎፔዲያው ጅማሬ ይህን ያህል በጉጉት የመጥበቁን ያህል ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄዎችም አሉ። የመጀመሪያው ጥያቄ ከኢንሳይክሎፔዲያ ኢትዮፒካ ጋር ተያይዞ ሊቀርብ የሚችል ጥያቄ ነው። ቤተክርስቲያኒቱ በነበራት ግዙፍ ሊባል የሚችል አስተዋጽዖ ምክንያት አብዛኛዎቹ የኢንሳይክሎፔዲያ ኤትዮፒካ ጽሑፎችም ይኹኑ በኢትዮጵያ ጥናት ተቋም የተሰሩ የጥናት ስራዎች ከቤተክርስቲያኒቱ ጋር መገናኘታቸው በግልጽ የሚታይ ጉዳይ ነው። ጥያቄው ታዲያ አዲሱ የኦርቶዶክስ ኢንሳይክሎፔዲያ ከነኚህ ቀደምት ጽሑፎች ምን የተለየ ይዘት ይኖረዋል? የሚል ነው።
ሌላው ጥያቄ ሊኾን የሚችለው ይህ ኢንሳይክሎፔዲያ ከኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አንጻር የሚጻፍ ከመኾኑ የተነሳ የሌሎችን የእምነት ተቋማት በተመለከተ በኢንሳይክሎፔዲያው ሊካተት የሚችለው ይዘት የሚቀርብበትን መንገድ የተመለከተ ነው። የካቶሊክ ኢንሳይክሎፔዲያን እንደ ምሳሌ ብንወስድ፥ የካቶሊክ ኢንሳይክሎፔዲያ በተጻፈበት ዘመን የተካተቱ አንዳንድ ሐሳቦችና አሁን ባለው ዘመናዊ አመለካከትና የእውቀት ደረጃ ተቀባይነት እንደሌላቸው ታምኖ ጥያቄ ውስጥ ወድቀዋል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚኾነው የኦርቶዶክስ አብያተክርስቲያናትን በተመለከተ ኢንሳይክሎፔዲያው የሚሰጣቸው ማብራሪያዎች ናቸው። ኢንሳይክሎፔዲያው አብዛኞቹን ከካቶሊክ እምነት ጋር የማይስማሙ የኦርቶዶክስ ዶክትሪኖች ሲያጥላላና ትክክል እንዳልኽኑ ወይም እርስ በእርሳቸው እንደሚቃረኑ አድርጎ አቅርቦት ነበር።
ይህን የመሰለው አቀራረቡ ታዲያ ምሑራዊነት የጎደለውና የሌሎች ሐይማኖቶችን ክብር የሚነካ በመኾኑ ተነቅፎበታል። በአሁኑም ዘመን ለጥሩ ማጣቀሻነት የማይመረጥና ዘመን ያለፈበት ኾኖ እንዲወሰድ አድርጎታል። ይህ አዲሱ የኦርቶዶክስ ኢንሳይክሎፔዲያ ዝግጅት ይህን ከመሰለው ልምድ በመነሳት አወዛጋቢ የኾኑ የባሕል የታሪክና ሌሎች እምነቶችን በተመለከተ ለሚያካትተው ይዘት የሚያደርገው ጥንቃቄ ከጅምሩ ሊነሳ የሚችል ጉዳይ ነው።
ገና በጅምር ላይ ያለው የኢንሳይክሎፔዲያው ዝግጅት እነኝህንና ሌሎች ጥያቄዎችን በሒደት የሚፈታቸው ጉዳዮቹ ይኾናሉ። በሰባት ጥራዝ እንደሚጠናቀቅ ከወዲሁ የተገመተው ይህ ኢንሳይክሎፔዲያ በሺሆች ለሚቆጠሩት የኢንሳይክሎፔዲያው ጽሑፎች አስተዋጽዖ የሚያደርጉ ምሑራን እጥረትና በሚሊዮን ለሚገመተው የዝግጅቱ ወጪ የሚኾነው ገንዘብ ጉዳይም ቀላል የሚባል ፈተና ላይኾንም ይችላል። ይህም ሁሉ ኾኖ ኢንሳይክሎፔዲያው ችግሮቹን ተቋቁሞና ጥራቱን ጠብቆ ለፍጻሜ እንደሚደርስ የብዙዎች ተስፋ ነው።