EU Refugeeከመካከለኛው ምስራቅና ከአፍሪካ ያለገደብ የሚፈሰው የስደተኛ ጎርፍ ያሳሰባቸው የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ችግሩን ለመፍታት ተገቢ ያልኾኑ ርምጃዎችንም ጭምር እየወሰዱ እንደኾነ እየተገለጸ ነው። ዓለም ካወገዛቸው አምባገነን መሪዎችና ጨቋኝ መንግስታት ጋር ምስጢራዊ ስምምነቶች መደረጋቸውም እየተጋለጠ ነው።

መዝገቡ ሀይሉ በጉዳዩ ዙሪያ ያዘጋጀውን የድምፅ ዘገባ እዚህ ያድምጡ አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ

በአብዛኛው ሶርያን ከመሰሉ የጦርነት አውድማ ከኾኑና እስካሁንም ያለፈባቸው የጦርነት መገረን ካልሻረላቸው አፍጋኒስታንና ኢራቅ፥ እንዲሁም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግር ከሚያደቃቸው የአፍሪካ አገራት የሚተመው የስደተኛ ሰራዊት ዳፋው አውሮፓም እየደረሰ ነው።

በሚሊዮን የሚቆጠረው የስደተኛው ብዛት ከሚጠበቀው በእጅጉ የበዛ ከመኾኑም በላይ በስደተኞቹ መካከል ሰርገው የሚገቡ አሸባሪዎች ይኖሩ ይኾናል የሚለው ስጋት፥ ቀድሞ በሰብአዊነታቸው የዓለም ምሳሌ ተደርገው የሚቆጠሩትን የስካንዲኔቪያ አገራት ሁሉ እንዲጨክኑ አድርጓቸዋል። ለጉዳዩ መፍትሔ ለማግኘት ከማሰብም ይመስላል ድንገተኛ ገደቦችን እንዲደነግጉ አስገድዷቸዋል። በሚወስዷቸው አንዳንድ ርምጃዎችም ምክንያት በሰበአዊ መብት ተሟጋቾች ትችትም እየቀረበባቸው ይገኛል።

የስደተኛው ፍሰት በብዙ የአውሮፓ አገሮች ውስጥ ዋነኛ የፖለቲካ አጀንዳ ከመኾን አልፎ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት በስምምነት አፍርሰውት የነበረውን ድምበራቸውን እስከመዝጋት ደርሰዋል። ችግሩ በዚህ ከቀጠለም የሸንገን ስምምነት በመባል የሚታወቀውንና አብዛኞቹን የአውሮፓ አገራት የሚያስተሳስረውን የቪዛ ስምምነት ከነጭራሹ እንዳያጠፋውም ተሰግቷል። ከዚህም በላይ ይኸው የስደተኞች ጉዳይ በአውሮፓ ፖለቲካ ውስጥ ጊዜ ያለፈባቸውና እየከሰሙ ይመስሉ ለነበሩት የቀኝ አክራሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ማንሰራራት ምክንያት ኾኗል። በዘረኝነታቸውና እስልምና ላይ ባላቸው ጥላቻ (Islamophobia) የሚታወቁት እነኚህ ፓርቲዎች በአንዳንድ የአውሮፓ አገራት ውስጥ ስልጣን እስከመያዝም ደርሰዋል። ስልጣን ባልያዙባቸውም አገራትም ውስጥ ቢኾን ተደማጭነታቸውና ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መጥቷል።

ይህን ችግር ለመፍታት ሲባዝኑ የከረሙት የአውሮፓ ኅብረት መሪዎችም በቅርቡ አስገራሚ የኾነ ስብሰባ አድርገው እንደነበር ተሰምቷል። የስብሰባው ይዘት አሳፋሪ ስለኾነባቸውም ይመስላል በብርቱ ምስጢርነት እንዲጠበቅና ጉዳዩን የመገናኛ ብዙኃንም ሕዝብም እንዳይሰማው በሚል ማሳሰቢያ ሲማማሉም እንደነበር ተገልጿል። ያም ኾኖ ይህን በምስጢር እንዲያዝ ማሳሰቢያ የተደረገበትን ሰነድ በጀርመኑ ድረ ገጽ ሽፔግል እጅ በመግባቱ ለዓለም ሁሉ ይፋ ኾኗል።

ሰነዱን ያጋለጠው የሽፔግል ዘገባ እንደሚጠቁመው የኅብረቱ አባል አገራት ተወካዮች ድሮ ይኮንኗቸው ከነበሩ የአፍሪካ ቀንድ አምባገነን መንግስታት ጋር ድብቅ ስምምነት አድርገዋል። ዘገባው እንደገለጸው ከአፍሪካ ቀንድ አገራትም መካከል መሪዋ በተገኙበት እንዲያዙ ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (ICC) ትእዛዝ ያስተላለፈባቸው ኦማር ሐሰን አልበሽር የሚመሯት ሱዳን ዋነኛዋ የስምምነቱ አካል ነበረች። የአውሮፓ ኅብረት ሱዳንን ዋነኛዋ ትኩረቱ ያደረገበት ምክንያት ባላት ስነምድራዊ አቀማመጥ ለአብዛኞቹ የአፍሪካ ስደተኞች መተላለፊያ ስለኾነች ነው።

ሱዳን ከኤርትራ፥ ከሶማልያ፥ ከኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ፥ ከመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ እና ከኢትዮጵያ በሊብያ በረሃዎች አቋርጦ አውሮፓ ለመግባት ለሚጓዘው የተስፈኛ ጎርፍ ዋነኛ መተላለፊያ ነች። ይህን የስደተኛ ጎርፍ ከአፍሪካ ሳይወጣ ባለበት ለማቆየት የተመኙት የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራትም ከሱዳን ጋር የድብቅ ስምምነቱን ለማድረግ ወስነዋል። በዳርፉር እና በሌሎች የውስጥ ፖለቲካ ችግሮች ምክንያት የጠለሸውን ስሙን ለማጽዳት ትልቅ ምኞት እንዳለው ለሚነገርለት የአልበሽር መንግስት ይህ ስምምነት ከሚያስገኝለት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ በተጨማሪ አብሮት የሚመጣው የፖለቲካ ትሩፋት ከድርድሩ የሚያገኘው ጥቅም እንደሚኾንም ይፋ የኾነው ሰነድ ይጠቁማል።

ድብቁ ሰነድ ከያዛቸው አስገራሚ ነገሮች አንዱ የዚህን ድርድር ውጤት አሉታዊ ገጽታ የገመገመበት መንገድ ነው። በሰነዱ እንደተገለጸው የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት የሱዳን መንግስት በዚህ ርዳታ በሚያገኘው የቁጥጥርና የምርመራ ዘመናዊ መሳሪያ ስልጣኑን ለማጠናከርና ተቃዋሚዎቹን ለማዳከም ይጠቀምበት ይኾናል የሚ ስጋት አላቸው። ይህም በተለያዩ የሰበአዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ ተቃዋሚዎቹንና ነጻውን ሚዲያ በመጨቆን ለሚወቀሰው የሱዳን መንግስት ተጨማሪ ዘመናዊ የጭቆና መሳሪያ እንደሚሰጠው ይገምታል የኅብረቱ አባል አገራት ግምገማ።

ያም ኾኖ ይህ ስጋት የኅብረቱን አባል አገራት ከሱዳን ጋር የሚያደርጉትን ድብቅ ስምምነት እንዲያቋርጡ አላደረጋቸውም። ሕልውናቸውን እየተፈታተነው የመጣውን ይህን የስደተኞች ጉዳይ በማንኛውም መንገድ ለመፍታት የቆረጡ የሚመስሉት የኅብረቱ አባል አገራት የስምምነቱ ይዘት ሊያስከትልባቸው የሚችለውን ፖለቲካዊ ጥያቄ ለመገደብ ያደረጉት ጥረት ይህን ስምምነት ከሕዝብ ና ከመገናኛ ብዙኃን ለመደበቅ መወሰናቸው ብቻ ነው። ይህን ጉዳይ በተመለከተም ግልጽነት አደማያስፈልጋቸው መወሰናቸውንም ሽፔግል ያወጣው መረጃ ይጠቁማል።

ይህ ስምምነት ተፈጻሚነት ካገኘ የአውሮፓ ኅብረት በሱዳን ሁለት የስደተኞች ማጎሪያ ካምፖች ለመገንባትና የሱዳንን ፖሊስ በልዩልዩ የምርመራና የቁጥጥር ተግባር ለማጠናከር የሚረዱ ስልጠናዎችን ይሰጣል። ለዚህም ተግባር የሚረዳ ዘመናዊ የቁጥጥር (surveillance) ቴክኖሎጂ ያስታጥቃል። ይህ ስምምነት በሱዳን ላይ ትኩረቱን ያድርግ እንጂ ኢትዮጵያ የምትገኝበትን የአፍሪካን ቀንድ ጨምሮ ለ ስምንት የአፍሪካ አገራት የገንዘብ ድጋፉን መስጠት ይጀምራል። የጀርመኑ የተራድዖ ድርጅት GIZ የዚህን ስራ ኃላፊነት ወስዶ ተግባራዊ እንደሚያደርገውም ተገልጿል።

 

የኅብረቱ አባል አገራት ይህን ጉዳይ አሁን ምስጢራዊ ሊያደርጉት ቢነሱም እቅዱ ቀደም ብሎ እንደተጀመረ ሲዘገብ ቆይቷል። ባለፈው የፈረንጆች ዓመት መገባደጃ ላይ በማልታ ተደርጎ በነበረው የሁለት ቀን ስብሰባ ላይ ከአፍሪካ መሪዎች ጋር በመቀመጥ አውሮፓውያኑ አገራት የሚያባርሯቸውን የማይፈለጉ ስደተኞች እንዲቀበሏቸው ጥያቄ አቅርበው ነበር። በድርድሩም ላይ የአውሮፓ ኅብረት አገራት ለአፍሪካውያኑ መሪዎች የ1.8 ቢሊዮን ዩሮ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ቃል ገብተው ነበር። ይኸው የገንዘብ መጠንም በጥቂት ዓመታት ውስጥ በእጥፍ አድጎ 3.6 ቢሊዮን ዩሮ እንደሚደርስም ተጨማሪ ቃል ገብተዋል።

በድርድሩ መጀመሪያ ላይ የገንዘቡ መጠን አንሷል ሲሉ የነበሩት የአፍሪካ መሪዎችም በመጨረሻ መግባባት ላይ ደርሰው ይህንኑ ዕቅድ ተፈጻሚ ለማድረግ ተስማምተው ስብሰባቸውን አጠናቀዋል። ይህ ስምምነት ብዙ ዜጎቿን በስደት እያጣች ያለችውን ኤርትራን ከየትኛውም የአፍሪካ አገር በበለጠ የገንዘቡ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋት ሲገለጽም ቆይቷል።

የአውሮፓ ኅብረት ይህንኑ የመሰለ ስምምነት ከቱርክ መንግስትም ጋር አድርጎ ነበር። ቱርክ ከሶርያና ከሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ አገራት እየተመመ የሚመጣውን ስደተኛ በመያዝ ለምታደርገው ትብብር የ 3 ቢሊዮን ዩሮ ስጦታ የቀረበላት ሲኾን ከገንዘብ ድጋፉ በተጨማሪ የአውሮፓ ኅብረት አባል ለመኾን ያቀረበችው ማመልከቻ በፍጥነት እንዲታይላት የሚያደርግና ዜጎቿ ያለቪዛ በአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት እንዲዘዋወሩ የሚያስችል ፈቃድም እንድታገኝ የኅብረቱ ተወካዮች ተስማምተው ነበር። ይህ ስምምነት ግን ከትችት አላመለጠም። የሰበአዊ መብት ድርጅቶች የአውሮፓ አገራት ስደተኞችን ላለመቀበል የሚያደርጉትን ይህን ጥረት ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን የጣሰና ሕገ ወጥ ነው ሲሉ የኅብረቱን አባል አገራት ወቅሰዋል።

ይህ በንዲህ እንዳለ የአውሮፓ ኅብረት ከቱርክ ጋር ባደረገው ስምምነት ምክንያት መግቢያ ያጡ ስደተኞችና መረጋጋት ከራቃት ከሊብያ ተጨማሪ ስደተኞች እንዳይመጡባት የሰጋችው ጣልያን ኅብቱ ተጨማሪ ገንዘብ በመመደብ የአፍሪካ አገራት ገድበው እንዲይዙ ለማድረግ የሚረዳ ነው ያለችውን አዲስ ሐሳብ አቅርባለች። ይኹንና የኅብረቱ ዋነኛ የገንዘብ ምንጭ የኾነችውን ጀርመንን ጨምሮ ይህን አዲሱን የጣሊያን ሐሳብ አልተቀበሉትም። የሐሳቡ ተቃዋሚዎች እንደሚሉት ከዚህ በፊት በማልታው ስምምነት የተወሰነው የ 1.8ቢሊዮን ዩሮ ፈንድ ለዚሁ ጉዳይ የተመደበ በመኾኑ ተጨማሪ ገንዘብ ማውጣት አስፈላጊ ኾኖ አልታያቸውም።

ባለቸው የሰበአዊ መብት አቋም በመጽናት የስደቱ ምክንያት የኾነውን የኢኮኖሚ ፥ የፖለቲካና የጦርነት ችግር ይፈቱ ይኾናል ተብለው የሚጠበቁት የአውሮፓ ኅብረ አባል አገራት ጉዳዩን በገንዘብ ኃይል ለመፍታት የሚያደርጉት ጥረት ከዚያም አልፎ የችግሩ ምክንያት ከኾኑት አምባገነን መንግስታት ጋር ይህን የመሰለ ስምምነት ማድረጋቸው ያልተጠበቀ ዜና ኾኖ ሰንብቷል። ድምበር የለሹ የሐኪሞች ድርጅት (Doctors with out Boarders)  ”ስደተኞች ገንዘባችሁን ብቻ ሳይኾን እናንተንም ይፈልጋሉ” ሲል ወቀሳውንም የሰነዘረው በዚህ ምክንያት ነው። የችግሩ ግዙፍነት ግን የአውሮፓውያኑን ዓለም አቀፋዊ ፖሊሲ መርህ ጽናት የት ድረስ ሊዘልቅ እንደሚችል የሚፈታተነው ኾኖ ይታያል።