የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የጻፉት “የኦሮሞ ህዝብ ታሪክ” የተሰኘው መጽሐፍ ሰኞ ሚያዝያ 17 ገበያ ላይ እንደሚውል ይጠበቃል፡፡ መጽሐፉ ዶክተር ነጋሶ ለዶክትሬት ማሟያ ባደረጉት ምርምር ላይ የተመሰረተ ሲሆን በምዕራብ ወለጋ በሚገኙት የሰዮ ኦሮሞዎች ዘንድ ከ1730-1886 በተከሰቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ለውጦች ዙሪያ ያጠነጥናል፡፡
ዶክተር ነጋሶ 408 ገጽ ባለው መጽሀፋቸው ከዚህ ቀደም በታሪክ ምሁራን አማካኝነት “የኦሮሞ ህዝብ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ፈልሶ ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ” ሲጻፍ ከነበረው በተቃራኒው ከሀገሪቱ “ነባር ህዝቦች አንዱ እንደነበር” በማስረጃ አስደግፈው ያስነብባሉ፡፡
በመጽሐፉ ውስጥ ካሉ ዘጠኝ ምዕራፎች ውስጥ ሶስቱ ስለ ኦሮሞ ህዝብ አመጣጥ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ስለ ነበረው መስፋፋት የሚተነትኑ ናቸው፡፡ በቀደምት የታሪክ ጸሀፍት ሲገለጽ የነበረውን “ከደቡብ ወደ ሰሜን” የተደረገ የኦሮሞ ፍልሰትንም የሚገዳደሩ ናቸው፡፡ ዶክተር ነጋሶ የኦሮሞ ሕዝብ ጎሳዎችን የትውልድ ሀረግ ቆጠራዎች እና ማህበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጦችን በማጣቀስ የኦሮሞ ሕዝብ ፍሰት ቀደም ሲል ሲነገር ከነበረው በተቃራኒ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡
“ከዚህ በፊት ሲጻፍ የነበረው የኦሮሞ ህዝብ ከባሌ ወደ ሰሜን እንደተስፋፋ ነው፡፡ የእኔ ምርምር የሚያሳየው ግን ከሰሜን ወደ ደቡብ እንደተስፋፋ ነው” ይላሉ ዶክተር ነጋሶ ስለ መጽሐፋቸው ይዘት ለዋዜማ ሲያስረዱ፡፡ “ከዚህ በፊት ሲባል የነበረው የኦሮሞ ህዝብ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ከማዳጋስካር ወይም ከቦረና መፍለሱን ነው፡፡ እርሱ ትክክል አይደለም፡፡ በእኔ ጥናት መሰረት የኦሮሞ ህዝቦች ከ16ኛው ክፍለ ዘመን በፊት በመሀል ኢትዮጵያ ይኖሩ ነበር፡፡”
ከአመጣጡ እና መስፋፋቱ ባሻገር የኦሮሞ ሕዝብ ከአጎራባች ሕዝቦች ጋር ስለነበረው መስተጋብር እንዲሁም የውስጥ አስተዳደር መርህዎች በመጽሐፉ ሰፋ ተደርጎ ተዳስሷል፡፡ ከ18ኛው ክፍለ ዘመን እስከ አፄ ምኒልክ ዘመን ድረስ የተካሄዱ ጦርነቶችና ውጤቶቻቸውም ቀርበውበታል፡፡
የምርምር ስራው ሁለት ተጨማሪ ነባር አስተሳሰቦችንም ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ነው፡፡ የመጀመሪያው “የገዳ ስርዓት ዲሞክራቲክ ነው” የሚለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ “እንደ አባ ጅፋር እና ጆቴ ያሉ የኦሮሞ ባላባቶች ንጉሳዊ ስርዓትን ከሌሎች ቦታዎች ቀድተው የጀመሩት ነው” የሚለው ነው፡፡ እነዚህን በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው አመለካከቶች “የሚገዳደሩ” እውነታዎችን በመጽሐፋቸው ማካተታቸውን ዶክተር ነጋሶ ያስረዳሉ፡፡
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ከምዕራፍ አምስት እስከ ዘጠኝ ያለውን የመጽሐፋቸውን ክፍል በምዕራብ ወለጋ ለሚገኘው የሰዮ ኦሮሞ ታሪክ አውለዋል፡፡ የአካባቢው ተወላጅ መሆናቸው እና አካባቢውን በሚገባ ማወቃቸው በሰዮ ኦሮሞ ላይ እንዲያተኩሩ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ፡፡ እንደ ዶክትሬት ማሟያቸው ሁሉ የሁለተኛ ዲግሪያቸውንም የሰሩት በሰዮ ማህበረሰብ ላይ ነበር፡፡
በጊምቢ እና ደምቢ ዶሎ መካከል በሚገኝ አይራ አካባቢ ከ1963 እስከ 1966 ዓ.ም በአስተማሪነት ተመድበው ይሰሩ በነበረበት ወቅት አብዛኛውን ጥናት ማከናወናቸውን ዶክተር ነጋሶ ይናገራሉ፡፡ የሳምንቱን መጨረሻ እንደዚሁም የዕረፍት ቀናቸውን በመጠቀም ታሪክ አዋቂ ሽማግሌዎች ያነጋግሩ፣ መረጃዎችንም ይሰበስቡ እንደነበር ወደ ኋላ መለስ ብለው ያስታውሳሉ፡፡
እንዲህ ለዓመታት የደከሙበት የምርምር ስራ በጀርመን ፍራንክፈርት ዮሓን ጎተ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ማዕረግ አጎናጽፏቸዋል፡፡ የፕሬዝዳንትነት ስልጣናቸው ማብቂያ አካባቢ ደግሞ በእንግሊዘኛ ቋንቋ በመጽሐፍ መልክ ታትሞ በሀገር ውስጥ ለንባብ በቅቶላቸው ነበር፡፡
“መጽሐፉ ገበያ ላይ የዋለው እኔ ከኢህአዴግ ከመልቀቄ ሁለት ሳምንት በፊት ነበር” ይላሉ ዶክተር ነጋሶ በሰኔ 1993 ዓ.ም የነበረውን ሁኔታ ሲተርኩ፡፡ “ዋልታ እና የኦህዴዱ ‘ኦሮሚያ’ ጋዜጣ ማስታወቂያ ማስነገር እና ስርጭቱንም ጀምረው ነበር፡፡ እንደለቀቅኩ ማስታወቂያው ቆመ፡፡ ሽያጩንም ምን እንዳደረሱት አላውቅም፡፡”
የምርምር ስራቸው “ለሰፊው ህዝብ” እንዲደርስ በነበራቸው ፍላጎት በአማርኛ እና በኦሮምኛ ተተርጎሞ እንዲቀርብ ከ”ዩኒቲ ቡክስ” ጋር ባደረጉት ስምምነት መጽሐፋቸው አሁን ለአንባቢያን እንደቀረበ ጨምረው ያስረዳሉ፡፡ መጽሐፉ ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ አንባቢያን በ120 ብር፣ በውጭ ሀገራት ለሚገኙ ደግሞ በ25 ዶላር ይቀርባል፡፡