IMG_8588ኢሕአዴግ መራሹ መንግስት ለ40 ከመቶ ከተሜው ንጹሕ የመጠጥ ውሃ ማዳረሱን ከመግለጽ አልቦዘነም፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እና የሃገር ውስጥ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ግን አሃዙ ከ22 በመቶ እንደማይበልጥ ያስረዳሉ፡፡ ከጊዜ ጊዜ የመጠጥ ውሃ እጥረት እየከፋ መሄዱን መሬት ላይ ያለው ሐቅ ምስክር ነው፤ ሹማምንቱም ይሕን ለመካድ ሲቸገሩ ማየት ተችሏል፡፡ መንግስት በቀዳሚ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ በዘርፉ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያስመዘግብ ተስፋ ሠጥቶ ነበር፤ ጠብ የሚል መፍትሔ አልታየም እንጂ፡፡

[ዳንኤል ድርሻ ያዘጋጀውን ዘገባ መዝገቡ ሀይሉ በድምፅ አዘጋጅቶታል አድምጡት አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ]

 

በ“ላንሴት” ማጋዚን ጥናታዊ ዘገባ… እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሃገራት ውስጥ በጦርነት፣ በሽብር ጥቃት እና በሁከት ሕይወታቸው ከሚያልፍ ዜጎች ይልቅ በውሃ ብክለት በሚመጡ በሽታዎች የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በእጀጉ እየጨመረ ነው፡፡ በውሃ ጣጣ በዓመት ሠባት መቶ ሺህ ሕጻናት (በቀን 2000) ይቀጫሉ፡፡ የሚሞቱት ሕጻናት ብዛት በቀን 4000 እንደሚጠጋ የሚገልጸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት… በአፍሪካና ኤዥያ ከአስር ሰዎች ስድስቱ ንጹሕ ውሃ እንደማያገኙ ይጠቁማል፡፡ የ“ዋተር ፓርትነርስ ኢንተርናሽናል” ኃላፊ ማርላ ስሚዝ ኔልሰን “…ከንጹሕ ውሃ እጥረትና እጦት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ከአምስት ሕጻናት ውስጥ አንዱ ዕድሜው 5 ዓመት ሳይሞላ ይሞታል” በማለት ነው የአደጋውን ክብደት ያስረዱት፡፡

ከ12 ወንዞቿ 122 ቢሊየን ሜትር ኩብ (ሜ.ኩ) ዓመታዊ ፍሰት የምታገኘው ኢትዮጵያ… የከርሰ ምድር የውሃ ሃብቷ 6.5 ሜ.ኩ ይጠጋል፤ በአማካይ አንድ ኢትዮጵያዊ በዓመት 1575 ሜ.ኩ ይደርሰዋል እንደማለት፡፡ ለመጠጥ የዋለው ከ3 በመቶ አለመብለጡ የሚያስቆጭ ነው፡፡ “የአፍሪካ የውሃ ማማ” የምትሠኘው ሃገር በሁለት አብይ ምክንያቶች በሃብቷ ልትጠቀም አልቻለችም፡፡ በድርቅ እና በመልካም አስተዳደር እጦት፡፡ ለሁለት አሠርት የተመላለሰው ድርቅ የውሃ ጉድጓዶችን ብቻ ሳይሆን ሐይቆችን ሳይቀር አድርቋል፤ ለተደጋጋሚ ግጭቶች መንስዔ ሆኗል፤ ድርቅና ረሃብን የሚከተሉት ኮሌራና ተቅማጥ እንደ ከዚህ ቀደሙ የሕጻናትን ሕይወት እየቀጠፉ ነው፡፡

የመልካም አስተዳደር እጦት ያስከተለውን ቀውስ በርዕሰ መዲናይቱ መመልከት ይቻላል፡፡ የአዲስ አበባ ሕዝብ ብዛት ከአንድ መቶ ሺህ ወደ 2.7 ሚሊየን ለማደግ የፈጀበት 50 ዓመት ብቻ መሆኑን የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ባለሥልጣን ዋቢ ነው፡፡ “ዩኤን ሃቢታት” በበኩሉ በ2010 የአዲስ አበቤዎች ብዛት 3.5 ሚሊየን ይደርሳል ሲል ይተነብያል፡፡ ከ15 ዓመት በፊት በቀን 204 ሺህ ሜ.ኩ የነበረው የከተማይቱ የመጠጥ ውሃ ፍላጎት በ2006 ወደ 431 ሜ.ኩ አድጓል፤ በ2020 ደግሞ 1.1 ሚሊየን ሜ.ኩ ይደርሳል፡፡ የሕዝብ ብዛቱና የውሃ አቅርቦቱ ግን ፈጽሞ ለንጽጽር የሚበቃ አይደለም፡፡ በአቃቂ ወንዝ ተፋሰስ ለምትገኘው አዲስ አበባ… ከጉድጓዶች ውጪ ዛሬም ዋነኛ የውሃ ምንጮች ከ40ና 50 ዓመት በፊት የተሰሩት ለገዳዲ፣ ገፈርሳ፣ አባ ሳሙኤል ናቸው፤ ለገዳዲን ውሃ እንዲቀልብ የተሰራው ድሬ እንኳ ከተገነባ ሁለት አሠርት አልፎታል፡፡

የአ.አ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን… በከተማዋ የንጹሕ መጠጥ ውሃ ሽፋን 97 % መድረሱን ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ከ5 ዓመት በፊት 85 ሊትር የነበረውን ዕለታዊ የነፍስ ወከፍ ፍጆታ በቅርቡ 100 ሊትር አስገባለሁም ብሎ ነበር፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት ግን የተጠቀሰው ቁጥር በእጅጉ የተጋነነ መሆኑን አሳይቷል፤ በዩኒቨርሲቲው የአ.አ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲቲዩት ባደረገው ጥናት ተጣርቶ ከሚወጣው ውሃ 37 ከመቶው ለተገልጋዩ ሳይደርስ ባክኖ ይቀራል፡፡ ለብክነቱ ወና ምክንያቶች የበሰበሱ ቧንቧዎች ናቸው፡፡ 5000 ኪሎ ሜትር ከሚረዝመው ቧንቧ እኩሌታው ከተዘረጋ 25 ዓመት አልፎታል፡፡

IMG_8299

ግማሽ ክፍለ ዘመን ዕድሜ ያስቆጠሩት የነ ለገዳዲ ግድብ በደለል መሞላት እና የውሃ ጉድለት ደግሞ ችግሩን እስካሁን ከነበረው መጥፎ ሁኔታ የሚያብሰው ነው፡፡ የለገዳዲ ክምችት አቅም ከ2,466 ሜትር በላይ ቢሆንም፣ በድርቁ የተነሳ የገባለት ውሃ ከ2,465 ሜትር ማለፍ አልቻለም፤ የአንድ ሜትር ቅናሽ ግድቡን 5 ሚሊየን ሜ.ኩ ውሃ ያሳጣዋል፤ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የድሬ ግድብ ለለገዳዲ የሚያቀብለው 5 ሚሊየን ሜ.ኩ ከሚቀጥለው ወር አንስቶ ሙሉ በሙሉ ይቋረጣል፡፡ ሁኔታው እስከ ሐምሌ ወር ባለበት ይቀጥላል፡፡ ስለዚህም የተሻለ ውሃ ያገኙ የነበሩ የከተማዋ ክፍሎች ሳይቀሩ በሳምንት ከ4 ቀን በላይ ማግኘት አይችሉም፡፡ 97 % ደርሻለሁ ያለው የአ.አ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ቀውሱን አድበስብሶ የሚያልፍበት አቅም በማጣቱ በይፋ የፈረቃ ሥርጭት መጀመሩን አውጇል፡፡

የወንዞች፣ ጉድጓዶችና ምንጮች መበከል ሌላ “ራስ ምታት” ሆኗል፤ ከ2700 ከሚበልጡ  የከተማይቱ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ፍሳሽ የማከም (ትሪትመንት) ሲስተም ያላቸው 10 ከመቶው ናቸው፡፡ 90 በመቶ የሚደርሱት ቱቦ ዘርግተው፣ በካይ ፍሳቸውን ከአቃቂ ወንዝ ጋር ይቀላቅሉታል፡፡ የማዘጋጃ ቤት ቆሻሻዎች እና ከሆስፒታል ላቦራቶሪዎች የሚወጡ ፍሳሾችም መጨረሻቸው አቃቂ ወንዝ ነው፡፡

በወንዞቹ ያለው ውሃ ለመጠጥ ሊቀርብ እንደማይችል ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡ ኢንዱስትሪ ባልተተከለበት የእንጦጦ ወንዝ መነሻ… በአነስተኛ መጠን የታዩት ክሮሚየም እና ማንጋኒዝ ንጥረ ነገሮች… ፋብሪካ በብዛት ባለበት ደቡባዊ የአዲስ አበባ አካባቢ ወንዝ እስከ 14 ሚሊግራም በሊትር ክምችት ተገኝቷል፡፡ በዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት ከ0.1 በላይ ሚሊግራም/በሊትር ማንጋኒዝ የተከማቸበት ውሃ ለኢንዱስትሪም ሆነ ለመጠጥ አገልግሎት አይውልም፡፡ በማዕድን ውሃ ውስጥ በሊትር 728 ሚሊግራም ናይትሬት መገኘቱም ተጠቅሷል፤ የዓለም ጤና ድርጅት የናይትሬት መጠን ከ10 ሚሊግራም/በሊትር ሊበልጥ አይገባም ነው የሚለው፡፡ ኢንዱስትሪዎች… በተለይ የቆዳ ፋብሪካዎች ዋና በካዮች መሆናቸው ቢረጋገጥም… ለመፍትሔ የሚያቃርብ እርምጃ ሲወሰድ መመልከት ግን አልተቻለም፡፡