በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት መንግስቱ ኃይለማርያም የተጻፈው “ትግላችን” የተሰኘው መጽሐፍ ሁለተኛ ቅጽ ዛሬ በገበያ ላይ ዋለ፡፡ አራት መቶ ገጾች ያሉት ሁለተኛው ቅጽ 14 ዋና ዋና ክፍሎችንና 60 ምዕራፎችን ይዟል፡፡ ቅጽ ሁለት እንደ መጀመሪያው ሁሉ “የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ የትግል ታሪክ” የተመዘገበበት መጽሐፍ እንደሆነ በሽፋን ገጹ ላይ የተገለጸበት ነው።
ሌተናል ኮሎኔል መንግስቱ ከአራት ዓመት በፊት ለንባብ በበቃው ቅጽ አንድ መጽሐፋቸው ደርግ ወደ ስልጣን ከመጣበት ዋዜማ አንስቶ የመጀመሪያዎቹን አምስት ዓመታት ዳስሰው ነበር፡፡ በሁለተኛው ቅጽ ደግሞ ቀጣዮቹ አምስት የደርግ አገዛዝ ዓመታት ምን ይመስሉ እንደነበር ጽፈዋል፡፡ በሱማሌ ወረራ የሚንደረደረው መጽሐፍ የኤርትራን ጉዳይ አንስቶ ስለ መከላከያ ኢንዱስትሪዎች ጠቃቅሶ ብሔራዊ አብዮታዊ የምርት ዘመቻን ታክኮ ለሰላም የተደረጉ ጥረቶችን በመዘርዘር ይደመደማል።
ኮሎኔል መንግስቱ በመጀመሪያው መጽሐፍ የደረሰባቸውን “የሰሩትን ስህተት ያለማመን” ችግር የከነከናቸው ይመስላል፡፡ በሁለተኛው መጽሐፋቸው ጀርባ ገጽ ከታተሙ አምስት ቁንጽል የመጽሐፉ ክፍሎች ውስጥ አንዱ ከስህተት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ “ብርጋዴር ጀነራል ተፈሪ በንቲን የደርጉ ሊቀመንበር ማድረግና ብርጋዴር ጀነራል ጌታቸው ናደውን በቅድሚያ፣ የምድር ጦር አዛዥ በኋላም የኤርትራ ክፍለ ሀገር አስተዳዳሪና የመላው የሰሜን መለዮ ለባሽ ሠራዊት አዛዥ በማድረግ ረገድ የተሰራው ስህተት የማንም ሳይሆን የእኔ ነበር” ሲሉ ክርክር በሚያስነሳ መልኩ ጽፈዋል።
ፕሬዝዳንት መንግስቱ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ሜካናይዝድ ብርጌድ ሲቋቋም አዛዥ ስለነበሩት ጌታቸው ናደው የነበራቸው አመለካከት ለጀርባ ገጽ ከተመረጡት ጥቅሶች ሌላኛው ነው፡፡ “አለባበስ የሚያውቁ፣ ቁንንና ኩሩ፣ በጣም አጭር የማይባል አማካይ ቁመት፣ ከላይ እስከ ታች የተደላደለ እና የተገነባ ሰውነት፣ ገብስማ ጸጉር እና ግርማ ሞገስ ያላቸው መኮንን ናቸው፡፡ ጠቅላላ ባህሪያቸው እና ወታደራዊ አመራራቸውን ስወድ፣ የማልወድላቸው ነገር ቢኖር ጀብደኝነታቸውን እና ጉረኝነታቸውን ነበር” ሲሉ በአንድ የቅርብ ረዳታቸው በመሆን ስላገለገሏቸው ወታደራዊ መኮንን ይገልጻሉ።
በመጽሐፉ ከጌታቸው ናደው ሌላ ስለ አማን አንዶም፣ ኢሳይያስ አፈወርቂ፣ ተፈሪ በንቲ እና ተድላ ባይሩን ስለመሳሰሉ ሰዎች የቀድሞው ፕሬዝዳንት የነበራቸው ግላዊ ነገር ግን አወዛጋቢ አመለካከት ተንጸባርቋል፡፡ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ከተቀላቀለች በኋላ ኢየሩሳሌም ባለው የኢትዮጵያ ገዳም ተመድበው የነበሩት አቡነ ፊሊጶስ ስለ ኢሳይያስ ማንነት ለመንግስቱ እንዳጫወቷቸው በመጽሐፉ የተገለጸው ክፍል በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል።
“ዛሬ የሻዕቢያ መሪ የሆነው ኢሳይያስ አፈወርቂ ኤርትራ ይወለድ እንጂ አባቱም እናቱም የትግራይ ተወላጆች ሲሆኑ እሱን ያሳደጉትና ያስተማሩት ደግሞ የወሎ ክፍለ ሀገር እንደራሴ የነበሩት እና የታወቁት ኢትዮጵያዊ አጎቱ ደጃዝማች ሰለሞን አብርሓ በደሴ ከተማ ነው” ሲሉ መንግስቱ ጳጳሱን ጠቅሰው ጽፈዋል፡፡
ለጥቀውም ” ‘ለብዙ ታቦቶች ተስላ ከጸነሰችው ሽል ጨንግፎ ገደላት’ እንደሚባለው አረቦች ካዘመቱብን ከጀብሐ ይልቅ ለአንድነታችን አስጊ ሆኖ የተገኘው እኛ የፈጠርነው ሻዕቢያ ነው መባሉ በእጅጉ አስገርሞኛል፣ አሳዝኖኛልም” ይላሉ።
ኮሎኔሉ በመጽሐፉ መግቢያ ሌላ በእጅጉ ያሳዘናቸውን ነገር ጠቅሰዋል፡፡ ሀዘኔታቸው የመነጨው “ብዙ ደከምኩበት” የሚሉት የመጀመሪያው ቅጽ መጽሐፍ አንባቢ እጅ ሳይደርስ “ከንቱ መባከኑ” ወይም “መውደሙ” ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ተጠያቂ የሚያደርጉት “ራሱን የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢ.ሕ.አ.ፓ) ብሎ የሚጠራው የፖለቲካ ድርጅት የአመራር አካላትና አባላት ቅሪት የሆኑ” ናቸው ሲሉ ይከሳሉ፡፡ ፕሬዝዳንቱ የመጀመሪያ መጽሐፋቸው “ስካን” ተደርጎ በኢንተርኔት የመሰራጨቱን ድርጊት “አሳዛኝና አሳፋሪ ሻጥር” ሲሉ ይገልጹታል፡፡ የድርጊቱን ፈጻሚዎችም “ከታሪክ የማይማሩ፣ ጊዜና ዕድሜ የማይለውጣቸው እና የጥፋት መልዕክተኞች” ሲሉ ይተቿቸዋል።
በዚህ ምክንያት ቅጽ ሁለት ከአንባቢያን እጅ የደረሰው በቅጽ አንድ የነበሩ የህትመት እና ማከፋፈል ጉዳዮች ላይ ለውጦች በማድረግ ነው፡፡ የመጀመሪያውን ቅጽ ለህትመት ያበቃው እና መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው ጸሐይ አሳታሚ ሁለተኛውን መድገም አልቻለም። ሁለተኛው እንደመጀመሪያው ቀድሞ ለገበያ የበቃው በአሜሪካ ሳይሆን በኢትዮጵያ ነው።
“ከመጀመሪያው ህትመት አንድ አራተኛውን ለአንባቢ ባለመዳረሱና አሳታሚው ድርጅት በደረሰበት ኪሣራ ምክንያት ሁለተኛ ህትመት ማሳተም አልቻለም” ሲሉ መንግስቱ በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ስለጉዳዩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ የመንግሰቱን መጽሐፍ በዋናነት እያከፋፈለ የሚገኘው አይናለም የመጽሐፍት መደብር ነው።