- በኢትዮዽያ የርሀብ አደጋው እየከፋ መምጣቱን ተከትሎ አለማቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮዽያ መንግስትን ፈቃድ ሳይጠብቅ አዲስ የእርዳታ ጥሪ ለማቅረብ እየተዘጋጀ ነው።
የሚከተለው የግብርና ስትራቴጂ ስኬትማ እንደሆነ በተደጋጋሚ የሚያውጀው የኢትዮጵያ መንግስት በአየር ፀባይ ለውጥና በብልሹ አስተዳደር ምክንያት በተከሰተው ድርቅ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ከጊዜ ወደ ጊዜ የማሻቀቡ ነገር የማይፈልገውን ነገር ግን ግድ የሆነበትን የተረጂዎችን ቁጥር እና የእርዳታ መጠን እንደገና እንዲከልስ አስገድዶታል።
የድርቁ ጉዳት በፀናባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ለአመት ከመንፈቅ ያህል ጠብ አልል ያለው ዝናብ ነገሮችን እያወሳሰበ እና መጪውን ጊዜም አስፈሪ እያደረገው ይገኛል። የኢትዮጵያ መንግስት ከእርዳታ ለጋሾች ጋር ተጨቃጭቆ እና ተሟግቶ በየጊዜው ይፋ የሚያደርገው የሰብዓዊ እርዳታ ዶሴ በጉዳዩ ዙሪያ ለሚሰሩ ድርጅቶችና ኤምባሲዎች ወሳኝ ሰነድ ነው። በዚህ ሰነድ ላይ ተመስርተው ነው የእርዳታ እጃችሁን ዘርጉልን ኦፌሴሊያዊ ጥያቄ የሚያቀርቡት።
የዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ቁጥር አንድ ራስ ምታት ከሆነችው ሶሪያ እና ጦርነት አላባራ ካለባት የመን እኩል የኢትዮጵያ ጉዳይ አፅንኦት እንዲሰጠው ለጋሾችን የማሳመን ከፍተኛ የቤት ስራ አለባቸው።
“የሶሪያ ጉዳይ ገንዘቡን እየመጠጠ ነው” ይላሉ በህፃናት ዙሪያ የሚሰራ የግብረ ሰናይ ድርጅት ኃላፊ።
“አንድ ተራ ሶሪያዊ በኢትዮጵያ ከሚገኘው ተረጂ አስር እጥፍ የላቀ እርዳታ ይደርሰዋል። ” የኃላፊውን መከራከሪያ ቁጥሮችም ይደግፉታል። ለሶሪያ ሰብዓዊ ቀውስ ለጋሾች 10 ቢሊዮን ዶላር ሲሰጡ ለኢትዮጵያ ግን እስካሁን የለገሱት 700 ሚሊዮን ዶላር ነው። ይህ ማለት ኢትዮጵያ ያስፈልገኛል ብላ በህዳር 2008 ዓ.ም ከጠየቀችው 1. 4 ቢሊዮን ዶላር ያገኘችው እኩሌታውን ብቻ ነው።
ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን አሁን እያሳሰባቸው ያለው ገንዘቡ እንኳ አሁን ቢመጣ ለተረጂዎች የሚከፋፈለው እህልና ምግብ ከግዢው እስከ ማጓጓዙ ድረስ የሚፈጀው ጊዜ ነው። ይህ ጊዜ ከአራት እስከ ስድስት ወር ድረስ የሚወስድ መሆኑ ደግሞ መጪውን ጊዜ በስጋት እንዲመለከቱት አድርጓቸዋል።
ጉዳዩ ያሳሰባቸው አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት የኢትዮጵያ መንግስት የሚያወጣውን ሰነድ እንኳ መጠበቅ አልፈለጉም። የኢትዮጵያ መንግስትን እንደማያስደስተው ቢያውቁም የሚፈለገውን እርዳታ በአፋጣኝ ለማግኘት እና ህይወት ለማትረፍ ሲሉ ለየመንግስቶቻቸው በሚልኳቸው ሪፖርቶች የሰብዓዊ ችግሩን ደረጃ ወደ “L3” ከፍ አድርገውታል።
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች በሚከተሉት የአስቸኳይ ችግሮች ምደባ መሰረት “L3” ከጫፍ የሚቀመጥ
ነው። ድርጅቶቹ ይህን ምደባ የሚጠቀሙት ጉዳቱ ከፍ ላለ እና ለግዙፍ ሰብዓዊ ቀውስ ነው። እንደተባበሩት
መንግስታት የእርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA) ገለጻ መሰረት ተመድ እና አጋሮቹ በአሁን ወቅት በአራት ሀገራት
ያሉ ችግሮችን በዚህ ምደባ ፈርጀዋቸዋል። ሀገራቱ — ጎረቤታችን ደቡብ ሱዳን፣ በአቅራቢያችን የምትገኘው የመን
እና በመካከለኛው ምስራቅ ያሉት ኢራቅ እና ሶሪያ ናቸው።
“ፊት ለፊት L3 ብለን አንጠራውም። ነገር ግን እየሰራን ያለነው በዚያ ደረጃ ነው” ይላሉ አንዲት ምዕራባዊት ዲፕሎማት። የአሜሪካው ዩ.ኤስ.አይድ ከሳምንት በፊት ወደ ኢትዮጵያ የላከውን ቡድን ምንነት መመልከት የድርቁ ሁኔታ በለጋሽ ሀገራት እንዴት እየታየ እንደሆነ ተጨማሪ ማገናዘቢያ ይሰጣል። የድንገተኛ አደጋ ተከላካይ ኤክስፐርቶችን ያካተተው የመጀመሪያው የዩ.ኤስ.ኤይድ ቡድን Disaster Assistance Response Team
(DART) ይባላል። የሎጀስቲክ ጉዳዮችን የሚከታተል ሌላ ቡድንም በቅርብ ቀን ቀዳሚዎቹን እንደሚቀላቀልም
ተነግሯል።
በዓመት ወደ 65 ለሚጠጉ አደጋዎች ምላሽ የሚሰጠው ዩ. ኤስ.ኤይድ እንዲህ አይነት ባለሙያዎቹን
የሚልከው እንደ መሬት መንቀጥቀጥ ና ጎርፍ ላሉ አፋጣኝ እና ጉዳታቸው ላቅ ላሉ አደጋዎች ነው ይላሉ የዋዜማ
ምንጮች።
ምዕራባዊቷ ዲፕሎማት የኢትዮጵያን ድርቅ እና ያስከተለውን ቀውስ መጠን ትልቅነት ለማመላከት በችግሩ ምክንያት ከቀዬው የተፈናቀለውን ሰው ቁጥር በምሳሌነት ያነሳሉ። “በሀገር ውስጥ ያለው ስደት ትልቅ ነው። እስካሁን ከ250,000— 500,000 ሰው በችግሩ ምክንያት የነበረበትን ቦታ ለመልቀቅ ተገዷል።”
ለጋሾች አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሀን ወደ ኢትዮዽያ እንዲገቡ አፋጣኝ ፈቃድ እንዲስጥ መንግስትን ማግባባት ይዘዋል። መንግስት ግን ለአብዛኞቹ ጋዜጠኞች ፈቃድ መከልከሉና በሀገር ቤት ያሉትን ችግሩን እንዳያጋልጡ በመፍራት ማሰሩ አሳዛኝ መሆኑን ለጋሾች ያሰምሩበታል።
“ዕርዳታ ፈልገህ ችግርህን ደሞ ደብቀህ ውጤታማ መሆን አይቻልም፣ አሁን መንግስት ፈቀደም አልፈቀደም አለማቀፉ ማህበረስብ ህይወት የማትረፍ ግዴታ አለበት” ይላሉ በቅርቡ ኢትዮዽያን የጎበኙ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባልደረባ።
እየጨመረ የመጣው በምግብ እጥረት የተጎዱ ህጻናት እና እናቶች ቁጥርም የጉዳዩን አሳሳቢነት የሚመሰክር ነው።
በሳምንቱ መግቢያ የወጣው የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ ሪፖርት እንደሚያመለክተው 2.2
ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት፣ ነፍሰ ጡር እና በማጥባት ላይ ያሉ እናቶች በመጠነኛ የምግብ እጥረት ተጠቅተዋል።
450,00 ህጻናት ደግሞ በፅኑ የምግብ እጥረት ተጎድተዋል። 2.2 ሚሊዮን የነበረው አስቸኳይ የዘር እርዳታ
የሚያስፈልጋቸው ገበሬዎች ቁጥር ወደ 3.3 ሚሊዮን ከፍ ብሏል።
የሚፈለገው እርዳታ ማሻቀቡን ከተለያዩ ሪፖርቶች እና ከረጂዎች የማያቋርጥ ውትወታ የተገነዘበ የሚመስለው
የኢትዮጵያ መንግስት በየዘርፉ ያለውን ቁጥር ለመከለስ መስማማቱ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን አስደስቷል። የበልግ እና
መኸር ወቅቶችን ተከትሎ በዓመት ሁለቴ ይወጣ የነበረው የሰብዓዊ እርዳታ ሰነድ በአጭር ጊዜያቶች ውስጥ ሲከለስ
ለሶስተኛ ጊዜ ነው። በነሐሴና ህዳር ከወጡት ሰነዶች ተከታይ የሆነው እና የድርቅ ተጎጂዎችን ቁጥር ከ10
ሚሊዮን በላይ ከፍ እንደሚያደርገው የሚጠበቀው ሰነድ ዝግጅት ከሶስት ሳምንት እስከ ወር ሊወስድ እንደሚችል
በተባበሩት መንግስታት ያሉ የዋዜማ ምንጮች ያስረዳሉ።
የችግሩን አንገብጋቢነት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የሚጠቁሙት ዲፕሎማቷም ሆኑ የግብረ ሰናይ ድርጅቱ ኃላፊ
የሚያስፈራቸው አንድ ነገር አለ። ፍርሃታቸው አጥንታቸው ያገጠጠ እና ፊታቸው የጎደጎደ ህጻናት ምስል የዓለም
አቀፍ ብዙሃን መገናኛዎችን የፊት ገጽ እና የቴሌቪዥን ስክሪን እንዳያጣብብ ነው። ይህ ከመሆኑ በፊት ፈጣን
እርዳታ የድርቅ ተጎጂዎች ዘንድ እንዲደርስ እየተመኙ መጪውን በስጋት አሻግረው ይመለከታሉ።