በሙሔ ሐዘን ጨርቆስ (ለዋዜማ ራዲዮ ብቻ) 

እንዴት ናችሁልኝ!? እኔ ያው ደህና ነኝ፡፡ ድሮስ ኮንዶምንየም የተመዘገበ ሰው ምን ይሆናል ብላችሁ ነው፡፡ ምን ቢማረር በመንግሥት አይጨክን!!

Luxury Mansions Under Construction @Wazema
Luxury Mansions Under Construction @Wazema

መቼ ለታ በ‹‹ሀይገር›› አውቶቡስ ወደ ‹‹ሲኤምሲ›› ተሳፍሬ ከሾፌሩ ጎን ጥቅስ አነበብኩ፡፡ ‹‹20/80 የተመዘገበና የተጠመቀ ዳነ›› ይላል፡፡ አልሳቅኩም፡፡ እንዲያውም ፈራሁ፡፡ አሽሙርና አሽሙረኛ ፈሪሃ እግዚአብሔር ባደረበት ሕዝብ መሐል ሲበዛ፣ ‹‹እረኛ ምን አለ›› የሚል ንጉሥ የመጥፋቱ ምልክት አድርጌ ስለምረዳው እፈራለሁ፡፡

ይህቺ ጥብሳ ጥብስ ስታጣ በጥቅሳ ጥቅስ የተዥጎረጎረች ከተማ አላማረችኝም፡፡ ‹‹ጠቃሾቿ›› በብዕር ፈንታ ‹‹ክሪክ›› ያነሱ ዕለት….ወየውላት፡፡ የታክሲ ወያላ ያለነገር አይሸሙርማ፡፡ የታክሲ ወያላ ስድብ ትቶ ባለቅኔ ሲሆን ለአንድ ታዳጊ አገር ጥሩ ምልኪ አይደለም፡፡  ጥቅሷ ኮርኩራኝ እንዲህ ስል ተቀኘሁ፡፡

ወያላ የወየነ ‘ለት፣

ያን ጊዜ ነው “ዋ” ማለት፡፡

ወያላ የወየነ ‘ለት፣

ተሳፋሪም አለቀለት፣ ወራጅም ጉድ ፈላበት፡፡

በዚህ የተመሰጠረ ቅኔ ዉስጥ ‹‹ወራጅ›› የሚለው ቃል ፍካሪያዊ ትርጉም ከሥልጣናቸው በሕዝብ አመጽ የሚወርዱ ሹመኞችን ያመለክታል፡፡ ይቺን ቅኔ ለከንቲባው ጽሕፈት ቤት መላክ አማረኝ፡፡ እውነት እውነት እላችኋለሁ ‹‹እረኛ ምናለ?›› የማይል ንጉሥ፣ ‹‹ወያላ ምን አለ?›› የማይል ከንቲባ ቢነግሡም ለመንፈቅ፣ ሲወድቁም መቀመቅ…፡፡

[ጦማሩን በድምፅ ሸጋ አድርገን አሰናድተነዋል አድምጡት]

ዉድ የዋዜማ ታዳሚዎች!

አወዳደቃቸው የማያምር ነገሥታት አወዳደቃቸውን ለማሳመር የስፖንጅ ፍራሽ ሳሎናቸው ዉስጥ ቢዘረጉ ከስብራት ይድናሉ እንዴ?   እንደኔ አወዳደቁ የማያምር ንጉሥ ከሕዝብ ርቆ ቤተ መንግሥት ለማስገንባት ጥልቅ ጉድጓድ ባያስቆፍር ነው የሚበጀው እላለሁ፡፡ ጉድጓዱ ዉስጥ ማን እንደሚገባበት አይታወቅማ፡፡ ንጉሥ ጋዳፊን ያየ በጥልቅ ጉድጓድ ቀርቶ በቦይስ ይቀልዳል እንዴ?!

አድማጮቼ!

ለመንደርደር ያህል ይህን ካልኩ ዘንዳ….እስቲ ለዛሬ የኛዎቹ ነገሥታት ጥልቅ አስቆፍረው እያስገነቡት ያለውን ቤተ መንግሥት ላስቃኛችሁ፡፡ ለተራው ሕዝብ ሹክሹክታን የማይመክት የጋራ መኖርያ ቤት በ10 ዓመት አንዴ እየገነቡ በዕጣ የሚያድሉት ሹማምንት ለራሳቸው ሲሆን ‹‹ሳሎኑ ጎልፍ የሚያጫውት›› የጋራ ቤተ መንግሥት ገንብተው በመንፈቅ ይጠናቀቅላቸዋል፡፡ ለመሆኑን ስንቶቻችሁ በየካ ኮረብታ ላይ ስለሚገነቡት የተራራ እልፍኞች ታውቁ ይሆን?

ከሰላምታዬ ቀጥዬ የማስቃኛችሁ ነገር ቢኖር በአካል ተገኝቼ ያያሁትን ይህንኑ የነገሥታት ሠፈር ይሆናል፡፡

###

እስኪ ካላችሁበት ሰፈር ወደ ‹‹ሲ-ኤም-ሲ›› ምናባዊ ታክሲ ያዙ፡፡ የታክሲው ሰልፍ ከረዘመ ባቡር ተሳፈሩ፣ ባቡሩ ከሞላባችሁ ሞልቶ የማይሞላ 119 ቁጥር አንበሳ አውቶቡስ አለላችሁ፡፡ እንደምንም ራሳችሁን ከዉስጡ አኑሩ፡፡ ሰዎች ሆይ! በሕይወት መሳፈርን የመሰለ ደግ ነገር የለም፡፡ የነአባዱላን ሰፈር ጨምሮ ብዙ ያሳያል፡፡

ታስታዉሱ እንደሁ በሙስና የማይታማው ደርግ በመውደቅያው ዋዜማ ለራሱ ባይሆንም ለዲፕሎማቶች ቤት ገንብቶ ነበር፡፡ እነዚያ ቤቶች እስካሁንም የ‹‹ሴ-ኤም-ሲ›› ቤቶች ተብለው ይጠራሉ፡፡ እዚያ ጋር ስትደርሱ ‹‹ወራጅ!›› በሉ፡፡ እንደወረዳችሁ ፊታችሁን ወደ ሰሜን ስታዞሩ በኢትዮጵያ የመጀመርያ የሆነውን ዘመናዊ የከተሜ መንደር ወይም (Urban Complex) ታገኛላችሁ፡፡ ይህ ወደ ሰማይ እያረገ ያለ የሚመስለው ‹‹ፖሊሎተስ›› አፓርትመንት መንደር ‹‹ፀሐይ ሪልስቴት›› ይባላል፡፡ በ30ሺ ካሬ ቦታ ላይ 11 የሚሆኑ ሕንጻዎች እጅብ ብለው የቆሙበት ግቢ ነው፡፡

ምንም እንኳ የፖሊሎተስ ክፍሎቹ ከርቀት በተናጥል ሲታዩ እንደ ቻይናዊያኑ ዐይኖች ጠበብ ያሉ ቢመስሉም የአፓርትመንቶቹ ቁመና በአመዛኙ ዘለግ ያሉ መሆናቸው ለአካባቢው ልዩ ግርማን አላብሰውታል፡፡ ሦስት ቢሊየን ብር የፈጁት አፓርትመንቶቹ G+12 የሆኑ 17 ሕንጻዎችን ይዘዋል፡፡ ከ17ቱ አስራ አንዱ አሁን እየተጠናቀቁ ነው፡፡ እንዲያውም ልክ የዛሬ ሦስት ወር ለገዢዎች ይተላለፋሉ፡፡ ኤርሚያስ አመልጋ አንድ ቢሊዮን ብር ሰብስቦ በሰባት ዓመት ዉስጥ አንድ ክፍል ቤት አላስረከበም፡፡ ቻይና ዱዲ ሳትቀበል በዓመት ተኩል 646  ቤቶችን ሠርታ ልታስረክብ ነው፡፡ የቻይናን ልቦና ይስጠን አቦ!

###

ለመሆኑ ‹‹ፀሐይ ሪልስቴት›› የማን ነው? ስሙ ያወዛግብ እንጂ ሙሉ በሙሉ የቻይኖች ንብረት ነው፡፡ “የዉጭ ድርጅቶች በቤት ልማት ለመሳተፍ የሚያበቃቸው የሕግ አግባብ የለም” አልተባለም እንዴ?” እንዳትሉኝ፡፡ ‹‹ቻይና የዉጭ ዜጋ ናት እንዴ?›› እላችኋለሁ፡፡

የፀሐይ ሪልስቴት የአንበሳው ድርሻ የ‹‹ጂኦሎጂ ኮርፖሬሽን ኦቨርሲስ ግሩፕ›› (CGCOC) ሲሆን ከፊሉ ድርሻ ደግሞ ሚ/ር ቼን ሼአዎ የተባሉ ቻይናዊ ቱጃር የግል ንብረት ነው፡፡ ይህን ዘመናዊ የአፓርትመንት ግንባታ መርቀው ያስጀመሩት ደግሞ ቻይንኛ (መንደሪን) አቀላጥፈው የሚናገሩት ፕሬዚዳንታችን ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ናቸው፡፡ (CGCOC) የተባለው የቻይና ኩባንያ ከዓመታት በፊት ጀሞ አካባቢ ‹‹ሀንሰም የመስታወት ፋብሪካን›› የገነባ ኩባንያ ነው፡፡ ይህ የመስታወት ፋብሪካ በከፊል የወይዘሮ አዜብ መስፍን ንብረት ነው የሚሉ ሐሜቶች ሕዝብ ጆሮ ደርሰው ነበር ያኔ፡፡ ኾኖም እስካሁን ተጨባጭ መረጃ ቀርቦባቸው አያውቅም፡፡ 

Tsehai Real Estate
Tsehai Real Estate

ፀሐይ ሪልስቴት አስራ አንድ የሚሆኑ ባለ 13 ፎቅ ሰማይ ጠቀስ ዘበናይ አፓርትመንቶችን ለማስረከብ 3 ወራት ብቻ እንደቀሩት ነግሪያችኋለሁ፤ ኾኖም ይህ ደብዳቤ እናንተ እጅ እስኪደርስ ድረስ ቤቶቹን ሙሉ በሙሉ ሽጦ እንዳልጨረሰ አረጋግጫለሁ፡፡ አንዱ ምክንያት ዋጋው የሚቀመስ አለመሆኑ ነው፡፡ 133 ካሬ የኾነ አንድ ባለ 4 መኝታ ቤት ለመግዛት 4 ሚሊዮን ብር መቁጠር ያስፈልጋል፡፡  በካሬ ከ23ሺ እስከ 26ሺ ብር ይጠይቃሉ፡፡ በአስራ አንዱ ፎቆች ጣሪያ ላይ ተንጠላጥሎ ለመኖር የሚሻ ሰው ደግሞ ቅንጡ የቆጥ ቪላ ወይም “Penthouse” ሊገዛ ይችላል፡፡ ዋጋውም ከ7 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር አምስት ሳንቲም አይቀንስም፡፡ 230 ካሬ ነው ለዚያውም፡፡ መስኮት፣ በር፣ ሴራሚክ፣ ወለል ንጣፍና ሌሎች የዉስጥ ሥራዎች በሙሉ የገዢው ጣጣዎች ናቸው፡፡ እነርሱ “ቻክ” አድርገው ብቻ መስጠት ነው፡፡ የቻይናን ልቦና ይስጠን አቦ!

በፀሐይ ሪልስቴት መኖር የተለዩ ጥቅሞች አሉት ከተባለ ቆሻሻን ራሱ ከየቤቱ እየለቀመ የሚያስወግድ የቻይና ካምፓኒ፣ ጽዱና አረንጓዴ ግቢ እንዲኖር ሥራዬ ብሎ የሚተጋ ሌላ የቻይና ካምፓኒ፣ የአፓርትመንቱ ምድር ቤት ዉስጥ ለሁሉም ነዋሪ በነፍስ ወከፍ ኮተት የሚቀመጥበት ግምጃ ቤት፣ ለአንድ ቤተሰብ አንድ መኪና ለማቆም የሚያስችል የመኪና ማቆምያ ስፍራ፣ 24 ሰዓታት የማይቋረጥ የመብራትና የዉኃ አገልግሎት ማቅረብ መቻሉ ነው፡፡

ዉድ የጦማሬ አንባቢዎች! እንዲሁም ክቡራትና ክቡራን

የነገሥታቱን ሰፈር ላስጎበኛችሁ ቃል ገብቼ ፀሐይ ሪልስቴት ዉስጥ መኳተኔ የነገስታቱ ሰፈር ዝም ተብሎ ዘው የሚባልበት ስላይደለ ነው፡፡ በርግጥ ፀሐይ ረልስቴትን ያስቃኘሁበት ሁነኛ ምክንያት ሳይኖረኝ ቀርቶ አይደለም፡፡ ለጊዜው ሁለቱን እጠቅሳለሁ፡፡

አንደኛ የፀሐዩ መንግሥታችን ባለ ዐምባ ራሶች እንዲኖሩበት የታሰበው ዐምባ  የሚገኘው ከፀሐይ ሪልስቴት አፓርትመንቶች ጀርባ በመሆኑ ነው፡፡ ሌላም ምክንያት ደግሞ ይህ ነው፡፡ ባለሥልጣኖቻችን በትግል ዘመንና በስልጣን ዘመን ያፈሯቸው ጎረምሳ ልጆች በዚህ በፀሐይ ሪልስቴት መንደር በነፍስ ወከፍ አንድ አንድ አፓርትመንት እንደተገዛላቸው በስፋት መነገሩ ነው፡፡ ልክ እናንተ ለአመት በዓል ለልጆቻችሁ ልብስ እንደምትገዙት ማለት ነው፡፡ ፖሊሎተስ የገዢዎችን ማኅደር በምስጢር የመያዝ ጥብቅ መመሪያ ስላለው በዚህ ጉዳይ ላይ ከሐሜት ከፍ ያለ ተጨባጭ መረጃ ይዤ መቅረብ ባለመቻሌ አዝናለሁ፡፡ ለዚህም ዉድ የጦማሬ አንባቢዎችን ከፍ ያለ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ የአንድ ሁለት- ሦስት ባለሥልጣናትና ልጆቻቸው ስም ግን ከፀሐይ ሪልስቴት ጋር ተደጋግሞ መነሳቱ አልቀረም፡፡ በተለይ በሹመትም በዝምድናም ወደ ቻይና እግር የሚያበዙት ሹማምንት የሸገር የሐሜት ወፍጮ ደጋግሞ ያነሳቸዋል፡፡

###

Tsehai Real Estate site
Tsehai Real Estate site

የፀሐይ ሪልስቴት ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች ርዝመት በምሥራቅ የምትወጣዋን ፀሐይ ሊጋርዱ ይችሉ ይሆናል፡፡ የፀሐዩ መንግሥታችንን ባለሥልጣናት ቪላዎች ሊጋርዱ ግን አይቻላቸውም፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡ ቪላዎቹ በሙሉ ከፀሐይ ሪልስቴት አፓርትመንቶች ጀርባ ከፍ ያለ ኮረብታ ላይ መገንባታቸው ነው፡፡ የትኛውም አዲስ አበባ ላይ የሚገነባ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻ ሊጋርዳቸው የማይቻለውም ለዚሁ ነው፡፡ በቦታው ተገኝቼ ማየት እንደቻልኩት ይህ ኮረብታ የአዲሳባን ሁለት አራተኛ ሰፈሮች ማየት ያስችላል፡፡ በመገንባት ላይ የሚገኙትን የባለሥልጣናት ቪላዎች በአንደኛው ሰገነት ላይ ወጥቼ ማየት እንደቻልኩት ደግሞ የትኛውም አውሮፕላን ሲነሳና ሲያርፍ ቁልጭ አድርጎ ማየት የሚያስችል ዕይታ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ የአውሮፕላን አብራሪው የደህንነት ቀበቶ መታጠቅ አለመታጠቁ ሳይቀር አይታይም ብላችሁ ነው ጎበዝ! “Extraordinary and Breathtaking Panoramic View including landing and takeoff from Bole International Airport” ይላል ቦታው ለባለሥልጣናት በምን አግባብ እንደተመረጠ የሚያስረዳ ከተክለ ብርሃን ዐምባዬ ኮንስትራክሽን ወይም ታኮን ያገኘሁት አንድ ሰነድ፡፡

###

የራስ አሉላ ኮረብታ

በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ የወረዳ 13 ራስ አሉላ ኮረብታን የሚያህል ዉብ መንደር ከዚህ በኋላ አዲስ አበባ ዉስጥ የትም-መቼም ሊፈጠር አይችልም፡፡ ቦሌ መድኃኒዓለም፣ ቦሌ 17-17፣ ሳር ቤት፣ሳር ቤት ገብርኤል-12 ቀበሌ (ይህ ሰፈር በተለይ ሸክ አላሙዲ ለግላቸውና ለወደዷቸው ቆንጆዎች አዘውትረው ቤት የሚገዙበት ሰፈር ነው)፣ ለገጣፎ ካንትሪ ክለብ፣ጃክሮስ መንደር…. እነዚህ ሁሉ በአዲሳ አበባ አይነኬ የሞጃ ሰፈሮች ናቸው፡፡

አሁን አንድ ጊዜ ልብ ብላችሁ አድምጡኝ! ከሁለት ዓመታት በኋላ የእነዚህ ሰፈሮች ዉበትና ዋጋ ተደምሮ በአንድ ሚዛን ቢቀመጥና የየካ ራስ አሉላ ኮረብታ በሌላ ሚዛን ቢቀመጥ የካ በብዙ ርቀት ሚዛን የሚደፋ እንዲሁም የሚያስቀና የሞጃዎች ሰፈር ይሆናል፡፡ በዚህ አንድም ጥርጥር አይግባችሁ፡፡ ይህን ቃሌን ያዙ፡፡ እንደ ትንቢት ሳይሆን እንደ እውቀት ቁጠሩት፡፡ ይህ የሚሆነው በየካ ኮረብታ ባለሥልጣናቱ ስድስት ቤቶችን ስላስገነቡ ብቻ ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል፡፡ ከዚህ የላቁ ብዙ ምክንያቶች ከዚህ በታች እዘረዝራለሁ፡፡ እርግጥ ነው የሹማምንቱንና የነገሥታቱን  ዳና ተከትለው እኛም የንጉሣዊያን ቤተሰቦች ነን ብለው ያመኑ በአመዛኙ ከአንድ ብሔር ጥላ የተሰባሰቡ ድንገቴ ባለሐብቶች ወደዚህ ኮረብታ መትመም ጀምረዋል፡፡ አፍሪካ ዉስጥ ይኖራል ተብሎ የማይገመት መንደር እየገነቡም ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ብቸኛ ምክንያት አይደለም፡፡

የአካባቢው ገጽታ ዳሰሳ

ሎስአንጀለስ ካሊፎርንያን የሚያውቁ ‹‹ይህ እኮ የሸገር “ቢቨርሊ ሂልስ” ነው ይሉታል የየካ ኮረብታን፡፡ ከአገር ወጥቼ የማላውቀው እኔ ግን ‹‹የነአባዱላ ሰፈር›› ብዬዋለሁ፡፡ ለምን በሉኝ…

የአሁኑ አፈጉባኤና የቀድሞው ጄኔራል የተከበሩ አቶ አባዱላ እኔ የማውቃቸው ብቻ አራት ልብ የሚያርዱ ቪላ ቤቶችናእልፍኝ ታዳራሾች (Mansions) አሏቸው፡፡ አንዱ ቦሌ ወሎ ሰፈር ይገኛል፣ ሁለተኛው ቦሌ ሸዋ ዳቦ ጀርባ ይገኛል (ንብረትነቱ የኪራይ ቤቶች ነው አሁን የሚኖሩትም እዚህ ነው)፣ ሦስተኛው ለገጣፎ ‹‹ሲሲዲ›› ካንትሪ ክለብ የሞጃዎች ሰፈር ይገኛል፣ አራተኛው ደግሞ አዳማ ላይ ያስገነቡት ቪላ ነው፡፡ የያንዳንዱ ቪላዎቻቸው ወቅታዊ አማካይ ዋጋ 15 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ባለመዶሻውና ሳቂታው አፈጉባኤያችን ቀላል ሰው እንዳይመስሏችሁ፡፡ መዶሻ ይዘው የሚስቁትም ያለምክንያት አይደለም፡፡

ከዓመታት በፊት ‹‹ይህን የአዳማውን ቪላ ይዤ ለትግል አይመቸኝም›› ብለው ለኦሕዴድ በስጦታ አስረክበውት የነበረ ቢሆንም ኦሕዴድ ግን ‹‹ግዴለም ይያዙት፣ ባይሆን ሌላ ጊዜ…›› ብሎ መልሶላቸዋል፡፡

የሚገርመው ከርሳቸው በተቃራኒ የሚቆሙት ሟቹ አቶ አለማየሁ አቶምሳ አንድም  ቤት በስማቸው አልነበራቸውም፡፡ የሥልጣን ዘመናቸውን ከፊንፊኔ ይልቅ ባንኮክ ነበር ያሳለፉት፡፡ የርሳቸውን ድንገተኛ ሞት ተከትሎም ቤተሰባቸው ለመበተን ተቃርቦ የነበረ ሲሆን በየካ ክፍለከተማ የኦህዴድ አባላት የማግባባት ሥራ ሠርተው አንድ የኪራይ ቤት በዚሁ ክፍለከተማ ተፈልጎ እንዲሰጣቸው ሆኗል፡፡

የነአባዱላ ሠፈር ነዋሪዎች

በነአባዱላ ሰፈር አሉላ ጫካ ላይ ከሚኖሩ እድለኞች መሐል መቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ይገኙበታል ወይ የሚለውን ለማጣራት ባደረኩት ጥረት በጉዳዩ ላይ ገና ዉሳኔ እንዳልተሰጠ ለማወቅ ችያለሁ፡፡

በርሳቸው ጥያቄ ይሁን በአጋጣሚ ባይታወቅም ጋሽ ግርማ ከታላቁ ቤተ መንግሥት እንደወጡ በቀጥታ ያመሩት 22 ማዞርያ አክሱም ሆቴል ጀርባ፣ ታላቁ ጦቢያ ጠጅ ቤት አጠገብ ከሚገኝ ባለሦስት ፎቅ ቤት ነበር፡፡ የቤቱ ባለቤት አቶ ሰለሞን ግርማ ቦሌ ሐያት ሆስፒታል ጀርባ ‹‹ምሳሌ›› የሚባል ዉብና ዘመናዊ ባርና ሬስቶራንት ባለቤት ሲሆኑ ቤታቸውን ከዚህ በተሻለ ዋጋ ማከራየት ይችሉ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ርዕሰ ብሔር ለነበሩ ሰው ማከራየቱ ራሱን የቻለ ክብር ማስገኘቱን ነበር የፈለጉት፡፡ መቶ አለቃ ግርማ ለዚህ ሊፍት ለተገጠመለት ቤት በየወሩ ግማሽ ሚሊየን ብር ሲገፈግፉ የቆዩበት ዘመን ቢደመር ለአምስት መቶ የ10/90 ተመዝጋቢዎች የጋራ መኖርያ ቤት ማሰራት ይችል ነበር፡፡ የሆነው ሆኖ ጋሽ ግርማ በመጨረሻ ከዚህ ዉድ ቤት ለቀው ጦር ኃይሎች ኔዘርላንድስ ኤምባሲ ፊትለፊት ከሚገኝና በዛፎች የተከበበ ሰፊ ግቢ እንዲዛወሩ ተደርገዋል፡፡ ንብረትነቱም የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ነው፡፡ አሁን የካ ኮረብታ ላይ ወደሚገነቡት እልፍኝታዳራሽ ይዛወራሉ ወይስ እዚያው ጦርኃይሎች ይፀናሉ የሚለው ለጊዜው ያልተመለሰ ጥያቄ ነው፡፡

በዚህ የነአባዱላ የነገሥታት ሰፈር እንዲኖሩ ከታጩ ባለሥልጣናት መካከል የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ አዜብ መስፍን፣ የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የመለስ ቀኝ እጅ የነበሩት የብአዴኑ አዲሱ ለገሰ፣ የዲህዴኑ ሌላው የመለስ ቀኝ እጅ የነበሩት ዶክተር ካሡ ኢላላ፣ የሕወሓቱ ቀደምት ታጋይ አባይ ፀሐዬ ይገኙበታል፡፡ አቶ በረከት ስምኦን ወደ አዲሶቹ ቤቶች ለመዛወር ብዙም ፍላጎት እንዳላሳዩ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በየካ ኮረብታ ላይ ለጊዜው እያንዳንዳቸው ከ18-20 ሚሊየን ብር የሚያወጡ ስድስት ቅንጡ ቤቶች ብቻ የተገነቡ ሲሆን ወደፊት ከዚሁ ሰፈር ወደ ምስራቅ አቅጣጫ ለ20 ዓመታት በላይ የሰፈሩ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችን አፈናቅሎ ሌሎች ተመሳሳይ የተራራ እልፍኝታዳራሾችን ለመገንባት እቅድ ተይዟል፡፡ በምስራቅ በኩል የሚገኙት እነዚህ ይዞታዎች ካርታ አልባ በመሆናቸው ነዋሪዎቹን ወደሌላ ቦታ በማዛወር አካባቢውን ሙሉ በሙሉ የባለሥልጣናት መንደር ለማድረግ እንደታቀደ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአካባቢው ለባለሥልጣናቱ ሰፊ ቦታ አስቀድሞ ለመያዝ ታስቦ የነበረ ቢሆንም አዲሳባ መስተዳደር የሊዝ ጽሕፈት ቤት በእቅዱ ዙርያ ቀደም ብሎ መረጃ ሳይደርሰው በመቅረቱ በአካባቢው የሚገኙትን ክፍት ቦታዎች በሊዝ አጫርቷቸዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ የሊዝ አሸናፊዎችን ወደ ሌላ ቦታ ለማዘዋወር የቀረበ ምክረ ሐሳብም ነበር፡፡ ምክረ ሐሳቡ ሳይገፋበት የቀረው ጉዳዩ ሚዲያዎች ጋር ደርሶ በሕዝቡ ዘንድ ብዙ ጫጫታ ይፈጥራል በሚል እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ያብራራሉ፡፡

ራስ አሉላ በቀለ ጫካና አጎራባቾቹ

ይህ በተለምዶ ራስ አሉላ ጫካ የሚባለው ኮረብታ በጀርባ በኩል ጥቅጥቅ ባለ 93ሺ ስኩዌር ካሬ የሚሸፍን ጫካ  ሲሆን ወደ መሪ ሎቄ ሰንጥቆ የሚያልፍ ባለ 40 ሜትር የአስፋልት መንገድ በፍጥነት ተገንብቶ በቅርብ ቀናት ዉስጥ ለትራፊክ ክፍት ይሆናል፡፡ አካባቢው ቅዝቃዜ ያለውና ነፋሻማ ነው፡፡ አሉላ ጫካ ተብሎ የሚጠራው ደን ለዚህ አስዋጽኦ አድርጓል፡፡ አሁን የራስ አሉላ ጫካ ‹‹መለስ ፓርክ›› በሚል የተሰየመ ሲሆን ልዩ ጥበቃ እንዲያገኝ ተደርጎ ሰፋፊ የመዝናኛ ፕሮጀክቶችም በጫካው ዉስጥ ለማካሄድ እቅድ ተይዟል፡፡ ይህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መለስ ፓርክ በሚል የሚተዳደረው ‹‹አሉላ ጫካ›› በወይዘሮ አዜብ መስፍን በቀጥታ የቅርብ ክትትል የሚደረግለት ሲሆን ንብረትነቱም የመለስ ፋውንዴሽ ሆኗል፡፡ ራስ አሉላ ጫካ  በቀድሞ አደረጃጀት ስፋቱ አንድ ቀበሌን የሚያካልል ነው፡፡

የአሉላ ኮረብታ አቻ የማይገኝለት የሞጃዎች መንደር ስለመሆኑ ለመረዳት በአጎራባች ሰፈሮቹ ምን እየተካሄደ እንደሆነ በቅጡ መረዳት ያሻል፡፡ ልዩ ጥበቃ የሚደረግለት ደን በአካባቢው መኖሩ፣ ብቸኛው የአረጋዊያን መጦርያ ማዕከል በቅርብ ርቀት መገኘቱ፣ የከተማውን ግማሽ ማየት የሚያስችል የመሬት አቀማመጥ መታደሉ፣ በአቅራቢያው አራት ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ለግንባታ ቦታ መውሰዳቸው፣ አቶ ተስፋማሪያም ገብረመድኅን የተባሉ ባለሐብት 8700 ካሬ ሜትር ቦታ እዚሁ ኮረብታ ላይ በልዩ ጨረታ በሊዝ ወስደው ሌላ ተጨማሪ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ለመገንባት በዝግጅት ላይ መሆናቸው ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ የአካባቢው ትሩፋቶች ሲሆኑ የአካባቢውን ዋጋ ይበልጥ የሚያንሩ ሌሎች ምክንያቶችም አልጠፉም፡፡

ከመለስ ፓርክ በቅርብ ርቀት የትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዶክተሮች ስብስብ የሚያስገነባው ግዙፍ ቴሪሸሪ ሆስፒታል ታጥሮ ለግንባታ በዝግጅት ላይ ሲሆን በቅርቡ ወደ ግንባታ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 150 ትውልደ ኢትዮጵያን ሐኪሞች በጋራ ሆነው በ30 ሺህ ስኩዌር ካሬ ቦታ ላይ የሚገነቡት ልዩ ሆስፒታል ለምስራቅ አፍሪካ የሜዲካል ቱሪዝም አንድ መዳረሻ እንደሚሆን ተገምቷል፡፡ ይህ በዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም ልዩ ክትትል የሚደረግለት ፕሮጀክት ሲሆን ተጨማሪ 120ሺ ስኩዌር ካሬ የማስፋሪያ ቦታ ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ነው፡፡ የዶክተሮቹ ጥምረት ከኢጋድ ጋር በጥምረት የሚሰራና የአንድ ቢሊየን ብር ፕሮጀክት እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ከዚህ ሆስፒታል ወረድ ብሎ በሚገኘው ‹‹ጊፍት ሪልስቴት›› ነው፡፡ በአካባቢው አንጻር የጊፍት ሪልስቴት ዘመናዊ ቤቶች ከጊዜ በኋላ ለዚህ አካባቢ የሚመጥኑ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ከዚህ ሪልስቴት ጎን አንድ ሌላ የተንጣለለ ሜዳ ይገኛል፡፡ ለጊዜው የአካባቢው ነዋሪዎች የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ሆኖም በዚህ ሜዳ ላይ በምስራቅ አፍሪካ ትልቁን የኤግዚብሽንና የስብሰባ ማዕከል ለመገንባት የአዲስ አበባ መስተዳደርና በአዲሳባ ንግድ ምክር ቤት በጋራ እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡Addis-Africa International Convention and Exhibition Center (AAICEC) ይሰኛል ሙሉ መጠርያው፡፡ የሜዳው ስፋት 110,000 ስኩዌር ካሬ ሲሆን ፕሮጀክቱ በጠቅላላ 2 ቢሊየን ብር ይፈጃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህ ፕሮጀክት የአዲሳባ ትልቁ ሞል (የገበያ ቦታ)፣ ሦስት የመሰብሰብያ አዳራሾች፣ ጅምናዚየሞች፣ ቴያትር ቤቶች፣ ሲኒማ ቤቶች እንዲሁም አንድ ባለ አራት ኮከብ ሆቴልን ያቀፈ ነው፡፡

የባለሥልጣናቱ መኖርያ ታዲያ በነዚህ ግዙፍ የፓርክ፣ የቤት፣ የገበያ፣ የመዝናኛና የመጦርያ ሰፋፊ ፕሮጀክቶች መሐል መገኘቱን ልብ ማለት ያሻል፡፡

የባለሥልጣናቱ እልፍኝ ታዳራሾች ዉስጣዊ ገጽታ

ለባለሥልጣናቱ የሚገነቡት ቤቶች ገና ሳይጠናቀቁ በጊዝያዊ የሽቦ አጥር ታጥረው 12 የጥበቃ አባላት በፈረቃ የሚጠብቋቸው ሲሆን ከጉልበት ሠራተኞችና ከተክለብርሃን አምባዬ (ታኮን) መሐንዲሶች ዉጭ ፀጉረ ልዉጥ ሰው መግባት አይፈቀድለትም፡፡ ሆኖም የዚህ ጽሑፍ ፀሐፊ ከተቋራጩ ሠራተኞች በአንዱ እገዛ ተደርጎለት የቤቶቹን የዉስጥ ገጽታ ለግማሽ ሰዓት ያህል ለመመልከት እድሉን አግኝቷል፡፡ የጉብኝቱ ወቅት ከሁለት ወራት በፊት ሲሆን በዚያን ወቅት የቤቶቹ ዉስጣዊ ልስን ተጠናቆ የሴራሚክ ስራዎች ጅማሮ እየተካሄደ ነበር፡፡

ቤቶቹ በቁጥር 6 ናቸው፡፡ ስድስቱም ቤቶች ተያይዘው ቢሰሩም የየራሳቸው ግቢና የመዋኛ ስፍራ፣ አረንጓዴ ሥፍራ እንዲሁም የአዲሳባን ግማሽ ቁልጭ አድርጎ ማየት የሚያስችል ሰገነት ከፍ ተደርጎ በተናጥል ተገንብቶላቸዋል፡፡  ከመሬት በታች አንድ ፎቅ፣ ከመሬት በላይ ባለ ሁለት ፎቅ ቤቶች ሲሆኑ በአምስት መቶ ካሬ ላይ ያረፉ ናቸው፡፡ የቦታው አቀማመጥ ኮረብታማ በመሆኑ አንድ ሰው በቪላዎቹ ሁለት የተለያዩ በሮች ሲገባ የሚያገኘው ሁለት የተለያዩ ወለሎችን ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ቤቶቹ ከደምበል ዳሌ ነጫጭ ቤቶች በሚጎራበቱበት አቅጣጫ የገባ ሰው የቤቱን ዋናውን ግቢ፣ የመኪና ማቆምያ ሰፊ ጋራዥና አትክልት ቦታ ሲያገኝ በተራራው በኩል የሚገባ ጎብኚ ደግሞ በቀጥታ ወደ ሳሎን የሚወስደውን ሊፍትና ወለል ያገኛል፡፡

የዚህ ጽሑፍ ባለቤት በአካል ተገኝቶ መመልከት እንደቻለው ቤቶች እያንዳንዳቸው ቢያንስ ዘጠኝ መኝታዎች አሏቸው፡፡ ይህንንም መረዳት የቻለው በቤቶቹ ሁለተኛ ፎቅ ላይ ‹‹Bed Room 9›› የሚል ጽሑፍ ተለጥፎ በመመልከቱ ነው፡፡ ከሳሎኑ ወደ ፎቆቹ የሚወስደው ደረጃ ጥምዝና ቅንጡ ወይም (spiral staircase) የሚባለው አይነት ሲሆን ከላይኛው ፎቅ ቁልቁል ወደ ዋናው ሳሎን ለመመልከት የሚያስችል ከፊል ሰገነት አላቸው፡፡ በጉብኝቱ ወቅት ዋናውን ሳሎን ለማግኘት አስቸጋሪ እንደነበር መካድ አይቻልም፡፡ የዚህም ምክንያት አብዛኛዎቹ ክፍሎች ሰፋፊ ስለነበሩና የትኛው ዋና ሳሎን የትኛው ምክትል ዋና ሳሎን፣ የትኛው የእንግዳ መቀበያ ክፍል፣ የትኛው ደግሞ የእንግዳ መኝታ ክፍል እንደሆነ በአንድ እይታ መለየት ፈታኝ ስለነበረ ነው፡፡ በክፍሎቹ መካከል የሚገኘው ኮሪደርም ከተለመደው ሰፋ ያለና በራሱ ሳሎን መሆን የሚችል ነው፡፡ ቤቱን ሙሉ ለሙሉ ጎብኝቶ ለመረዳት የባለሙያ ድጋፍን የሚሻ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

ዋናው መኝታ ወይም (master bedroom) በግምት ከ110 ካሬ የማያንስ ሲሆን በደቡብ በኩል ግድግዳ አልባ ሆኖ በመስታወት ብቻ የተሠራ ነው፡፡ ይህም የአዲሳባን ሁለት አራተኛ ለመመልከት እንዲያስችል ተደርጎ ተገንብቷል፡፡ የዚሁ ክፍል የገላ መታጠቢያ ክፍል የሳውናና ስቲም አገልግሎት የሚሰጡ፣ ጃኩዚ፣ ልብስ መልበሻና፣ በትንሹ ሁለት መቶ ሀምሳ ጫማዎችን መደርደር የሚችል ልዩ የጫማ መደርደሪያ ቁምሳጥን የሚገጠምለት ስፍራ እንደተተወለት ከመሐንዲሱ ገለጻ  ለመረዳት ይቻላል፡፡

የአንድ መጸዳጃ ቤት አማካይ ስፋትም የባለ ሦስት መኝታ ኮንዶምንየም ሳሎንን ያክላል፡፡ ‹‹ለኛ ሽንት ሲሸና ጎረቤት የሚያሰማ ኮንዶሚንየም ይሠሩልናል፣ ለነርሱ ሳሎን የመሠለ ሽንት ቤት ይሠራሉ›› እንድል ያበቃኝም ይኸው ይህንኑ መረዳቴ ነው፡፡ አምስቶ መቶ ካሬ ላይ በተቀመጠው ሕንጻ የሠራተኞችን መጸዳጃ ቤት ጨምሮ 12 ሽንት ቤቶች ይገኛሉ፡፡

###

በአዲሳባ ከመርካቶ ቀጥሎ ዉዱ መሬት- የካ ኮረብታ

ከፀሐይ ሪልስቴት ጀርባ ተራራ እየተማሰ ነው፡፡ ተራራ ተምሶ ቋጥኝ እየወጣ ነው፡፡ ቋጥኝ ወጥቶ ቀይ አፈር ተምሶ ጥልቅ የኮንክሪት ምሶሶ እየተቸከለ ነው፡፡ አካባቢውን በድንገት የጎበኘ በአንድ ጊዜ ቢያንስ ከ50 የማያንሱ ጃክ ሐመሮች፣ ሎደሮች፣ ዶዘሮች፣ ኤክስካቫተሮችና አፈር ጫኝ ሲኖትራኮች በሥራ ላይ ሊያገኝ ይችላል፡፡ እስራኤል በጉልበት የያዘቻቸውን መሬቶች በአንድ ጀንበር ሰፋፊ ግንባታዎች አካሂዳ ለመጨረስ የምትጥረውን ምስል እንድናስብ የሚያስገድደን የዚህ ኮረብታ ግንባታ እንግዳ ሰው ላይ አግራሞትን መፍጠሩ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡

ይህ ስፍራ ለድሀ በፍጹም የተፈቀደ ሥፍራ አይደለም፡፡ ለድሀ ብቻ ሳይሆን ለተራ ሐብታምም የሚሆን ቦታ የለውም፡፡ በቀድሞ ስሙ አሉላ በቀለ ጫካ ይባል እንደነበር የነገሩኝና ከቦታው ተፈናቅለው በዘበኝነት እየሰሩ ያጋኘኋቸው አባት ራስ አሉላ በቀለ የንጉሡ ቀኝ እጅ የነበሩ ሰው እንደነበሩ፣ አሽከሮቻቸውን አሰማርተው አልፎ አልፎ ይኖሩበት የነበረ ሰፈር እንደነበር አጫውተውኛል፡፡ ወታደራዊው መንግሥት ሲመጣ ራስ አሉላ ተታኩሰው ሞቱ፡፡ ጫካውንም ደርግ ተረከበው፡፡ መጀመርያ የጦር ቁሳቁሶች ማከማቻ አድርጎት ቆየ፡፡ ከዚያም የኢትዮጵያ ዱር አራዊትና እንሰሳት ጥበቃ ያስተዳድረው ነበር ይላሉ አካባቢውን፡፡ በኋላም በኩማ ደመቅሳ አስተዳደር ጊዜ ለአንድ የአሜሪካ ዩኒቨርስቲ ቢሰጥም ተግባራዊ ሥራ ሳይሰራ በመቆየቱ ለ‹‹ሰንሻይን ሪልስቴት›› ተላልፎ ቆይቷል፡፡

የሰንሻይኑ አቶ ሳሙኤል ታፈሰ ይህንን ከአንድ ቀበሌ በላይ የሚሆነውን ቦታ አጥረው 10 ሚሊዮን ብር የፈጀ ግዙፍና ዘመናዊ መግቢያ በር አስገንብተው አካባቢውን በሽቦ አጥር አስከብረውት ቢቆዩም በፍጥነት ማልማት አልቻሉም በሚል ቦታው መክኖባቸዋል፡፡ ከቦታው ስፋት የተነሳ ለአጥር ያወጡት 25 ሚሊዮን ብር መና ቀርቶባቸዋል ይላሉ እኚሁ የጥበቃ አባል፡፡

አካባቢው ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ከተደረገ በኋላ ከአራተኛው ዙር ጀምሮ ለአስር ተከታታይ ዙሮች እየተሸነሸነ በሊዝ የቀረበ ሲሆን በካሬ 4ሺ ብር ከመሸጥ ጀምሮ በመጨረሻ በካሬ 28 ሺ ብር ለመሸጥ በቅቷል፡፡ አሁን በዚህ ተራራ ላይ የበሬ ግንባር ቦታ የምታህል ትርፍ ቦታ እንኳ ኖራ ለጨረታ ብትቀርብ የአዲሳባ የመሬት ሊዝ ጨረታ ሪከርድ በተሰበረ ነበር ይላሉ ተንታኞች፡፡ ለዚህም እንደምክንያት የሚያቀርቡት በቅናሽ ዋጋ በሊዝ ገዝተው የገቡ ባለሀብቶች አሁን መሬቱን እየሸጡ ያለበትን ዋጋ በመጥቀስ ነው፡፡

500 መቶ ካሬ ባዶ ቦታ በዚህ ሥፍራ በዛሬ ገበያ 10 ሚሊዮን ብር ያወጣል ይላሉ የአካባቢው ደላሎች፡፡ ዉስጥ ለውስጥ በምስጢር በሚደረጉ ድርድሮች ብዙ መካከለኛ ባለሐብቶች ይዘዋቸው የነበሩ ቦታዎችን በሚያስደንቁ ዋጋዎች ሽጠው ለመውጣት እንደተገደዱ ይነገራል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ቦታው የባለሥልጣናት መንደር መሆኑ ሲታወቅ በአመዛኙ የአንድ ብሔር ተወላጆች በከፍተኛ ዋጋ መሬት በመግዛት፣ አንዳንዴም ሻጩ ባቀረበው ማንኛውም ዋጋ ለመክፈል ፍቃደኛ በመሆን ሰፊ የደላላ መረብ በመዘርጋት መንቀሳቀስ መጀመራቸው ነው፡፡ በአካባቢው ቦታ ይዘው ሽጠው ለመውጣት ፍቃደኛ ለሆኑ ሁለት ባለይዞታዎች ለፍቃዳቸው ብቻ 2 ሚሊየን ብር በጉርሻ መልክ እንደተሰጣቸው የዚህ ጦማር ፀሐፊ ማረጋገጥ ችሏል፡፡

“ጃክሮስ የቤት ባለቤት የሆኑ ብዙዎቹ ባለሐብቶች ቤቶቻቸውን እየሸጡ ወደዚህ ተራራ ተዛውረዋል” ይላል ስሙ እንዲጠቀስ የማይፈልግ ሌላ የመሬት ደላላ፡፡ አንዳንድ ባለሐብቶች ቤትለቤት እየሄዳችሁ የማሳመን ሥራ ሥሩ ብለው ያዙናል፡፡ ለዚህም በወር እስከ 5ሺ ብር ይሰጡናል፡፡ እኔ አዲሳባ ዉስጥ 15 ዓመት ሙሉ ቤትና መሬት አሻሽጫለሁ፡፡ እንደዚህ ሰፈር ያበደ ቦታ ግን አላየሁም” ይላል በአካባቢው ያገኘሁት እሳት የላሰ ደላላ፡፡

በዚሁ አካባቢ በ5ኛው ዙር በ7ሺህ ብር የሊዝ ዋጋ ቦታ የያዘ ወጣት ባለሐብት ‹‹በሳምንት ቢያንስ አንድ ደላላ ስልኬ ላይ ይደውላል›› ሲል የሰውን ጉጉት ይገልጻል፡፡ ‹‹ስልኬን ከየት እንደሚያገኙት አላውቅም፣ የሁሉም ጥያቄ ግን ቦታውን በፈለከው ዋጋ እንሽጥልህ የሚል ነው›› ሲል ይናገራል፡፡ ይህ ወጣት ባለሐብት በዚህ አካባቢ አብዛኛዎቹ ይዞታዎች ለምን በአንድ ብሔር ተወላጆች እንደተያዙ ግልጽ ባይሆንለትም በጉዳዩ ላይ ብዙ መናገር እንደማይፈልግ ይገልጻል፡፡ ‹‹ከአንድ ብሔር መሆናቸው እኮ አጋጣሚምም ሊሆን ይችላል›› ሲል ትህትና የተጫነው ምላሽ ይሰጣል፡፡

የየካ ኮረብታን ልዩ የሚያደርጉ 10 ነጥቦች

  1. የሥራ ዘመናቸው ያጠናቀቁ ባለሥልጣናት መንደር፣ የትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሆስፒታል፣ የአረጋዊያን ማዕከል ግንባታ እየተካሄደ መሆኑ፡፡
  2. ኮረብታውን ሰንጥቆ የሚያልፍና ከሲኤምሲ-ወደ መሪ ሎቄ የሚሻገር ባለ አርባ ሜትር አስፋልት መንገድ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ፡፡
  3. 93ሺ ካሬ ጥብቅ ደን በመለስ ፓርክ ስም በቅርብ ርቀት መገኘቱና አካባቢው ነፋሻማ እንዲሆን ማስቻሉ፡፡
  4. አምስት የተለያዩ ባለአምስት ኮከብ ሆቴሎች ግንባታ የሚካሄድ መሆኑ፡፡
  5. በቁጥር 17 ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች እያንዳንዳቸው ባለ 12+1 በፀሐይ ሪልስቴት በግንባታ ላይ መሆናቸው፡፡
  6. የአዲስ አፍሪካ ትልቁ የመሰብሰቢያና የኤግዚብሽን ሴንተር በዚሁ አካባቢ የሚገነባ መሆኑ፡፡
  7. በአዲሰ አበባ ትልልቆቹ የገበያ ማዕከላት፣ ቴአትር ቤቶችና መዝናኛ ማዕከላት በቅርብ ርቀት በግንባታ ላይ መሆናቸው፡፡
  8. ግምታቸው ከ10 ሚሊዮን ብር በታች የሆነ አንድም ቤት በአካባቢው አለመኖሩ፡፡
  9. የአዲስ አበባን ግማሽ ማየት የሚያስችል ኮረብታ መሆኑ፡፡
  10. ከቦሌ አለማቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ የሚያኮበኩቡና የሚያርፉ አውሮፕላኖችን ሙሉ በሙሉ ማስቻሉ ናቸው፡፡