ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ የነበራቸው ሰብእና እና የተለየ ባሕርይ ለእውነተኛ ታሪክም ለልቦለድም የተለመደ ገጸባሕርይ ሲያደርጋቸው ይስተዋላል። ከኢትዮጵያ ነገስታትም መካከል እንደርሳቸው የልቦለድ ታሪክ፣ የቲያትርና የስነ ግጥም ንሸጣ ምክንያት የኾነም የለም ሲባል ይሰማል።
በአውሮፓ ምድር በቅርቡ ስማቸው እንዲነሳ ሲያደርግ የነበረ ሌላ የታሪካቸው አንድ ገጽታ ተፈጥሮም ነበር።በእንግሊዝ የሲኒማና የቲያትር ጥበብ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው አንድ የጥበብ ሰው የቴዎድሮስ ትውልድ አለኝ ማለቱን ተከትሎ የ ማ ቢወልድ ማ ምርምር አስነስቶ ነበር።
(መዝገቡ ሀይሉ ዝርዝሩን ያሰማችኋል አድምጡት)
ይህ የስነጥበብ ሰው እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1997 ዓም ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ሰር ፒተር ዩስቲኖቭ ነበር። ፒተር ዩስቲኖቭ ትልቁ የእንግሊዝ ማዕርግ ተሰጥቶት ሰር ከመሰኘቱም ሌላ 2 የአካዳሚ አዋርድ፣ 2 የኤሚ አዋርድ፣ 2 ጎልደን ግሎብ ሽልማቶችን ጨምሮ በሕይወቱ ዘመን ባስመዘገበው ትልቅ የስነጥበብ ስራው ትልቅ ክብር የተሰጠው ሰው ነበር።
ፒተር ዩስቲኖቭ ስለቤተሰቡ ታሪክ ሲናገር ከብዙ የአውሮፓ አገራትና ከአፍሪካ ደግሞ ከኢትዮጵያ የተቀየጠ የቤተሰብ ታሪክ ያለው ሰው ነበር። በእንግሊዟ ለንደን ከተማ ቢወለድም የቤተሰቡ ጥንተ ታሪክ ከሩስያዊ፣ ከፖላንዳዊ አይሁድ፣ ከጀርመናዊ፣ ከፈረንሳዊ፣ ከኢጣልያዊና ኢትዮጵያዊ ዘር የሚመዘዝ ረጅም ታሪክ ያለው ነው። ያም ኾኖ ከኢትዮጵያ ወገን ያለው ዝምድና በታሪኩ በደምብ አለመመዝገብ ምክንያት ግልጽ ሊኾንለት እንዳልቻለ ሲናገር ቆይቷል። ትንሽ ዘግየት ብሎ ግን ከ አንድ ሬዲዮ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን መጥተው በጋፋት የመድፍ ስራ ሲሰሩ ከነበሩት ፈረንጆች መካከል አንዱ የኾኑትና የአፄ ቴዎድሮስን ልጅ ያገቡት ሳልሙለር ቅድመ አያቱ እንደነበሩና ይህም የአፄ ቴዎድሮስ ዘር እንደሚያደርገው ተናግሮ ነበር።
ይህ የዩስቲኖቭ ንግግር ምንም እንኳን ርግጠኝነት ባይኖርበትም ያንን የአፄ ቴዎድሮስን ዘመን አንድ ሌላ ገጽታ ዳግመኛ እንዲመረመር አድርጓል። በርግጥም በሌሎቹ ነገስታትም ዘንድ የተለመደ የነበረውን በጋብቻ በመተሳሰር ወዳጅነት የማጥበቅ ወግ አፄ ቴዎድሮስ ከፈረንጆቹ ጋር ለመፈጸም መሞከራቸው በታሪካቸው የተቀመጠ ጉዳይ ነበረ። አፄ ቴዎድሮስ ለፈረንጆቹ የሚድሩላቸው የራሳቸው ሴት ልጆች ባይኖሯቸውም እንደራሳቸው ልጆች የሚያይዋቸውን የወንድማቸውን የክንፉ ኃይሉን የልጅ ልጆች ሲያጋቡ ነበር። ጋብቻው በአፄ ቴዎድሮስ ቀጥተኛ ዘመዶችና በፈረንጆቹ መካከል ብቻም አልነበረም። ሌሎች ባለስልጣኖችም ይህን የመሰለ ጋብቻ ሲያደርጉ ነበረ። ጸጋዬ ገብረመድኅን እጅህን ስጥ አለኝ ፈረንጅ እያስባለ በቴያትሩ የሚያስፎክራቸው አፄ ቴዎድሮስ ልጃቸውን ለመስጠት ስሱ አልነበሩም።
አገራቸውን በቴክኖሎጂ ለማሳደግ ከፈረንጆቹ መወዳጀት እንዳለባቸው የገባቸው ቴዎድሮስ አስገድደው መድፍ ያሳነጧቸውን ፈረንጆች እዚያው ለማስቀረት በመጀመሪያ ሙከራ ያደረጉት በጋብቻ መዛመድን ነበር። ያም አልኾን ብሎ ሲያስቸግሯቸው ፈረንጆቹ ራሳችው ከሰሩት መድፍ ጋር በግር ብረት አዋደው በእስር እንዲማቅቁ አደረጉ። ይህም ኋላ ከእንግሊዝ መንግስት ጋር ለመጋጨትና የመቅደላውን ጦርነት ለመቀስቀስ ምክንያት ኾነ