በዓለም ላይ የአረጋዊያን ጉዳይ ቁልፍ የልማት አጀንዳ መሆኑ ከታመነበት ቆይቷል፡፡ የማንኛውም ማህበረሰብ ጤናማነት የሚለካው ለአረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች በሚሰጠው እንክብካቤ እንደሆነ ቢታመንበትም ብዙ የሚነገርለት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ግን ለአረጋዊያን ኑሮ ዋስትና እምብዛም ያስገኘው ትሩፋት የለም፡፡
አረጋዊያን አሁንም በከባድ ኑሮ ውድነት ኑሯቸውን በከፋ ድህንትና ጉስቁልና የሚገፉ ሲሆን አብዛኛዎቹ ከድሀነት ወለል በታች እንደሆኑ በርካታ ጥናች ይጠቁማሉ፡፡ ለዚህ አንዱ ምክንያት ኢትዮጵያ ሁሉን ዓቀፍ የጡረታና ማህበራዊ ዋስትና ፖሊሲ የሌላት ሀገር ስለሆነች እንደሆነ ግልፅ ነው::
( ቻላቸው ታደስ በድምፅ ያዘጋጀውን ዘገባ ያድምጡት)
መንግስት ላለፉት ሦስት ዓመታት ብሄራዊ የማህበራዊ ዋስትና ረቂቅ ፖሊሲ በማዘጋጀት ተጠምዶ ቆይቷል፡፡ ሁሉን ዓቀፍ እንደሆነ የሚነገርለት አዲሱ የማህበራዊ ዋስትና ረቂቅ ፖሊሲ ለችግር ተጋላጭ በሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ብቻ አተኩረው የነበሩትን የማህበራዊ ዋስትና መርሃ ግብሮች በማስፋት ዜጎች ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች የሚኖራቸውን ተጋላጭነት ቀድሞ መከላከል ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ ሆኖም ፖሊሲው ገና ሳይፀድቅ ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ተጀምሯል፡፡ ሁሉን ዓቀፍ ማህበራዊ ዋስትናን ማረጋገጥ ደግሞ የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አንዱ ኣላማ ነው፡፡
በዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት ዕድሜቸው ከስልሳ በላይ የሆኑ ሰዎች እንደ አረጋዊያን የሚቆጠሩ ሲሆን ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገሮች ብቻ የአረጋዊያን ብዛት በ2005 ዓ.ም ከነበረበት ሰላሳ ሰባት (37) ሚሊዮን በ2050 ዓ.ም መቶ ሃምሳ አምስት (155) ሚሊዮን እንደሚደርስ የህዝብ ዕድገት ትንበያዎች ያሳያሉ፡፡
ባለፉት ዓመታት የአረጋዊያን ቁጥር ከጠቅላላው ህዝብ ብዛት አንፃር ሲታይ የተጠበቀውን ያህል ጭማሪ እንዳላሳየ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ቢገልፅም ትንበያው እንደሚያሳየው ግን ከጠቅላላው ዘጠና ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ አራት ሚሊዮኑ ከስልሳ ዓመት በላይ የሆናቸው አረጋዊያን እንደሆኑ ይገመታል፡፡ ይህም የጠቅላላው ህዝብ አራት በመቶ መሆኑ ነው፡፡
ሆኖም ከአረጋዊያን መካከል በመንግስት ጡረታ የታቀፉት አምስት መቶ ሺህ ያህሉ ብቻ ናቸው፡፡ እንደገና ከእነዚህም ውስጥ ከሰባ አምስት በመቶ በላይ የሚሆኑት የሚያገኙት ወርሃዊ የጡረታ ክፍያ ከሶስት መቶ እስከ አራት መቶ ብር ብቻ ነው፡፡ ይህ ክፍያ እንኳን ከባዱ የኑሮ ውድነት ታክሎበት እንዲያውም እዚህ ግባ የማይባል ስለሆነ በጡረታ ሽፋኑ የታቀፉት አረጋዊያንም ከኑሮ ዋስትና ችግሮች ተጋላጭነት እንዳላመለጡ ያሳያናል፡፡
የማዕከላዊ ስትስቲክስ ኤጀንሲ እንደሚለው በቁጥር ላቅ ያሉት የሀገሪቱ አረጋዊያን ሴቶች ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ አረጋዊያን የሚገኙትም በገጠር መሆኑ ለማህበራዊ አገልግሎቶች ያላቸውን ተደራሽነት ውስን ስላደረገው ለችግር ያላቸውን ተጋላጭነት አባብሶታል ይላሉ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲም ሆኑ የኸልፕ ኤጅ ኢንተርናሽናል ሪፖርቶች፡፡
በአረጋዊያን ላይ የሚሰሩት ግብረ ሰናይ ድርጅቶቹ ኸልፕ ኤጅ ኢንተርናሽናል እና ኮርድኤድ ያጠኑት አንድ ጥናት እንደሚለው መሬትን ጨምሮ የንብረት ባለቤትነት መብትና ቋሚ የገቢ ምንጭ የሌላቸው ሴት አረጋዊያን በበለጠ ለኑሮ ዋስትና ችግሮች ተጋላጭ ናቸው፡፡ በመሆኑም በአዲስ አበባ ብቻ እንኳ በርካታ አረጋዊያን ሴቶች ከእጅ ወደ አፍ ለሆነ ገቢ ማገዶ እንጨት በመልቀም፣ ጉልት በመነገድና የዕለት ጉልበት ስራዎችን በመስራት ላይ እንደተሰማሩ በማህበራዊ ጥናት መድረክ (Forum for Social Studies) እና በኸልፕ ኤጅ ኢንተርናሽናል የተደረጉ ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡
ከፌደራሉ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኤጀንሲ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በመላ አዲስ አበባ ለአረጋዊያን መጠለያ የሚሰጡ ተቋማት ሶስት ብቻ ናቸው፡፡ በአንፃራዊነት በትልቅነቱ የሚታወቀውም ሀገር በቀሉ ግብረ ሰና ድርጅት “መቄዶኒያ የአረጋዊያንና አዕምሮ ህሙማን ማዕከል” ሲሆን እሱም ያቀፋቸው አረጋዊያን የተወሰኑ ናቸው፡፡ በከተማዋ በመንግስት ይዞታ ስር የሚገኝ አንድ አነስተኛ የአረጋዊያን መጠለያ ብቻ ነው ያለው፡፡ በዚህም ሳቢያ በከተማዋ የሚገኙ በርካታ አረጋዊያን ለልመና መዳረጋቸውን በኸልፕ ኤጅ እና ኮርዴድ የተደረጉ ጥናቶች ይገልፃሉ፡፡
የሀገራችን አረጋዊያንን ችግር ያባባሰው አንዱ ምክንያት ድርብ ጫና መሸከማቸው ነው፡፡ በአንድ በኩል በጡረታ ዘመናቸውም እንኳ ጧሪ ደጋፊ ስለሌላቸው ራሳቸውን ለመመገብ መስራት ወይም መለመን ይጠበቅባቸዋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ የአንድ ለአቅመ-ስራ ያልደረሱ ልጆቻቸውን፣ የልጅ ልጆቻቸውን ወይም ታማሚ ቤተሰቦቻቸውን የመንከባከብ ሃላፊነት አለባቸው፡፡ በተለይ ኤችአይቪ ኤድስ ከተስፋፋ ጀምሮ ወላጅ አልባ ህፃናትን የመንከባከብ ሃላፊነት በአብዛኛው በአረጋዊያን ትክሻ ላይ መውደቁን ድርጅቱ ይገልፃል፡፡ ይህን የኸልፕ ኤጅ ድምዳሜም መንግስት ይጋረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህገመንግስት በአንቀፅ 90 (1) የሀገሪቱ አቅም በሚፈቅደው መጠን ሁሉም ዜጎች ማህበራዊ ዋስትና የማግኘት መብት እንዳላቸው ደንግጓል፡፡ ሆኖም መንግስት በመዋጮ ላይ ከተመሰረተው ጡረታ ውጭ እንኳን ለሁሉም ዜጎች ለአረጋዊያንና ለህፃናትም ማህበራዊ ዋስትና ሽፋን ማቅረብ አልቻለም፡፡
መንግስት የተለያዩ መለስተኛ ማህበራዊ ዋስትናና ማህበራዊ ጥበቃ ለመስጠት የሚያግዙ ፖሊሲዎችና ህጋዊ ማዕቀፎች ነድፎ ስራ ላይ ቢያውልም አጥጋቢ ውጤት እንዳልተገኘ ከመንግስት የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ለአብነትም ምንም እንኳ በጤና ረገድ ድሆች ለተወሰኑ የህመም ዓይነቶች ነፃ ህክምና የሚያገኙበት አሰራር ቢኖርም ለአረጋዊያን ብቻ በተናጥል የተቀረፁ የጤና መርሃ ግብሮች ግን የሉም፡፡ ነፃ ህክምናውም ቢሆን ድሃ ታማሚ አረጋዊያን ቋሚ ገቢ ሳይኖራቸው የሚታዘዙላቸውን መድሃኒቶች በአብዛኛው በግል መድሃኒት ቤቶች ለመግዛት ስለሚገደዱ የነፃ ጤና አገልግሎቱ ሙሉ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል፡፡
በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር ተዘጋጅቶ ለሚንስትሮች ምክር ቤት በቀረበው አዲሱ ረቂቅ ፖሊሲ መግቢያ ላይ እንደተጠቀሰው እስካሁን በስራ ላይ ያሉት የጡረታና ማህበራዊ ዋስትና ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችም ቅንጅት የሚጎላቸው፣ ተቋማዊ ያልሆኑ፣ ሽፋናቸው አነስተኛ፣ ተጠያቂነት ማስፈን ያልቻሉ እና ተጋላጭነትን በመከላለከልና አቅምን በማሳደግ ላይ ያላተኮሩ ናቸው፡፡
ከፖሊሲ ክፍተት ባሻገርም በሀገሪቱ ካለው በአረጋዊያን ላይ ከተጋረጠው ተጋላጭነት አንፃር አረጋዊያንን የሚንከባከቡ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሉም ማለት ይቻላል፡፡ ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር ውጭ በአረጋዊያን ላይ የሚሰሩ ስራዎችን ብቻ የሚያስተባብር ራሱን የቻለ መንግስታዊ ተቋምም የለም፡፡ “ኸልፕ ኤጅ ኢንተርናሽናል”ም በአረጋዊያን ላይ የሚሰራ ብቸኛው ዓለም ዓቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት