Poverty

የድህነትን መጠን ወጥ በሆነ መስፈሪያ ለመለካት ሥራ ላይ የዋለው የድህነት ወለል ልክ ከአንድ ዶላር ከ 25 ሣንቲም ወደ አንድ ዶላር ከ90 ሣንቲም ሊያሳድግ እንደሆነ የዓለም ባንክ አስታወቀ።

ቀድሞውን ይህንኑ የ አንድ ዶላር ከ 25 ወለል እንደጠቋሚ በመጠቀም ሕዝባቸውን ከዚህ ወለል በላይ ለማድረግ ሲታገሉ ለነበሩ አገሮች ይህ አዲሱ የድህነት ወለል ከፍ ብሎ የተሰቀለ ፈተና ይሆንባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

(ለዝርዝሩ የመዝገቡ ሀይሉን ዘገባ እዚህ ያድምጡ)

ከዚህ በፊት በነበረው የ አንድ ዶላር ከ 25 ሣንቲም መለኪያ ከድህነት ወለል በላይ እንደነበሩ ይታሰቡ የነበሩ በ10 ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ድሆችን መልሶ ከድህነት ወለል በታች በማስገባት ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ የሰዎች ቁጥርን እንዲያሻቅብ እንደሚያደርገውም ይጠበቃል። ከሰሐራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ያለው ይህ የድህነት መጠን ወለል ከዚህ ማሻሻያ በኋላ ብዙም ለውጥ ባያመጣም ከፍተኛ ድህነት ቅነሳ ባስመዘገቡ የእስያ ሀገራት ውስጥ ግን የድህነት መጠኑ በእጥፍ እንደሚጨምር ይጠበቃል።
የዓለም ባንክ ከኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ያገኘውን መረጃ በመመርኮዝ በሚያወጣቸው ሪፖርቶች፤ የድህነት ቅነሳው ጥሩ ውጤት እያስመዘገበ እንደሚገኝ ይጠቁማል። ይህንኑ የ አንድ ዶላር ከ 25 ሳንቲም ወለል ልኬት መሠረት በማድረግም እ አ አ. በ 1995 ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ 37% የሚኾነው ብቻ ከድህነት ወለል በላይ እንደነበረ እና እ አ አ. በ 2011 ግን ይህ መጠን ከፍ ብሎ 63% የሚኾነው ሕዝብ ከወለሉ በላይ እንደሆነ አሳውቆ ነበር።

የዓለም ባንክ መረጃውን ያገኘበት የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ቁጥሮች ለብዙዎቸ አጠራጣሪ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን የመሳሰሉ አሐዞችን ለፖለቲካ ፍጆታ እንደሚጠቀምባቸው በተደጋጋሚ የሚነገር ሲኾን፤ ይህንንም ይሁን ሌሎች ከመንግሥት አካል የሚወጡ ኢኮኖሚ ተኮር መረጃዎች ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ይሁን ላለመቀበል የሚያስችል ገለልተኛ ምርመራ ለማድረግም የወቅቱ የአገሪቱ ኹኔታ አይፈቅድም።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ 2011 የ አንድ ዶላር ከ 25ቱ የድህነት መለያ ወለል ወይም መስመር በብር የመግዛት አቅም ሲመነዘር አቻ የሚሆነው ምንዛሬ 5 ብር ገደማ ነበር። ይህ መለኪያ ከድህነቱ ወለል በላይ ያደረጋቸው 63% የሚኾኑ ኢትዮጵያውያን ድኆች አብዛኞቹ በአዲሱ መለኪያ መሠረት በቀን አንድ ሰው ሊኖረው የሚገባው የገቢ መጠን ወደ 16 ብር በመጠጋቱ ምክንያት ብዙዎች ተስበው ከወለሉ በታች መሆናቸው አይቀርም።
በዓለም ባንክ ባለሙያዎች ገለጻ መሠረት እስከ ዛሬ ድረስ ይደረጉ ከነበሩ ጥናቶቸ በተለይ የተሟላ መረጃ በማግኘቱ የተሻለ ክለሳ ማድረጋቸውን ይናገራሉ። በዘመኑ ባለው የመረጃ ቅልጥፍና እና ጥራት ምክንያት ከዚህ በፊት ከነበሩት ጥናቶች በተለየ የገንዘብን የመግዛት አቅም ለማጥናት በተደረገው የመረጃ ማሰባሰብ ሥራ የተሻለ መረጃ እንዳገኙም ይናገራሉ።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የዓለም ባንክ በሚቀጥሉት 15 ዓመታት ውስጥ የዓለም አገራት ድህነትን በማጥፋት በኩል ሊያሳኩ የሚገቧቸውን የእድገት ግቦች አጽድቋል። ከእነዚህም ግቦች ውስጥ ዋነኛው ግብ ድህነትን እ አ አ. በ2030 ከዓለም የማጥፋት እቅድ ነው።