ቱርክ በተለምዶ ከሚታወቀው በተለየ በአፍሪካ ውስጥ ሰብኣዊ ዕርዳታን፣ ንግድን፣ ባህልን፣ ኢንቨስትመንትንና የልማት ዕርዳታን ያቀናጀ ፖሊሲ በመተግበር ላይ ነች፡፡ የቱርክ ኢንቨስትመንትና ብድር አሰራር ከቻይና ተመራጭ እንደሆነ ታዛቢዎች ያስረዳሉ፡፡
ቱርክ ከአፍሪካ ጋር የቆየ ግንኙነት ቢኖራትም በተለይ ገዥው ጀስቲስ ኤንድ ዴቬሎፕመንት ፓርቲ እኤአ በ2002 ስልጣን ከያዘ ወዲህ ልዩ ትኩረት መስጠት ጀምራለች፡፡ ለአፍሪካ ልዩ መርሃ-ግብር ቀርፃ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረችውም እኤአ ከ1998 ጀምሮ ነው፡፡ እኤአ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮም የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ፣ ፕሬዝዳንቱ፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዲሆም የግዙፍ ኩባንያ ባለቤቶች በተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች ተደጋጋሚ ጉብኝቶችን አድርገዋል፡፡ በያዝነው ሳምንት መጀመሪያም ፕሬዝዳንት ረጅብ ተይፕ ኤርዶዋን ለስራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነበር፡፡
አውሮፓን፣ እስያንና መካከለኛው ምስራቅን የምታገናኘው ቱርክ ስትራቴጂክ አቀማመጧ አሁን ለምትከተለው የውጭ ፖሊሲዋ መሰረት ነው፡፡፡
አምባሳደር ዴቪድ ሺን ለቻታም ሃውስ ባጠኑት አንድ ጥናት ቱርክ በአፍሪካ የምትተገብረው ፖሊሲ መነሻው የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በመገንዘቧ፣ ከመካከለኛው ምስራቅና ከአውሮፓ ህብረት ጋር የነበራት የንግድ ግንኙነት በመቀዛቀዙ እና በአፍሪካዊያን ሙስሊሞች ላይ ተፅዕኖ ለማድረግ በመፈለጓ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
(የቻላቸው ታደሰ የድምፅ ዘገባን እዚህ ያድምጡ)
ቱርክ ከአፍሪካ ጋር በንግድና ልማታዊ እርዳታ ያላት ትስስር እየዳበረ መጥቷል፡፡ እኤአ በ2000 ዓ.ም ሰባት መቶ አርባ ሁለት ሚሊዮን ዶላር የነበረው የንገድ መጠን በ2013 ወደ ሃያ ቢሊዮን ዶላር አድጓል፡፡ በያዝነው ዓመት ከአፍሪካ ጋር ያላትን የንግድ መጠን ወደ 50 ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ አቅዳለች፡፡
ቱርክ በአፍሪካ ያላት ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትም በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ይገኛል፡፡ እስከ እኤአ 2014 ድርስ እንኳ በኢትዮጵያ ብቻ ከአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስትመነት እንደነበራት ተመራማሪው አምባሳደር ዴቪድ ሺን ይገልፃሉ፡፡ ይህም ቻይና በኢትዮጵያ ካላት ኢንቨስትመንት በመጠኑ እንደሚበልጥ ያሳያል፡፡
ቱርክ ለሱማሊያ ብቻ እንኳ የምትሰጠው ሰብዓዊና የልማት ዕርዳታ ተወዳዳሪ የለውም፡፡ ከሌሎች እርዳታ ሰጭዎች በተለየ ቱርካዊያን እርዳታ ሰጭዎች ተቀማጭነታቸውን በሞቃዲሾ በማድጋቸው የምዕራባዊያንን አጀንዳ በሚጠራጠሩት ሱማሊያዊያን ዘንድ አመኔታና ዝና አትርፎላቸዋል፡፡
መቼም ከቱርክ የውጭ ፖሊሲ ጀርባ ሙስሊም ወንድማማችነትን የማጠናከር ፍላጎት እንዳለ መገንዘብ አይከብድም፡፡ ለሱማሊያ የሰጠችው ትኩረትም በከፊል ይህንን እንደሚያሳይ በርካታ ታዛቢዎች ያስረዳሉ፡፡
አፍሪካ አዲሲቷ የኢንቨስትመንትና ንግድ ማዕከል እየሆነች በመምጣቷ ቱርክ በአፍሪካ ዘላቂ አካባቢያዊና ዓለማቀፋዊ አጀንዳ እንዳላት ግልፅ ሆኗል፡፡ ሆኖም አመጣጧ የአፍሪካን ሃብት ለመመዝበር ይሁን አይሁን ለማወቅ ትንሽ ጊዜ መጠበቅ ያሻል፡፡