የአራት ፓርቲዎች ስብስብ የሆነው ኢህአዴግ የብሔር ውክልናን ያለቀቀ አንድ ፓርቲ ለመሆን ተሳነው በህወሀትና በሌሎቹ ፓርቲዎች መካከል የጌታና ሎሌ ግንኙነት ከመኖሩ ባሻገር ፓርቲው ውስጣዊ ሽኩቻና ውጥረት በዚሁ ከቀጠለ አደጋው የከፋ ስለመሆኑ የሚናገሩ አሉ። ቻላቸው ታደሰ የፓርቲውን ውስጣዊ ፈተና ተመልክቶታል። ያዘጋጀውን ትንታኔ እነሆ አድምጡ
በ2000 ዓ.ም የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ “ውህደት” (union) ማለት “ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ በህግ መሠረት ተመዝግበው የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድ ላይ ተዋህደው አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ የሚመሰርቱበት ሁኔታ ነው” በማለት ይገልፀዋል። ስለሆነም ስለ ኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውህደት ስናነሳ ድርጅቶቹ ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ አፍርሰው፣ አርማዎቻውንና ማህተሞቻቸውን ለምርጫ ቦርድ አስረክበው አባሎቻቸውን በቀጥታ የአዲሱ ህብረ-ብሄራዊ ፓርቲ አባል ያደርጋሉ ማለታችን ነው፡፡
እንደሚታወቀው ኢህአዴግን ወደ ውህድ ህብረ-ብሄራዊ ፓርቲ ለመቀየር እንቅስቃሴ የተጀመረው በህወሃት ክፍፍል ማግስት ነበር፡፡ ስለ ሂደቱ መጀመርም በወቅቱ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ጋዜጣ ላይ ሰፍሮ አንብበናል፡፡ ስለሆነም ኢህአዴግ የጠላቱን የኢሠፓን አወቃቀር ለመኮረጅ በአማካሪነት የኢሠፓውን የርዕዮተ-ዓለምና ድርጅታዊ መዋቅር ቁንጮ የነበሩትን አቶ ሽመልስ ማዘንጊያን ከእስር ፈትቶ በኮንትራት ማሰራት ጀምሮ እንደነበር በወቅቱ በጦማሮች መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ሙሉ በሙሉ እውነተኛ እንደሆነ ማረጋገጥ ባይቻልም፡፡
በእርግጥ በአቶ መለስ ዜናዊ ይመራ የነበረው የህወሃት ማዕከላዊ አመራር በዚያ ወቅት የግንባሩን ውህደት የፈለገው በህወሃት ክፍፍል ሳቢያ በትግራይ የነበረው ማህበራዊ መሰረቱ እንዳሳሳበት በማሰብ ወደ ሌሎች ክልሎች ለማስፋት አስቦ ስለነበር ነው የሚለው አንደኛው መላ ምት ነው፡፡ መቼም አቶ መለስ ራሳቸው በክፍፍሉ ወቅት በሁለት እግራቸው የቆሙት በኦህዴድና ብአዴን ድጋፍ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ስልጣናቸውን ሲያረጋጉ ግን የውህደቱን አጀንዳ መልሰው በጠረጴዛቸው መሳቢያ ውስጥ ወሸቁት፡፡ ሌላኛው መላ ምት ደግሞ ስራው እምብዛም ሳይገፋበት የ1997ቱ ምርጫ ከተፍ በማለቱ ተዳፍኖ ቀረ የሚለው ነው፡፡
ያም ሆኖ የውህደት አጀንዳው እንደገና በሌሎች አጋጣሚዎች በአለፍ ገደም መነሳቱ አልቀረም፡፡ የቀድሞው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚንስትር ደዔታ ኤርሚያስ ለገሰ “ባለቤት አልባ ከተማ” በተሰኘው መፅሃፉ እንደሚገልፀው ከምርጫው በኃላም በሌላ የኢህአዴግ መድረክ ላይ በአቶ ተፈራ ዋልዋ አማካኝነት በመጠኑ ተቀንቅኗል፡፡ የድርጅቱ መሪዎች ጉዳዩ መሰረታዊ አለመሆኑን በመናገር አዳፍነውት እንዳላፉም ያስታውሳል፡፡
ለሦስተኛ ጊዜ እንደገና የተነሳው ከአቶ መለስ ህልፈት በኃላ የዛሬ ሁለት ዓመት ባህር ዳር ላይ በተካሄደው ጉባዔ ላይ የህወሃት መስራችና ከፍተኛ አመራር የነበሩ ሰው በድንገት “ድርጅታችን የሚዋሃደው መቼ ነው?” የሚል ጥያቄ መሰንዘራቸው ተዘግቦ ነበር፡፡ መቼም በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት አሰራር ቀደም ብሎ ያልተያዘና የበላይ አመራሩ ያለወሰነበት አጀንዳ በተለይም የድርጅቱ የጡት አባት አቶ መለስ በሌሉበት በድንገት መነሳቱ ለጉባዔተኞቹ ፈረንጆች “ቦምብ ሼል” (bomb shell) የሚሉት ዓይነት እንደሆነባቸው አያጠራጥርም፡፡ ስለሆነም የመድረኩ መሪዎች እንደ ድሮው ሁሉ “ይህን ጉዳይ በይደር እናቆየው” በማለት ለማዳፈን ተገደዱ፡፡ በይደር ይቆይ የተባለው ጉዳይ ግን እነሆ በሰሞኑ የኢህአዴግ ጉባዔም ሳይነሳ ቀርቷል፡፡
ኢህአዴግ ጠንከር ያለ ግፊት በሚመጣበት ጊዜ በአብዛኛው “ፕራግማቲስት” (pragmatist) ድርጅት መሆኑን በተግባር ቢያሳይም ”የመዋሃድ ወይም አለመዋሃድ”ን ጉዳይ ግን በእጅጉ ከሚፈራቸው አንኳር አጀንዳዎች መካከል ቀዳሚው ሆኗል፡፡
ለመሆኑ ውህደት ለኢህአዴግ ስትራቴጂ ነው? ወይንስ የመጨረሻ ግብ? ብለን ብንጠይቅም የምናገኘው ምላሽ የተዘበራረቀ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡ አንዳንዶች አመራሮች እንደ መጨረሻ ግብ ያዩት ይሆናል፡፡ ሌሎች ደግሞ እንደ ስትራቴጂ፡፡ በግንባሩ መተዳደሪያ ደንብ ላይ ስለ ውህደት ምንም አለመጠቀሱ ግን እንደ መጨረሻ ግብ አለመያዙን ሊያመለክት ይችላል፡፡
እንደ ፕሮፌሰር ክሪስቶፈር ክላፋም፣ ሳራ ቮግ እና ኬጅትል ቶርኖቮል የመሳሰሉ ምሁራን በተደጋጋሚ እንደሚገልፁት ብሄር-ዘለል ማንነት የአማራው ብቻ ሳይሆን የብዙ ብሄሮች ተወላጆችና የታላላቅ ከተማዎች ነዋሪዎችም መለያ ሁኗል፡፡ በእርግጥም በ1997ቱ ምርጫ ህዝቡ ለዘውግ-ዘለል ህብረ-ብሄራዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ድጋፉን መስጠቱ ለኢሀአዴግ ግልፅ መልዕክት ነበረው፡፡
እንደሚታወቀው ከመጠን በላይ የከረረው የብሄር ፌደራሊዝም ኢትዮዽያዊያን እንደልባቸው ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው እንዳይሰሩ አድርጓቸዋል፡፡ በጋብቻ ትስስር፣ በስራ፣ በመንደር ሰፈራ ወይም በፍልሰት ምክንያት ፌደራሊዝሙ ካሰመረላቸው ክልሎች ውጭ የተገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችም ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶቻቸው ለመጨፍለቁም ምክንያት ሆኗል፡፡ በብሄር-ተኮር ድርጅቶች የሚመሩት ክልሎች በአንድ ውህድ ህብረ-ብሄራዊ ፓርቲ ቢመሩ ኖሮ ግን ችግሩ ሙሉ በሙሉ ባይቀረፍም እንኳን መሻሻል ያሳይ እንደነበር በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡
ሆኖም ግን በተለይ ህወሃት የምርጫውን ውጤት የተረጎመበት መንገድ ከነባራዊ ሁኔታው ጋር የሚፃረር እንደነበር ግልፅ ይመስለናል፡፡ መቼም በውህድ ፓርቲ አወቃቀር ስሌት ህወሃት “በቁጥር ብልጫ ያላቸውን ብሄሮች በሚወክሉት ኦህዴድና ብአዴን እዋጣለሁ” በሚል ”የሥነ-ልቦና ቀውስ” (siege mentality) ውስጥ እንደገባ እሙን ነው፡፡ በሌላ አባባል “ወደ ህብረ-ብሄራዊ ፓርቲ መለወጣችን የታገልንለትንና የምንወክለውን ህዝብ ጥቅም ለድሮው ስርዓት ናፋቂዎች አሳልፈን እንድንሰጥ ያደርገናል” የሚል ፍርሃት ተጋቶበታል፡፡ ስለሆነም በውህደቱ አጀንዳ ላይ በረዶ እንደቸለሰበት ይታመናል፡፡
ሆኖም ግን በየትኛውም መለኪያ ውህደት በስልጣን ላይ ካሉት አመራሮች ጥቅም ጋር ይጋጭ እንደሆነ እንጂ የሚወክሉትን ህዝብ ጥቅም ስለመጉዳቱ አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ ያስቸግራል፡፡ በጥቅሉ የድርጅቱ በተለይም የህወሃት አመራሮች በውህደት ላይ ያሳዩት ባህሪ ለራሳቸው ጥቅም እንኳን የሀገሪቱን የድርጅታቸውንም ዘላቂ ጥቅም መስዕዋት ከማድረግ ወደኃላ እንደማይሉ ያረጋግጣል፡፡
የእስካሁኑ ነባራዊ ሁኔታዎች እስከመቼ እንደሚቀጥሉ በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም ህወሃት ቀሪዎቹን ሦስት ድርጅቶች በተናጥል ከፋፍሎ ስለያዛቸው የስኒ ማዕበል እንኳን እንዳያስነሱ አድርጓቸዋል፡፡ ህወሃት መጠነኛ ድርጅታዊና መንግስታዊ ለውጦችን የሚፈራ ድንጉጥ ድርጅት ውህደትን በእጅጉ ይፈራል፡፡ በአንፃሩ ግን አብላጫ ህዝብ የሚወክሉት ሌሎች አባል ድርጅቶች ግን ከውህደቱ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ዕድል እንደሚያሰፋላቸው ማሰባቸው አይቀርም፡፡ አንዱ የድርጅቱ ውስጣዊ ተቃርኖ ማሳያም ይህ ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ አባል ድርጅቶቹ ያልተመጣጠነ የስልጣን ክፍፍልና ሃብት ያላቸው ስለሆኑ የውህደት አጀንዳ ምንጊዜም አንገብጋቢ ነው፡፡ ህብረ-ብሄራዊ ፓርቲ የሚኖረው የስልጣን መዋቅርና የስልጣን ቦታዎች አሁን በኢህአዴግ ውስጥ ካሉት በእጅጉ ማነሱ አይቀርም፡፡ ስለሆነም አንዴ ነባራዊ ሁኔታው ስለሚናጋ ለትንሽ የስልጣን ቦታዎች በርካቶች ፉክክር ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ስልጣናቸውንና ውክልናቸውን አጥተው የሚንገዋለሉ በርካታ የዘውጌ ፖለቲከኞችና ካድሬዎች ስለሚኖሩ አኩራፊዎች ይበዛሉ፡፡ አኩራፊዎቹን ሁሉ በመንግስታዊ መዋቅሩ ውስጥ መሰግሰግ ካልተቻለ ደግሞ ለጋውን ህብረ-ብሄራዊ ፓርቲው ያዳክሙብኛል፤ ምናልባት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ቢካሄድ ደግሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ማሸነፍ እንቅፋት ይሆንብናል ብለው የድርጅቱ መሪዎች መስጋታቸው አይቀሬ ነው።
ለአዲሱ የስልጣን ድልድል የሚመረጡት መመዘኛዎችም የየድርጅቶቹ የትግል ታሪክ፣ ቀደም ሲል ይወክሉት የነበረው ብሄር ብዛት፣ ወይስ የግለሰቦች አመራር ችሎታና ብቃት? የሚሉት ጉዳዮች አጨቃጫቂ መሆናቸው አይቀርም፡፡ ሆኖም የብሄር ፌደራሊዝሙ ፍልስፍና ወይም አተገባበር ሳይሻሻል ከብሄር ውክልና በላይ ችሎታንና ብቃትን መመዘኛ ማድረግ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ችሎታና ብቃት ዋነኛ መመዘኛዎች ከሆኑ ግን በተለይ የኦህዴድና የደቡቡ ድርጅት አመራሮች ውህደትን ለመደገፍ ይቸገራሉ፡፡
ከሃብት አንፃር ካየነውም በ2000 ዓ.ም የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ አንቀፅ (31) የፖለቲካ ፓርቲዎች ውህደት ከፈፀሙ ምርጫ ቦርድ የእያንዳንዳቸውን ንብረትና ገንዘብ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ለውህዱ ድርጅት እንዲተላለፍ የማዘዝ ሥልጣን እንዳለው ይደነግጋል፡፡ ሆኖም የእያንዳንዳቸው ሃብት ብዛት አለመታወቁ አንድ ነገር ሆኖ በተለይ ግን ግዙፍ ሃብት እንዳለው የሚነገርለት ህወሃት ሃብቱን ለውህድ ህብረ-ብሄራዊ ድርጅት ለማውረስ ፍቃደኛ ይሆናል ወይ? የሚለው በጣም አጠራጣሪ ነው፡፡
ውህደት በአባል ድርጅቶች ላይ መለያ ድርጅታዊ አርማቸውንና ስያሚያቸውን የማጣት የስነ-ልቦና ችግር ማስከተሉም አይቀርም፡፡ መቼም የስነ-ልቦና ችግር ተጠቂ ላለመሆን አርቆ አሳቢ ፖለቲከኛ መሆን ይጠይቃልና፡፡ የስነ ልቦና ችግሩ ደግሞ በተለይ እስካሁንም የነፃ አውጭነት ስያሜን በያዘው ህወሃትና ብአዴን ላይ መበርታቱ አይቀርም፡፡
በውህደት በኩል እስካሁን በኢህአዴግ ውስጥ ተጨባጭ ልምድ አለ ከተባለ ቀደም ሲል የበርካታ የብሄር-ተኮር ድርጅቶች ግንባር የነበረው የደቡብ ኢትዮዽያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ደኢሕዴግ) ወደ ንቅናቄ መሸጋገሩ ቢሆንም ድርጅቶቹ ወደ የተዋሃዱት ግን በህወሃት ተገደው እንደሆነ በሰፊው ይታመናል፡፡ ቀደም ሲል በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ አምስት ክልሎች ፈርሰው የአሁኑን የደቡብ ክልል ለመመስረት የተገደዱትም በወቅቱ ጠቅላይ ሚንስትር ከነበሩት ታምራት ላይኔ ቢሮ በወጣ አንድ ቀጭን ደብዳቤ እንደነበር ጉዳዩን የተከታተሉ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ያኮረፉ የዘውጌ ፖለቲከኞችም በክልሉ በርካታ ትናንሽ ዞኖችና ወረዳዎች እንዲፈለፈሉ በማድረጋቸው የብሄር ፊደራሊዝሙን ክፉኛ እንዳከረሩት እሙን ነው፡፡ በአንፃሩ ግን ያጡትን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አካክሰውበታል፡፡ ሕዝቦች ግን ተጠቃሚ እንዳልሆኑ የክልሉን ሁኔታ የሚከታተል ሁሉ ያውቀዋል፡፡
የሀገሪቱ ህገ መንግስት በመግቢያው ላይ “አንድ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ስለመመስረት” ተስፋ ይሰጣል፡፡ ሌሎች ነገሮች እንደተጠበቁ ሆነው ለተስፋው ጨልሞ መቅረት አንዱ ተጠያቂ ግን የገዥው ድርጅት የብሄር-ተኮር አወቃቀር በመንግስታዊ አሰራሩ ላይ ያመጣው አሉታዊ ተፅዕኖ ነው፡፡
ለመሆኑ ከዚህ በኃላ ኢህአዴግ ምን አማራጮች አሉት? ብሎ መጠየቅ ይቻላል፡፡ ኢህአዴግና ሀገሪቱ የገቡበትን አጣብቂኝ መነሻ አድርገን ከመንግስት አንፃር ካየነው አንደኛ ራሱን እንደ ድርጅት በማፍረስ ሀገሪቱን ለባለአደራ መንግስት ማስረከብ ይችላል፡፡ በነገራችን ላይ የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ማንኛውም ፖለቲካ ድርጅት ራሱን በህጋዊ መንገድ ለማፍረስ የሚያስችለውን ህጋዊ ሁኔታ ከመደንገጉም በላይ ሁሉም ድርጅቶች ይህንኑ በየመተዳደሪያ ደንባቸው ማካተት እንዳለባቸው ግዴታ ጥሎባቸዋል፡፡ አስቂኙ ነገር ግን ኢሕአዴግ በውህደትም ሆነ በሌላ ምክንያት ራሱን ስለሚያፈርስበት ሁኔታ በመተዳደሪያ ደንቡ ውስጥ አላካተተም። ያም ሆነ ይህ እንዲያው ከመርህ አንጣር አነሳነው እንጂ የዚህ ቢሆን መላ ምት የመከሰት ዕድሉ ዝግ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ሁለተኛው አማራጭ እነ ፕሮፌሰር ተኮላ ሃጎስና ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ እየተከራከሩበት ያለው ስልጣኑን ለጦር ሰራዊቱ ማስረከብ ወይም ከጦር ሰራዊቱ ጋር ስልጣንን በመጋራት ስልጣኑን አስጠብቆ የመቆየት አማራጭ ነው፡፡
ሦስተኛው አማራጭ ድርጅታዊ ህልውናውን እንደጠበቀ የብሄራዊ አንድነት ሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ለሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች ጥሪ ማድረግ ነው፡፡ በእርግጥ ለድርጅቱም ለሀገሪቱም የሚሻለው ይህ አማራጭ ይመስላል፡፡ ሆኖም የቢሆን ዕድሉ ሊሳካ የሚችለው ድርጅቱና የሚመራው መንግስት ከባድ ቀውስ ውስጥ ከገቡ ብቻ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ከ1997ቱ የሚልቅ ፖለቲካዊ ቀውስ፡፡
መቼም ድርጅቱ ዋናውን ጅረት ትቶ በገባሮቹ ተወስኖ መቅረቱ እውን ሆኗል፡፡ የውህደትን ጥቅሞችና ጉዳቶችም እንዲያው ከመርህና ነባራዊ ሁኔታዎች አንፃር አነሳን እንጂ ከእንግዲህ ድርጅቱ ቢዋሃድም ለሚመራት ሀገር ችግሮች መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ባህሪውም የሚፈቅድለት አይመስልም፡፡ ከላይ ያየናቸው ክስተቶችም የድርጅቱ ውስጣዊ አንድነት መዛባቱን፣ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትም መላላቱንና ታዋቂው ፕሮፌሰር ሬኒ ሌፎርት ደጋግመው እንደሚሉት “አመራሩም በመደናበር ላይ ያለ” ስለሆነ (a leadership in disarray) እንዲሁ የሚመጣውን ሁሉ ለመቀበል የመረጠ ይመስላል፡፡