ዴሞክራሲ ማዕከላዊነት የጥቂቶችን ሀሳብ በብዙሀኑ ላይ በመጫን ይሁንታ ለማግኘት አምባገነን አገዛዝ የሚጠቀምበት መሳሪያ ሆኗል። ኢህ አዴግም የዚህ ሰለባ ሲሆን የፓርቲ ስልጣንን ለማስጠበቅ የሀገሪቱ ዕጣ ፈንታ በጥቂቶች ሀሳብ ላይ እንዲንጠለጠል ያደርገዋል ይለናል ተከታዩ የቻላቸው ታደሰ ዘገባ። አድምጡት
እንደሚታወቀው ገዥው ድርጅት ኢህአዴግ በርካታ መሰረታዊ ውስጣዊ ችግሮችና ተቃርኖዎች ያሉበት ድርጅት ነው፡፡ ከችግሮቹ መካከል አንዱ የሩሲያ ቦልሸቪኮች መመሪያ የነበረው የ“ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት” (democratic centralism) መርሁ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በአወቃቀሩ በውህድ ፓርቲነት ፋንታ የብሄር ድርጅቶች ግንባር ሆኖ መቅረቱ ነው፡፡ አወቃቀሩን ለሌላ ጊዜ እናስተላልፈውና በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ላይ በማተኮር በድርጅቱና በሀገሪቱ ላይ ያመጣውን መዘዝ ከሰሞኑ የግንባሩ ጉባዔ ውሳኔዎች ጋር እያንሰላሰልን እንመልከት፡፡ መቼም ስለ ኢህአዴግ ውስጣዊ ችግር የምናነሳው ተወደደም ተጠላ የድርጅቱ ተክለ-ሰውነትና ውስጣዊ ባህሪ በሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታና መፃዒ እጣ ፋንታ ላይ አሉታዊም ሆነ አወንታዊ አንድምታ ስላለው እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል።
በሀገራችን ፖለቲካ ውስጥ ከሰረፀ ግማሽ ምዕተ-ዓመት ያስቆጠረው ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የተወሰነ የሐሳብ ነፃነትንና የአብላጫ ድምፅ ውሳኔን የሚቀበል መርህ ነው፡፡ በዋናነት ግን በአንድ መንፈስ የተቃኘ የተግባር አንድነትን (unity of action) የሚጠይ በመሆኑ ዴሞክራሲን በአመዛኙ ለተግባር አንድነት ተገዥ ያደርጋል፡፡ ለዚህም ነው ምዕራባዊያን ምሁራን ቃሉን “የዴሞክራሲና ማዕከላዊነት ያልተቀደሰ ጋብቻ” (unholy marriage of democracy and centralism) በማለት የሚጠሩት፡፡
በእርግጥ የድርጅቱ ላዕላይ አመራር በጋርዮሽ አመራር (collective leadership) ላይ የተመሰረተ ስለሚሆን ሙሉ ስምምነት ላይ እስኪደርስ ለወራት የሚዘልቅ ውይይትና ክርክር ሊካሄድ ይችላል፡፡ በከፍተኛው አመራርና በሌላው አባል መካከል ግን አጥጋቢ የሃሳብ ውይይትና ክርክር አይካሄድም::
በአግድሞሽም ሆነ ከታች ወደ ላይ የተለየ ሃሳብን በግልፅ ማቀንቀን እንደ ሴራ መጎንጎንና አንጃ ማቋቋም ተደርጎ ይወሰዳል:: ከዲሞክራሲዊ ማዕከላዊነትም ጋር ፍፁም ተፃራሪ ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ከሃሳብ ትግል ይልቅ ተሳትፎን ብቻ የሚያበረታታ ስለሆነ ነፃ ሃሳብ የማንሸራሸር መብት የሚረጋገጠው ላዕላይ አመራሩ እስከፈቀደው ድረስ ብቻ እና አመራሩ የያዘውን አቋም የሚጋፋ እስካልሆነ ድረስ ብቻ ይሆናል:: በዚህ መርህ በሚመራ ድርጅት ውስጥ ተቃራኒ ሃሳብ የሚንሸራሸርበት መዋቅርም ሆነ አሰራር የለም፡፡ ለምሳሌ የኢህአዴግ ልሳኖች በሆኑት አብዮታዊ ዴሞክራሲ ጋዜጣና አዲስ ራዕይ መፅሄት ላይ ለየት ያለ ሃሳብ ተንፀባርቆ የማያውቀው ለዚህ ነው፡፡
ለምሳሌ በኢህአዴግ ጉባዔ ላይ ሞቅ ያለ ውይይትና ክርክር ቢደረግ እንኳ ምንጊዜም የሃሳብ ልዕልና ባለቤትና አድራጊ ፈጣሪ ተደርጎ የሚወሰደው የድርጅቱ ሥራ አስፈፃሚ የማይከለሰውንና የማይሻረውን የመጨረሻ ውሳኔውን ቀደም ብለው ማሳለፉ እየታወቀ ነው፡፡ ለዚህም ነው በድርጅቱ ነባርና አዲስ ትውልድ መካከልም የሃሳብ ትግል ስለመካሄዱ ተሰምቶ የማይታወቀው፡፡
የድርጅት ውሳኔዎች ሁሉ ከላይ ወደታች ይወርዳሉ፡፡ በታዕታይ መዋቅሩ ጋር የሚደረጉ ስብሳበዎች ሁሉ ዓለማቸው የላዕላይ አካላት ውሳኔዎችን ሙሉ በሙሉ ለማስረፅ እንጂ አዲስ ግብዓት ለመሰብሰብ ወይም ለማስገምገምና ለማስተቸት አይደለም፡፡ በውሳኔ አተገባበርም ተግባሪዎች እንደየነባራዊ ሁኔታው መጠነኛ ማስተካከያዎች እንኳ ማድረግ አይፈቀድላቸውም::
ለምሳሌ ከሁለት ዓመት በፊት ባህር ዳር በተካሄደው ጉባዔ ላይ አንድ ከፍተኛ የህወሃት አመራር በድንገት “በግንባሩ ውህደት ላይ መወያየት አለብን” ማለታቸው አጀንዳው ቀደም ብሎ ካለመያዙ አንፃር በግልፅ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን የጣሰ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት አቶ ተፈራ ዋልዋ በድሬዳዋና አዲስ አበባ ወጣቶች አደረጃጀት ላይ ብቻቸውን ተቃውሞ ሲያነሱም በአርምሞ የታዩት መርሁን እንደጣሱ ተቆጥሮ ነው፡፡
የኢህአዴግ አደረጃጀትም በጥብቅ ተዋረድ ላይ የተመሰረተ ሲሆን ወደ ፍፁማዊነት የተጠጋ የፓርቲ ስልጣንን ለጥቂት የድርጅቱ ቁንጮዎች አመቻችቷል፡፡ እነሱም የሃሳብ ልዕልና ያላቸው፣ የማይሳሳቱና የማይተኩ መሆናቸውንና የድርጅቱ ህልውናም በእነሱ ህልውና ላይ የተመሰረተ መሆኑን ለማሳመን ይጠቀሙበታል:: በከፍተኛው አመራርና ሌሎች አባላት መካከል ያለው ድርጅታዊ ተዋስዖም “Animal Farm” በተሰኘው የጆርጅ ኦርዌል ዝነኛ መፅሀፍ ያለው የአሳማዎችና ሌሎች እንስሳት ግንኙነትን ዓይነት ነው:: ስለሆነም ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በዋናነት በድርጅታዊ ዲስፕሊንና ውስጣዊ ድርጅታዊ አንድነት ሽፋን የማዕከላዊ ስልጣን ማስጠበቂያ መሳሪያ ሆኗል::
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ግን የሰሞኑ ግንባሩ ጉባዔ አቋም መግለጫ “ውስጠ-ድርጅት ትግል በማካሄድ ችግሮቻችን በስር ነቀልነት እንፈታለን” ሲል አውጇል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የውስጠ-ድርጅት ዴሞክራሲን ጠፍንጎ በያዘበት ሁኔታ ድርጅታዊና ሀገራዊ ችግሮች በምን ተዓምር በስር-ነቀልነት እንደሚፈቱ እንቆቅልሽ ነው፡፡ የድርጅቱ ቁልፍ ተቃርኖም ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡
ሌላኛው የጉባዔው የአቋም መግለጫ “መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ በድርጅታችን ውስጥ ተጠያቂነትን እናሰፍናለን” ይላል፡፡ እውነተኛ ውስጠ-ድርጅት ዴሞክራሲ ሳይኖር ተጠያቂነት ከየት ይመጣል? ከፈረሱ ጋሪውን ከማስቀደም ውጭ፡፡
በገዥው ድርጅት ውስት ዴሞክራሲያዊ ባህል ስለሌለ ለውጥ አራማጅ ቡድኖች ሊፈጠሩ አልቻሉም፡፡ የድርጅቱ የወጣት ክንፍ አባላትም እንኳን የደቡብ አፍሪካው ብሄራዊ ኮንግሬስ አባል እንደነበረው ጁሌስ ማሌማ ወሳኝ ትግል ሊያካሂዱ ቀርቶ ኮሽታቸውም አይሰማም፡፡ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትና የውስጠ-ዴሞክራሲ ዕጦት አኮላሽቷቸዋልና፡፡ ተተኪ ወጣት አመራሮች ቢመጡም እንኳ ነባሩን ገዥውን ሃሳብ እንዲያቀነቅኑ ተደርገው ስለተቀረፁ መተካካት የሚባለው ነገር ትርጉም አይኖረውም፡፡ በለውጥ ፈላጊ ሃይሎች ግፊትና በሃሳብ ብልጫ ያልተፈጠረ የመተካካት መርሃ ግብርም የይስሙላ ከመሆን አያልፍም፡፡
በጉባዔው አፅንዖት የተሰጠው የሚመስለው የመልካም አስተዳደር ችግር ውስብስብ መሆኑም ተረስቷል፡፡ ሊፈታ የሚችለውም በሳይንሳዊ መንገድ በሚመራ መንግስታዊ ቢሮክራሲ እንጂ በፓርቲ መዋቅርና በአመራር ተነሳሽነት ብቻ አይደለም፡፡ ገዥው ድርጅት ግን መንግስታዊ ቢሮክራሲያዊ መዋቅሩን በፓርቲ መዋቅር ሰንጎ ይዞታል፡፡ ድርጅታዊ ስንክሳሩን በሙሉ በመንግስታዊ መዋቅሩ ውስጥ አጋብቶበታል፡፡ መቼም የመልካም አስተዳር ችግር ከአንድ ጉባዔ ወደ ሌላኛው ሲንከባለል የኖረውም በኢህአዴግ ውስጠ-ድርጅት ዴሞክራሲ ዕጦት፣ የፓርቲና መንግስት መዋቅር መቀላቀል፣ የአመራሩና አስፈፃሚዎች ብቃት ማነስና የአሳታፊ ፖሊሲዎች አለመኖር ሳቢያ እንደሆነ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡
የጉባዔው መንፈስ በሙሉ የሚነግረን ድርጅቱ ዛሬም መሰረታዊ ጉዳዮችን ወደ ጎን ገሸሸ አድርጎ ችግሮችን ሁሉ ከ”አመራር ተነሳሸነት ጉድለት” እና ከአፈፃፀም ተግዳሮቶች ጋር ለማያያዝ መሞከሩን ነው፡፡ አንዳንድ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር አባላትና የመንግስት ባለስልጣናትም “ዋናው ችግር ያለው ከላይ ነው፤ ታች ያለውን አንቆ የያዘው ላይኛው አመራር ነው” ማለታቸው ይህንኑ ያጠናክራል፡፡ ታችኛው አመራር፣ ካድሬና መንግስት ሰራተኛ ሸምቀቆውን እንዳይበጥስ ያደረገውን ምክንያት ግን አይነግሩንም፡፡ ያን ማድረግ የዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህን በአደባባይ ማጋለጥ ይሆንባቸዋልና፡፡
ኢህአዴግ የተኮላሸ ድርጅት መሆኑን የሚያሳየን ለመልካም አስተዳደር መንኮታኮት ተጠያቂ መሆን የሚገባቸው የአቅም ማነስ ያለባቸው አመራሮቹን አሁንም በአመራርነት እንዲቀጥሉ ማድረጉ ነው፡፡ ጉባዔተኞቹም “ተጠያቂው አመራሩ ነው” ሲሉ በጥቅሉ ስለሆነ የትኛውንም ግለሰብና አባል ድርጅት ላለማስኮረፍ ታስቦ የሚደረግ የታይታ ስራ ነው፡፡ እንኳን መዋቅራዊ ለውጥ የአመራሮች ሹም ሽር ወይም ሽግሽግ እንኳ ለማድረግ የማይፈልግም የማይችልም ድርጅት ሆኗል፡፡ ጭራሸ ህወሃት ቀደም ሲል የተሰናበቱ አንጋፋ አመራሮቹን እንዲመለሱ አድርገዋል፡፡ ለምን? ቢባል በድህረ-መለስ ዘመን የህወሃት የበላይነት እየተሸረሸረ ነው የሚል ስጋት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
በአባል ድርጅቶች ውስጥ ብቻ ሳይሆን በድርጅቶች መካከልም መፈራራትና መጠባበቅ እንጂ ፖለቲካዊ ትግል ስለማይካሄድ ሀገሪቱ ተጎጂ ሁናለች፡፡ ሆኖም ኢህአዴግ ውስብስብ ሀገርን እየመራም እንኳን በውስጡ ድርጅታዊ ቅራኔዎች አለመከሰታቸውን እንደ ጥንካሬና ጤናማነት ሊያቀርበው ይፈልጋል፡፡ መቼም ቅራኔን፣ ዴሞክራሲያዊ ክርክርን፣ አዳዲስና ተራማጅ ሃሳቦችን የማይወልድ ድርጅት ጤናማ ነው ብሎ ማለት ያስቸግራል፡፡ እስካሁን ተቃርኖውን ያስቀረው ዋናው ምክንያት ግን የዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ልጓምን አንቆ በያዘው ህወሃትና በሌሎች አባል ድርጅቶች መካከል ያለው የጎንዮሽ ግንኙነት የ”ዳዊትና ጎሊያድ” መልክ ያለው በመሆኑ እንደሆነ ኢሕአዴግን ያጠኑት እነ ፕሮፌሰር ክርስቶፈር ክላፋምና ሳራ ቮግ የመሳሰሉ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡
ፍትሃዊ ስልጣንና ሃብት ክፍፍል፣ ድርጅታዊ አወቃቀር፣ የመንግስትና ፓርቲ አንድነትና ልዩነት፣ የጦር ኃይሉ ተዋፅዖና ህገመንግስታዊነት፣ የፌደራል ሥርዓቱ የተመሰረተበት ፍልስፍናና አፈፃፀሙ፣ የበጀት ድልድል፣ የመልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ የመሬት ፖሊሲና የብሄር ጥያቄ የመሳሰሉት ሁሉ ቁልፍና አንገብጋቢ ጉዳዮች ሆነው ሳለ ድርጅታዊ ቅራኔ ሊፈጥሩ ላለመቻላቸው አንዱ ምክንያት ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ነው፡፡ ኢህአዴግ ብዝሃ አመለካከቶችን የምታስተናግድ ኢትዮጵያን ለመመስረት ላለመቻሉም እንዲሁ፡፡
የገዥው ድርጅት ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የፊደራሊዝሙን ስርዓት ጭምር የተማከለ እንዲሆን አድርጓል፡፡ እነ ፕሮፌሰር ሳራ ቮግ፣ አለን ሎቪስ እና ዶክተር አሰፋ ፍስሃ የሀገሪቱን ፌደራሊዝም ለማጥናት ከመደበኛው ህግመንግስታዊ አወቃቀር ይልቅ በኢህአዴግ ኢመደበኛና የመጋረጃ ጀርባ አሰራር ላይ የሚያተኩሩትም ለዚህ ነው፡፡
ኢህአዴግ መቼም ቢሆን የሚታደስ ድርጅት አይመስልም፡፡ ለመታደስ መሞከር ውስጣዊ ድርጅታዊ ንቃቃት ይፈጥርብኛ ብሎ ሰግቷል፤ ንቃቃቱን መቋቋም የሚችልበት መዋቅር ደግሞ የለውም፡፡ ከእንግዲህ “ነብር ዥንጉርጉርነቱን…“ እንደሚባለው ሁሉ እንኳን ግብሩን የግንባርነት አወቃቀሩንና ስያሜውን እንኳ ይቀይራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ አሁን የሀገሪቱ ችግር ከድርጅቱ አቅም በላይ እንደሆነበት ከማንም ታዛቢ የተሰወረ አይደለም፡፡ አንድ ቀን ግጭቶችና የታፈኑ ቅራኔዎች ሲገነፍሉ ግን ሀገሪቱን አርማጌዶን እንዳይውጣት ያሰጋል፡፡