Eni Egypt gasበአፍሪካ ግዙፉ የሆነው የጣሊያኑ ኤኒ የነዳጅ ኩባንያ የግብፅ ግዛት አካል በሆነው ሜዲትራኒያን ባህር ውስጥ ከ30 ትሪሊዬን ኩዩቢክ ጫማ ወይም 850 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ያህል የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ማግኘቱን ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ አስታውቋል፡፡ የዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙሃንም ዜናውን የተቀባበሉት ወዲያውኑ ነበር፡፡ ክምችቱ ኩባንያው ቀደም ሲል ሞዛምቢክ ውስጥ ካገኘው 75 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ ግማሽ ያህል መሆኑ ነው፡፡ ኩባንያው በመጭዎቹ ሁለት ዓመታትም ምርት እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡ አሁን ባለው ስሌት ክምችቱ የግብፅን ነዳጅ ፍላጎት ለሁለት አስርት ዓመታት ማሟላት ይችላል ተብሎለታል፡፡ ተፈጥሮ ጋዝ ለኢንዱስትሪ፣ ለተሽከርካሪዎች፣ ለምግብ ማብሰያ ጋዝ እና ኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨት ይውላል፡፡
የክምችቱ መገኘት ዜና የተበሰረው ግብፅ ታሪካዊ ወቅት ላይ ባለችበት ወቅት ነው፡፡ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ስምንት ቢሊዮን ዶላር የፈጀውን የስዊዝ ካናል ማስፋፊያ ፕሮጀክት መርቀው በከፈቱ በወሩ ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የእስልምና አክራሪ ቡድኖች በሳይናይና ካይሮ ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶችን እያደረሱ ባሉበት ወቅት፡፡

በተለይም ደግሞ ግብፅ የኢትዮጵያው ታላቁ ህዳሴ ግድብን ነባራዊ ሁኔታ ተቀብላ ስምምነት በፈረመችበት ማግስት፡፡ በአንጣሩ ደግሞ ከፀደዩ አብዮት ጀምሮ ከተከሰቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች እያገገመች ባለችበት ወቅትና የሃይል አቅርቦት እጥረቷን ለማሟላት በተጨነቀችበት ወቅትም ጭምር ነው፡፡

የቻላቸው ታደሰን ዘገባ አድምጡ

 

 

የግብፅ የአምና ተፈጥሮ ጋዝ ፍጆታዋ ብቻ 1.7 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በእርግጥ ግብፅ ድሮውንም የተፈጥሮ ጋዝ ባለቤት ብትሆንም የወስጥ ፍጆታዋን ግን መሸፈን የሚያስችላት አልነበረም፡፡ ያም ሆኖ ግን ለእስራዔል ከዓለም ዓቀፍ ዋጋ በታች ስትሸጥ ቆይታለች፡፡ ተቃርኖው ግን በምርት መስተጓጎልና ፍጆታ መጨመር ሳቢያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ዋነኛ የተፈጥሮ ጋዝ አስመጭ ሆና ነበር፡፡ እንዲያውም እስራዔል ገና ያልተጠቀመችበት ጋዝ ክምችት ስላላት እርሱን ስታወጣ ግብፅም መሸጧን ትታ ከእስራዔልም ለመግዛት እየተደራደረች ነበር፡፡
ላለፉት ጥቂት ዓመታት ዓለም ዓቀፍ ኩባንያዎች በሃይል አቅርቦት እጥረት ሳቢያ በግብፅ ያላቸው ኢንቨስትመንት ተገድቦ የቆየ ሲሆን ሀገሪቱም ለበርካታ ዓመታት በሃይል መቆራረጥ ችግር ስትሰቃይ ቆይታለች፡፡ በተለይ ከ2011ዱ አብዮት ወዲህ ኢኮኖሚዋ በዚህ ሳቢያ በእጅጉ ተጎድቷል፡፡
አሁን ዋናው ጥያቄ የክምችቱ መገኘት በታላቁ ህዳሴ ግድብና በጠቅላላው በግብፅ ውስጣዊ ሁኔታና አካባቢያዊ ሃያልነቷ ላይ ምን አንድምታ ይኖረዋል? የሚለው ነው፡፡ በመጀመሪያ ግን የጋዝ ክምችቱን ያገኘውም ሆነ የኢትዮጵያውን ታላቁ ህዳሴ ሃይድሮ-ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ የሚገነባው ኩባንያ ሁለቱም የጣሊያን ኩባንያዎች መሆናቸውን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡
ግብፅ የጋዝ ክምችቷን ምን ዓይነት ዓላማዎችን ለማሳካት ትጠቀምበት ይሆን? ብለን ብንጠይቅ ሁለት እርስበርስ የሚደጋገፉ መሰረታዊ ዓላማዎችን መለየት እንችላለን፡፡ አንደኛ በኢነርጂ አቅርቦት ራሳን ችላ በኢንዱስትሪ የበለፀገች መሆን ነው፡፡ እስካሁንም በገጠማት ገንዘብ እጥረት ሳቢያ በርካታ የኢንርጂ ኩባንያዎች ሙዋለ-ንዋያቸውን ለማፍሰስ ሲያንገራግሩ ቆይተዋል፡፡
መንግስትም ለበርካታ ዓመታት ለነዳጅ ድጎማ ማድረጉ የህብረተሰቡን ፍጆታ ስለጨመረው የግብፅ ዓመታዊ የተፈጥሮ ጋዝ ፍጆታ 50 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ደርሶ ነበር፡፡ ስለሆነም ባለፈው ዓመት አል ሲሲሰ አብዛኛውን የጋዝ ድጎማ ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡ ግብፅ ለነዳጅ የምታውለው ድጎማ ከሀገሪቱ በጀት 22 በመቶውን ሲወስድ 18 በመቶው ደግሞ ለኤሌክትሪክ ሃይል ድገማ ይውል እንደነበር በቅርቡ ባወጣው አንድ ሪፖርት ይገልጣል፡፡ ይህም ለትምህርት፣ ጤናና መሰረተ ልማት በድምሩ ከሚውለው ድጎማ ይበልጣል፡፡
የአሁኑ የጋዝ ግኝት ግን መሰረተ-ልማቷን በሰፊው ለማስፋፋትና የተስተጓጎለውን የኢንቨስትመንትንት ፍሰትም እንደገና ለመሳብ ይረዳታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የውስጥ ፍላጎቷንም ሙሉ በሙሉ ስለሚሸፍን ከውጭ ነዳጅ በማስገባት የምታወጣውን ወጭ ለሌሎች ፕሮጄክቶች ማስፈፀሚያ ለማዋል ያስችላታል፡፡

ሁለተኛ ደግሞ ለጥቂት ዓመታት ተዳክሞ የቆየውን ሃያልነቷን እንደገና በማጠናከር በአባይ ተፋሰስ ሀገሮች በተለይም በኢትዮጵያ ላይ ተጥዕኖ ለማድረግ ልትጠቀምበት ታስብ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን ተፈጥሮ ጋዙ ምርት ከመጀመሩ በፊት የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚጠናቀቅበት ዕድልም ይኖራል፡፡ መቼም የሃይል አቅርቦት አንገብጋቢ በሆነበት ዘመን የተፈጥሮ ጋዙ መገኘት ጅኦ-ፖለቲካ፣ የንግድና ኢንቨስትመንት አንድምታው ብዙ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡ ክምችቱ ከዋናኛዎቹ ነዳጅ ዘይት አምራቾች ተርታ ያሰልፋታልና፡፡

በእርግጥ አል ሲሲን ከቀደምቶቻቸው የሚለያቸው በውጭ ፖሊሲ ከመወዛገብ ይልቅ ዋና ትኩረታቸውን የውስጡን ኢኮኖሚ በማረጋጋት ላይ ማተኮራቸው ነው፡፡ የአሁኑ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችቱም ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገር የሰውዬውን ፖለቲካዊና ህጋዊ ቅቡልነት እንዲሁም በጠቅላላው የሀገሪቱን ተደማጭነት እንደሚጨምር ይታመናል፡፡ ወታደራዊ ተቋሙም ከአዲሱ ትሩፋት ተጠቃሚ መሆኑ አይቀርም፡፡ በተለይ ወታደራዊ ኢንዱስትሪዎቹን በማጠናከር ረገድ፡፡
የፈረንሳይና ኔዘርላንድ አጥኝ ኩባንያዎች ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ ሀገሮች ላይ ስለሚያስከትለው ጉዳት በጋራ እያጠኑ ቢሆንም፤ ግብፅም ከኢትዮጵያና ሱዳን ጋር የሦስትዮሽ የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረመች ቢሆንም የተፈጥሮ ጋዙ ግኝት ግን ሂደቱን አቅጣጫ ያስቀይረው ይሆን? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል፡፡ መቼም ግብፅ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አጣቂኝ ውስጥ ስለገባች እንጂ አሁን በአባይ ወንዝ በተለይም በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለውን ነበራዊ ሁኔታ (status quo) በሙሉ ልብ መቀበሏ ያጠራጥራል፡፡

በዲፕሎማሲም ረገድ ቢታይ አዲሱን ግዙፍ ሃብቷን በምስራቅ አፍሪካ የአባይን ፖለቲካ ለመዘወር ልትጠቀምበት መሞከሯ አይቀርም፡፡ በተለይ ሱዳን የህዳሴውን ግድብ መደገፏ ሳያበሳጫት አልቀረም፡፡ ስለሆነም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ቢቀር እንኳ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን የኢንቴቤው ክፍለ-አህጉር አቀፍ የናይል ወንዝ አጠቃቀም ስምምነት አካል እንዳይሆኑ ለማድረግ መሞከሯ አይቀርም፡፡

 

በአንፃሩ ግን ግድቡ ውሃ አጠራቅሞ ስለሚቆይ በድርቅ ጊዜ እንኳን ወንዙ ያለማቋረጥ እንዲፈስ ስለሚያደርግ ለሱዳን እስካሁን ከምታገኘው ውሃ የበለጠ ሊያስገኝላት ይችላል ይላሉ አንድ የስቶክሆልም ዓለም ዓቀፍ ውሃ ተቋም ባለሙያ፡፡
ከደቡብ ሱዳን ጋር የጀመረችውን ወታደራዊ ትብብርና ዕርዳታም የበለጠ ለማጎልበት ልትጠቀምበት ትችላለች፡፡ በተለይ የጆንገሌ ካናልን በመገንባት በዓመት እስከ 7 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ከትነት ለማስቀረት ያቀደችው እኤአ ከ1975 ዓ.ም ጀምሮ ቢሆንም እስካሁን ተግባራዊ ማድረግ አልቻለችም፡፡ ደቡብ ሱዳናዊያን ስነ-ምህዳራዊና ሰብኣዊ መዘዞችን በመፍራት በዕቅዱ ደስተኞች ባይሆኑም ጉዳዩ ግን ከደቡብ ሱዳን ግጭት በፊትም እንደገና መንቀሳቀስ ጀምሮ ነበር፡፡ ምናልባት የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ከሆነ በአካባቢው ላይ ስልጣን የሚኖራቸው ተቃዋሚው ሬክ ማቻር ምን ዓይነት አቋም እንደሚይዙ ወደፊት ይታያል፡፡

ግብፅ እስካሁንም ግድቡ በውሃ እስኪሞላ ድረስ እስከ ስድስት ዓመታት ድረስ ስለሚወስድ የውሃው ፍሰት መጠን ይቀንሳል የሚለው ስጋቷ እንዳለ ነው፡፡ ይህም በተለይ ከአስዋን ግድብ የማነቸውን ሃይል ይቀንስብኛል ባይ ናት፡፡ ስጋቷንም በሁለት ጥናቶች ለማስረዳት ሞክራለች፡፡

ታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚያስቀረው ውሃ መጠንም በየዓመቱ ከዘጠኝ እስከ 12 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እንደሚደርስና ግዙፍ የእርሻ መሬቷም ያለ ውሃ በማስቀረት በግብርናው ላይ ከባድ ጉዳት እንደሚያደርስ የግብፁ አል ሞኒተር ጋዜጣ ባለፈው ወር ዘግቦ ነበር፡፡ ብዙውን ጊዜ ከግብፅ መገናኛ ብዙሃ የሚወጡ መረጃዎች ተዓማኒነት ቢጎላቸውም፡፡ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ግድቡ ለመስኖ ስራ እንደማይውል ደጋግመው ከመግለፅ ባይቆጠቡም 168 ሜትር ከፍታ ያለው ግድብ ከፍታው እንዲቀንስ ግብፅ ትፈልጋለች፡፡ ግድቡ የሚይዘው የውሃ መጠንና የታቀደው ስድስት ሺህ ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ሃይልም እንዲቀንስ ማለት ነው፡፡
ያም ሆነ ይህ ግብፅ በኤሌክትሪክ ሃይል ራሷን መቻሏ በኢትዮጵያ ላይ ሁለት ተፃራሪ ታሳቢ ውጤቶች ሊያስከትል ይችላል፡፡ በአንድ በኩል የጋዙ መገኘት የግብፅን ሃይል ማመንጫ አማራጮች ስለሚያሰፋላት ኢትዮጵያ ከህዳሴው ግድብ ከሚመረተው ኤሌክትሪክ ሃይል ለግብፅ ለመሽጥ ያላትን ተስፋ ያሟጥጠዋል፡፡ በተፈጥሮ ጋዝ የሚታዝ ኤሌክትሪክ ምርት ደግሞ በጣም ውጤታማ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ እንዲያውም ግብፅ የኤሌክትሪክ ግሪድ በመዘርጋት ለሱዳንም በመሽጥ የኢትዮጵያን ኤሌክትሪክ ሽያጭ ተስፋ ታጨልመው ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ኤሌክትሪክ ሃይል በመሽጥ በዓመት እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር ሊያገኝበት እንደሚችል የዓለም ባንክን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በሌላ በኩል ግን ከሃይል አቅርቦት አንፃር ብቻ ከታየ የአስዋን ግድብ የውሃ መጠን መቀነስ እምብዛም ስለማያሳስባት በህዳሴው ግድብ ላይ ያላት ተቃውሞ ሊለዝብ ይችላል፡፡ አስዋን ግድብ የግብፅን 15 በመቶ ሃይል አቅርቦት እንደሚሽፍን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ችግሩ ግን የናይል ወንዝ የሃይል አቅርቦት ብቻ ሳይሆን የእርሻ፣ አሳ ምርትና መጠጥ ውሃ አቅርቦት ጭምር ዋነኛ ምንጭ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ስናየው የተፈጥሮ ጋዙ መገኘት ግብፅ በህዳሴው ግድብ ላይ በምትከተለው ፖሊሲ ላይ የሚኖረው አወንታዊ አስተዋጥዖ እምብዛም ያደርገዋል፡፡
አኤአ በ2050 የግብፅና ኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት በድምሩ በ100 ሚሊዮን እንደሚጨምር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በተለይ የግብፅ ህዝብ በሚቀጥሉት ስምንት ዓመታት ብቻ በአማካይ በ10 ሚሊዮን ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አሁን የተገኘው የተፈጥሮ ጋዝ ክምችትን ነጥለን ከወሰድነው ደግሞ ለግብፅ የሚበቃት ለሃያ ዓመታት ብቻ እንደሆነ የጣሊያኑ ኩባንያ ይናራል፡፡ በረዥም ጊዜ አንፃር ሲታይ ግን የግብፅ ህዝብ ቁጥር በፍጥነት መጨመርና ከኢኮኖሚዋ ማንሰራራቱ ጋር ሲዳበል የነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ፍጆታዋም በዚያው መጠን ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በጥቅሉ ሲታይ አዲሱ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ለግብፅ ላይ ከሰማይ እንደወረደ መና ይቆጠራል፡፡ ያ ማለት ግን መሰረታዊ ችግሮቿን ሙሉ በሙሉ ይቀርፋል ማለት አይደለም፡፡ ግብፅ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ከምትቀያይረው አቋሟ አንፃር አዲሱ ግኝት ምን ያህል ባህሪዋን እንደሚቀይረው በመጭዎቹ ወራት የሚታይ ይሆናል፡፡ ግብፅ ያለ የሌለ ሃይሏን አሟጣ ብትንቀሳቀስ ኢህአዴግ-መራሹ መንግስትም ተንበርካኪ ላለመሆኑ ወደፊት ይታያል፡፡