PHOTO Credit – TRT

ዋዜማ ራዲዮ-  የኮቪድ 19 ክትባት የፀጥታ ችግር ካለባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች በቀር በሁሉም ክልሎች እና ወረዳዎች መዳረሱን የጤና ሚኒስትር ገለፀ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ሙሉቀን ዮሀንስ ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡

በኮቫክስ ኢኒሼቲቭ አማካኝነት የካቲት 28 ቀን 2013 ዓም 2.2  ሚሊዮን አስትራዜኒካ የተባለውን የኮቪድ 19 ክትባት ኢትዮጵያ መረከቧ ይታወሳል፡፡

በጥቅሉ 7.62 ሚሊዮን ክትባቶችን ለመረከብ የታቀደ ሲሆን ቀሪው በግንቦት ወር ወደ ሀገር እንደሚገባ ተነግሯል፡፡

በፈርንጆቹ 2021 ማገባደጃ ድረስ ከጠቅላላ ህዝብ ቁጥር 20 በመቶ (22 ሚሊዮን ገደማ) የሚሆኑትን ዜጎች ለመከከተብ የታቀደ ሲሆን እስካሁን ምን ያህል ሰው ክትባቱ እንደደረሰው የሚያሳይ ቁጥር ገና እየተሰባሰበ መሆኑ ተገልፆልናል፡፡

“መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓም የክትባት መስጠት ስነስርዓቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ በይፋ ከተጀመረ በኋላ ከፍተኛ ትኩረት የሰጠነው  በየክልሉ እና በሁሉም የጤና ኬላ እና ጣቢያዎች ማሰራጨት፣ ስልጠና መስጠት እና ክትባቱን መስጠት ላይ ነው፡፡ የጤና ባለሞያዎች ተከትበዋል፡፡ አሁን ደግሞ ከ65 አመት በላይ የሆናቸውን እና ከ55 በላይ ሆኗቸው ተጓዳኝ ህመም ያለባቸውን መከተብ ጀምረናል፡፡ ምን ያህል ሰው እስካሁን ተከተበ የሚለውን ቁጥር እንግዲህ ከሚቀጠጥለው ሳምንት በኃላ ሰርተን እናሳውቃለን፡፡” ብለዋል ዶ/ር ሙሉቀን

ከዚህ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ክትባቱ እየተሰጠባቸው ባሉ የተለያዩ ጤና ጣቢያዎች ተዟዟራ የተመለከተችው የዋዜማ ሪፖርተር ክትባቱን ለመውሰድ የተገኙ በርካታ አዛውንቶች አካላዊ ርቀትን መጠበቅ በማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ ሆነው መታዘቧንና አዛውንቶቹ ለበሽታው ይበልጥ ተጋላጭ እንዳይሆኑ የተሻለ አሰራር ለምን እንዳልተመቻቸ አማካሪውን ጠይቃለች፡፡

“እውነት ነው በአንዳንድ ጤና ጣቢያዎች እንዲህ አይነት ሁኔታ እንደተፈጠረ መረጃው እኛም ደርሶናል ማስተባበል አንችልም፡፡” ያሉት ዶ/ር ሙሉቀን “ጥቆማው እንደደረሰን በስልክ ደውለን እንዲስተካከል ነግረናል በቀጣይ ቀናትም እያስተካከልን እንሄዳለን፡፡” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡  [ዋዜማ ራዲዮ]